የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ ተከናውኗል

13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እጣ ማውጣት እና የደንብ ውይይት ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል ሲከናወን በቦታው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛዎችም ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

4:30 የተጀመረው ፕሮግራምን ከስምንቱ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት አምስቱ በመድረኩ ተገኝተው የመሩ ሲሆን በውድድሩ የሚካፈሉ የክለብ ተወካዮችም በቦታው ተገኝተው የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓቱን አካሂደዋል።

ፕሮግራሙን በንግግራቸው የከፈቱት አዲሱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍስሃ(ኢ/ር) በለቱ ለተገኙ አካላት ምስጋና አቅርበው የሚከተለውን ብለዋል። “በመጀመሪያ ጥሪያችንን አክብራችሁ እዚህ ስለመጣችሁ በፌደሬሽኑ ስም አመሰግናቸዋለሁ። እኛ ውድድሩ ከመስከረም 26 – ጥቅምት 11 እንዲከናወን ባስቀመጥነው እቅድ መሰረት ስራዎችን እየሰራን ነው ነገር ግን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውድድሩን እስከ ጥቅምት 7 አጠናቁ ተብሎ ደብዳቤ ተልኳል። ይህንን ግን እኛ አንቀበለውም፤ በተቻለው መጠን ጥቅምት 11 የሚደረገውን የእኛን የፍፃሜ ጨዋታ እና የአሸናፊዎች አሸናፊን ጨዋታ ለማስተካከል እንሞክራለን።”በማለት ከብሄራዊ ፌደሬሽኑ ውድድሩን ቶሎ እንዲያጠናቅቁ ጥያቄ መቅረቡን አስረድተዋል። ፕሬዝዳንቱ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩ “በሲቲ ካፑ የሚወዳደሩት ክለቦች እንዲጎዱ እንፈልግም። ምን አልባት በአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታው የሚጫወቱት ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ በሲቲ ካፑም ፍፃሜ የሚደርሱ ከሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የአሸናፊዎች አሸናፊን ጨዋታ እንዲያራዝምልን እንጠይቃለን። ካልሆነ ግን ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም እንሞክራለን።” ብለዋል።

አንድ ሰዓት በፈጀው በዚህ ፕሮግራም ከፕሬዝዳንቱ የመክፈቻ ንግግር በኋላ የውድድሩን ደንብ አስመልክቶ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን መስተካከል አለባቸው በተባሉት የውድድሩ ደንቦች ላይም ማስተካከያዎች ተደርገው በስምምነት ታልፏል።
በደንቡ ላይ አዳዲስ ጉዳዮች መካተታቸው የተነገረ ሲሆን በተለይ አምና የተሻሻለው የክልል ክለቦች ውድድሩን ሲያሸንፉ የሚሰጣቸውን ሽልማት አስመልክቶ እንደ አምናው ክለቦቹ ዋናውን ዋንጫ እንደሚሰጣቸው ተነግሯል። ከዋንጫው ሽልማት በተጨማሪ የክልል ተጋባዥ ክለቦች እንደየ ደረጃቸው ከሚገኘው ጠቅላላ ገቢ በፐርሰንት እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።

ከዚሁ ከገንዘብ ክፍፍል ጋር በተያያዘ ከሚገኘው ጠቅላላ ገቢ 48% የሚሆነው ለክለቦቹ የሚሰጥ መሆኑ በማብራሪያ የተገለፀ ሲሆን አንደኛ የሚወጣው 15%፣ ሁለተኛ የሚወጣው 10%፣ ሶስተኛ የሚወጣው 7%፣ አራተኛ የሚወጣው 4% እንዲሁም ቀሪው በየደረጃቸው 3% ለየክለቦቹ እንደሚሰጥ ተብራርቷል።


ከደንቡ ውይይት በኋላ በቀጥታ ወደ እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት የታለፈ ሲሆን ፌደሬሽኑ ስምንቱን ክለቦች በሁለት ምድብ ከፋፍሎ እጣውን አውጥቷል።እጣው ከመውጣቱ በፊት የሁለቱም ምድቦች የቡድን አባቶች የተመረጡ ሲሆን ክለቦቹ ባላቸው የደጋፊ ብዛት ምርጫዎች ተከናውነው ኢትዮጵያ ቡና የምድብ ሀ ፋሲል ከነማ የምድብ ለ አባት ሆነው ተመርጠዋል።
በዚህም መሰረት በምድብ ሀ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ሲደለደሉ በምድብ ለ ፋሲል ከነማ፣ ወላይታ ድቻ፣ ኳራ ዩናይትድ እና ጅማ አባጅፋር ተመድበዋል። በድልድሉ መሰረት ከምድብ ሀ ቅዳሜ 8:00 መከላከያ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም 10:00 አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና እንደሚገናኙ ተገልጿል።

ከእጣ ማውጣቱ ስነ ስርዓት በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የተሰጠ ሲሆን ስለተለያዩ ጉዳዮች ማብራሪያዎች   ተሰተዋል። ስለ ስታዲየም መግቢያ በቅድሚያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ከአምናው የስታዲየም መግቢያ መጠነኛ ለውጦችን ማድረጋቸውን በማስረዳት የመግቢያ ዋጋዎቹን አሳውቀዋል። ዳፍ ትራክ እና ሚስማር ተራ 15 ብር፣ ካታንጋ 30፣ ከማን አንሼ ያለ ወንበር 50፣ ከማን አንሼ ወንበር ያለው 70፣ ጥላፎቅ 120 እንዲሁም ክቡር ትሪቡን 250 መሆኑ ተገልጿል።
ከመግቢያ ዋጋው በተጨማሪ ስለ ስታዲየም የፀጥታ ሁኔታ በተደረገው ገለፃ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፀጥታ ሃይሎች ጋር ንግግሮች እንደተደረጉ ተነግሯል። ከዚህም ጋር ተያይዞ 9 የሲሲ ቲቪ ካሜራዎችን በስታዲየሙ እንደተተከለ የተነገረ ሲሆን የፀጥታ ችግሮች ከመስፋፋታቸው አስቀድሞ ችግሮች ላይ ለመድረስ እንደተሰራ ተነግሯል።

በመጨረሻም ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድሩ አለመሳተፍ የተጠየቁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ክለቡ የሰጣቸው ምላሽ ከቡድን ስብስብ ማነስ ጋር እንደሆነ ተናግረዋል።