የፕሪምየር ሊጉ የ2010 የውድድር ዘመን መቼ እንደሚጀምር ታወቀ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 2010 እንደሚጀመር ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት አመታት ሊጉ የመንግስት የሚጀመርበትን ቀን ዘግይቶ የማሳወቅ ልምድ የነበረው ሲሆን ክለቦችም ቀድሞ መርሀ ግብሩ የሚጀመርበት ቀን እንዲነገራቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡ ፌዴሬሽኑም በዚህ ምክንያት የውድድሩን መጀመርያ ቀን እንደቆረጠ ተነግሯል፡፡

ሊጉ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ካልተራዘመ በቀር ጥቅምት 4 እንዲጀመር የወሰነ ሲሆን በመስከረም ወር ደግሞ የ2009 የውድድር ዘመን አፈጻጸም ሪፖርት እና የእጣ ማውጣት ይደረጋል፡፡ በእጣ ማውጣቱ ጥያቄ እንዳያስነሳ በሚልም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ የአካሄድ ለውጥ እንደሚኖር ታውቋል፡፡

ከአዲሱ የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጀመር 1 ሳምንት ቀደም ብሎ መስከረም 25 እና 28 በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *