የክለቦች የዝውውር እንቅስቃሴ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ላይ ከወዲሁ ጠንካራ ተሳታፊ ከሆኑ ክለቦች አንዱ ሆኗል፡፡ ውላቸው ዘንድሮ የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ውለል ያደሰ ሲሆን አዳዲስ ተጫዋቾችንም ለማስፈረም ተስማምቷል፡፡

ውላቸውን ለማደስ የተስማሙ ተጫዋቾች

ደስታ ዮሐንስ

ወደ ሀዋሳ ዋናው ቡድን ካደገ ወዲህ ድንቅ አቋሙን ያሳየውና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የቡድኑ አምበል ሆኖ የተሾመው ደስታ ዮሐንስ በክለቡ ለተጨማሪ ሁለት አመታት የሚያቆየውን ስምምነት አድርጓል። ደስታ በዚህ የዝውውር መስኮት ስሙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በስፋት ሲነሳ የነበረ ተጫዋች ነው፡፡

ታፈሰ ሰለሞን

ምርጥ የውድድር ዘመን ያሳለፈው ታፈሰ ሰለሞን ከአህሊ ሸንዲ በ2007 ወደ ሀዋሳ ከተማ ከተዛወረ ወዲህ በእግርኳስ ህይወቱ የተረጋጋ መስሏል፡፡ ለቀጣዮቹ 2 አመታትም በሀዋሳ ለመቆየት ተስማምቷል፡፡ ሆኖም አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች ስሙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር ተያይዟል፡፡

ዳንኤል ደርቤ

የቡድኑ አንጋፋ ተጫዋች የሆነው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳንኤል ደርቤ በ2005 በድጋሚ ከተመለሰ በኋላ አስካሁን በቡድኑ የቆየ ሲሆን እስከ 2011 መጨረሻም በክለቡ የሚቆይ ይሆናል፡፡

አዲስአለም ተስፋዬ

ወደ ዋናው ቡድን ካደገ ወዲህ ከሀዋሳ ከተማ ውጪ የሌላ ክለብ መለያ ለብሶ የማያውቀው የመሀል ተከላካዩ አዲስአለም በቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዘመናትም በሀዋሳ ከተማ ይቆያል፡፡

ሶሆሆ ሜንሳህ

ቶጓዊው ግብ ጠባቂ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ቡድኑን በአንድ አመት ውል የተቀላቀለ ሲሆን ለተጨማሪ ሁለት አመታት በክለቡ ለመቆየት ተስማምቷል፡፡

ውላቸውን ያላደሱ ተጫዋቾች

ጋዲሳ መብራቴ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያመራ መቃረቡ የተነገረ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ቁርጡ የሚታወቅ ይሆናል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድኑን የተቀላቀለው ጃኮ አራፋትም ውሉን አጠናቆ ለሙከራ ወደ እስራኤል ያቀና ሲሆን የሙከራ ጊዜው ካልተሳካ በሀዋሳ ለመቆየት ፍላጎት እንዳለው ታውቋል፡፡

አዲስ ፈራሚዎች

ጋብሬል እና ፍቅረየሱስ

በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከቆዩ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ጋናዊው ጋብሬል አህመድ ለሀዋሳ ከተማ ለመፈረም ከተስማሙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከ2003 ጀምሮ በደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቆየው ጋብሬል ሀዋሳን መቀላቀል ከሊጉ ምርጥ የአማካይ ክፍል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማን ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሌላው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለገብ ፍቅየሱስ ተወልደብርሀን ወደ ከፍተኛ ሊግ ከወረደው ክለብ ለቆ ወደ ሀዋሳ ያመራ ሲሆን ከሁለገብ ሚናው አንፃር ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በርካታ አማራጭ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወንድይፍራው ፣ ሳዲቅ እና ያቡን ዊልያም

በኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት ያሳለፉት ወንድይፍራው ጌታሁን ፣ ሳዲቅ ሴቾ እና ያቡን ዊልያም ውላቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርተዋል፡፡ ወንድይፍራው ከኤኮ ፌቨር ጋር በመፈራረቅ በርካታ የቡና ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን በግርማ በቀለ እና ሙጂብ ቃሲም መልቀቅ የሳሳውን የተከላካይ መስመር ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሳዲቅ እና ዊልያም ዘንድሮ በኢትዮጵያ ቡና ብዙም የመሰለፍ እድል ያላገኙ ሲሆን በሀዋሳም በቋሚነት ለመሰለፍ ከባድ ፉክክር ይገጥማቸዋል፡፡

ተክለማርያም ሻንቆ

ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በሶስት የተለያዩ የሊግ እርከኖች ያሳለፈው ተክለማርያም ሻንቆ ከፕሪምየር ሊጉ ከወረደው አአ ከተማ ጋር ያለውን ኮንትራት ማጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ መጓዝን ምርጫው አድርጓል፡፡ ተክለማርያም በሀዋሳ ቋሚ ለመሆን ውሉን ካደሰው ሶሆሆ ሜንሳህ ጋር መፎካከር ይጠበቅበታል፡፡

የሚያድጉ ተጫዋቾች

ባለፉት አመታት ከተስፋ ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን የማሳደግ ልምድ ያለው ሀዋሳ ከተማ በወጣቶች እግርኳስ ላይ የበላይነታቸውን ካሳዩት የ20 አመት እና 17 አመት በታች ቡድኖቹ 5 ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን እንደሚያሳድግ ታውቋል፡፡

የሚለቁ እና ከክለቡ ጋር ድርድር ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች

በዘንድሮው አመት ውላቸውን የሚያጠናቀቁ ተጫዋቾችን ጨምሮ ሀዋሳ 5 ተጫዋቾችን እንደሚያሰናብት የታወቀ ሲሆን የመከላከያው አዲሱ ተስፋዬ እና የኤሌክትሪኩ አሸናፊ ሽብሩ ከክለቡ ጋር ስማቸው የተያያዙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሐምሌ 25 በሚከፈተው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮትም ተጨማሪ የውጪ ተጫዋቾች ሊያስፈርም እንደሚችል ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *