ውድድሮችን ለመጀመር የሚያስችለው መነሻ ሰነድ ለክለቦች ቀረበ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እንዲሁም የ1 እና 2ኛ ሴቶች ሊግ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ክለቦች ጋር ዛሬ በካፍ የልህቀት ማዕከል ባደረገው ውይይት ውድድሮችን ለማስጀመር የሚያስችል መነሻ ሰነድ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የእግርኳስ እንቅስቃሴዎች እንዲመለሱ የመነሻ ሰነድ አዘጋጅቶ እንደነበረ ይታወቃል። ሰነዱም ለየክለቦቹ ተወካዮች ቀርቦ ውይይቶች ተደርገዋል። ሰነዱ ከመቅረቡ በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለተሰብሳቢዎቹ መጠነኛ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በገለፃቸውም ውድድር እንዴት መደረግ እንዳለበት ለመመካከር ወይይቱ እንደተዘጋጀ ጠቁመዋል።”ዛሬ በዚህ ቀን እንጀምራለን አንልም። መንግስት ጀምሩ ሲለን እንዴት እንደምንጀምር ለመወያየት እንጂ። ስለዚህ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ጠንካራ ውይይት አድርጋችሁ አቅጣጫ አስቀምጡ።”

ከፕሬዝዳንቱ መጠነኛ ንግግር በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አ/ማ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ማሞ አጭር ንግግር በተከታይነት አድርገዋል። “በመነሻ ሰነዱ ላይ የሊግ ካምፓኒው እንዲሳተፍ መደረግ ነበረበት። ከእናንተ ጋር ሆነን ሰነዱን ብናዘጋጅ የተሻለ ነገር እናመጣ ነበር። ለወደፊቱ ይሄ አካሄድ እንዲታረም እንፈልጋለን። ካለበለዚያ ካምፓኒው አይቋቋም።”

አጭር ገለፃው ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና የሴቶች ሊግ ተወካዮች ለብቻ እንዲሁም በ3 ምድብ የሚገኙ የከፍተኛ ሊግ ክለብ ተወካዮች በሁለት ተከፍለው የተዘጋጀው መነሻ ሰነድ ለውይይት ቀርቦላቸዋል።

መነሻ ሰነዱን ካዘጋጁት ግለሰቦች ውስጥ አቶ ቴድሮስ ፍራንኮ ለፕሪምየር ሊግ ተወካዮች፣ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ እና አቶ ሙሉጌታ ምስገናው ደግሞ በሁለት ለተከፈሉት የከፍተኛ ሊግ ክለብ ተወካዮች ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት እና የውድድርና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን ሰነዱን አቅርበዋል።

30 ገፆች ያሉትን ይህንን ሰነድ ለማዘጋጀት 8 ሳምንታት እንደፈጁ የተገለፀ ሲሆን በውስጡ ያሉትንም ሃሳቦች እንደሚከተለው እናቀርባለን። (በሶስቱም አዳራሾች የነበረው ገለፃ ተመሳሳይ ነው)

በዋናነት ውድድሮች ሲመለሱ መመርመር- መለየት- ማከም የሚለውን የዓለም የጤና ተቋም መርህ ተከትሎ ወደ ውድድር ለመመለስ እንደታሰበ ተገልፃል። ከዚህ በታች የተጠቀሱት እና በዛሬው እለት በልህቀት ማዕከሉ የቀረበ የመነሻ ሃሳብ ለሁሉም የውስጥ ሊጎች እንዲያገለግል የተደረገ ሲሆን ከውድድሮቹ ባህሪ አንፃር የውድድር ማድረጊያ ቦታዎች ብቻ የተለያዩ ሆነው ቀርበዋል።

* የእግርኳስ እንቅስቃሴን ለማስጀመር ሊሟሉ የሚገባ ቅድመ ሁኔታዎች

ፌደሬሽኑ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር ከዚህ ቀደም ይሰሩባቸው የነበሩ የውድድር ደምቦችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንፃር በመቃኘት ፕሮቶኮል እንደተዘጋጀ ተገልጿል። ከተለመዱት ደምቦች በተጓዳኝ የሰዎች ቁጥሮችን መወሰን፣ የጉዞ መመሪያ፣ የተጫዋቾች እና መሰል አካላት እንቅስቃሴ፣ ንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም በሽታውን ለመቆጣጠር የሚረዱ መመሪያዎች ተካተውበታል። ከነዚህም መካከል:-

– በውድድር ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት እንዲሁም ንክኪ የሚኖራቸው ድገፍ ሰጪ አካላት ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት 72 ሰዓት ያልሞላው ነፃ የሆነበትን የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት ማቅረብ አለባቸው።

– ከላይ የተጠቀሱት አካላት ናሙና ከሰጡ በኋላ ውጤት እስኪመጣ ራሳቸውን ማግለል ይጠበቅባቸዋል።

– በላብራቶሪ ውጤት ነፃ ሆኖ ነገርግን ምልክቶች የታዩበት ተጫዋች ከሆነ በክለቡ የጤና ባለሙያ ታይቶ ለጨዋታ ብቁ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ መጫወት ይችላል።

-ሁሉም ክለቦች የኮቪድ የጤና መኮንን(health officer) መቅጠር ይኖርባቸዋል።

-ተጫዋቾች የሚሰማቸውን ስሜት ለክለቡ የኮቪድ መኮንን መንገር ወይም የ24 ሰዓት ውሎ የሚያስረዳ ፎርም መሙላት አለባቸው።

-ተጫዋቾች እና ባለሙያዎች ከህብረተሰቡ ጋር እንዳይቀላቀሉ ቋሚ የሆነ የመቀመጫ ቦታ (ካምፕ) መዘጋጀት አለበት።

-ክለቦች በኢፌዲሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር መመሪያ መሰረት መጓጓዣ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል።

-ውድድሮች ውስን እና የተመረጡ ስታዲየሞች ላይ ብቻ በዝግ ይከናወናሉ።

-የቴክኒክ ቁሳቁሶች (ኮን፣ ኳስ እና የመሳሰሉት) በፀረ ተህዋሲያን ቶሎ ቶሎ መፅዳት አለባቸው።

-ሁሉም ተጫዋች በስማቸው የተለየን ቁሳቁስ ብቻ ይጠቀማሉ።

*በጨዋታ እና በስልጠና ወቅት ሊሟሉ የሚገባ ቅድመ ጥንቃቄዎች

-በስልጠና ወቅት ርቀትን የጠበቁ ልምምድ ማከናወን።

-በጨዋታ ወቅት ዳኛን ከቦ ማናገር እና መከራከር የተከለከለ ነው።

-ኳስ አቀባዮች ኳስን በእግራቸው ብቻ እንዲያቀብሉ ይደረጋል።

-በጨዋታ ጊዜ አንድ ተጫዋች የተጋጣሚን ተጫዋች ለረጅም ጊዜ መከታተል አይችልም።

-ጎል አስቆጥሮ በጋራ ደስታ መግለፅ አይቻልም።

-ጨዋታው ሲጠናቀቅ ሁሉም በአንድ ጊዜ ከሜዳ እንዲወጡ ከማድረግ ይልቅ በየተራ እንዲወጡ ይደረጋል።

-ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጫዋቾች መታጠብ (ሻወር መውሰድ) ያለባቸው በመኖሪያ ካምፓቸው ብቻ መሆን አለበት።

-ተጫዋቾች የራሳቸውን ትጥቅ ከፍ ባለ የሙቀጥ መጠን ባለው ውሃ (እስከ75°c) እራሳቸው እንዲያጥቡ ይመከራል።

-ሁሉም ከሜዳ ውጪ የሚገኙ አካላት(ከዋና አሰልጣኝ በስተቀረ) የአፍ እና የአፍ መሸፈኛ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ርቀታቸውን የመጠበቅ ግዴታ ይጠበቅባቸዋል።

-ከላይ የተጠቀሱት መመሪያዎችን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የጤና ሚኒስቴር ባዘጋጁት ቼክ ሊስት ቡድኖች ይገመገማሉ።

*ውድድር የሚጀመርበት ጊዜ እና ቦታዎች

-የጤና ጥበቃ ፍቃድ ከተገኘ እና የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ ውድድሮች ከ6-8 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጀመራሉ።

-ውድድሮች ያለ ደርሶ መልስ በአንድ ዙር ብቻ ይከናወናሉ።

-በዛሬው የምክክር መድረክ ላይ በቀረበው ሰነድ መነሻነት ክለቦቹ የሚገኙበትን ክልል ባማከለ መልኩ 6 የውድድር ስፍራዎች ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር መመረጣቸው ተገልጿል። እነሱም ባህር ዳር፣ አዳማ አበበ ቢቂላ፣ ሃዋሳ፣ ትግራይ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ስታዲየሞች ናቸው።

-የከፍተኛ ሊግ ውድድርን በተመለከተ ቡድኖች የሚገኙበትን ቦታ ባማከለ መልኩ የተለያዩ ቦታዎች በመነሻነት ተለይተዋል።
የምድብ ሀ በአዲስ አበባ/አበበ ቢቂላ እና ወልዲያ ስታዲየሞች፣ በምድብ ለ በሃዋሳ እና ነቀምት/ጅማ ስታዲየሞች እንዲሁም የምድብ ሐ ጨዋታዎች በመድን እና በወላይታ ሶዶ ስታዲየሞች ላይ እንዲካሄዱ የምክረ ሃሳብ ቀርቧል።

*ከሰነዱ ገለፃ በኋላ የነበረውን ውይይት እና የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ከቆይታ በኋላ ይዘን እንመለሳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ