​ኢትየጵያ ቡና ሶስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በዘንድሮው የክረምት የዝውውር መስኮት የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች በሌሎች ክለቦች እየተነጠቀ የሚገኘው ኢትዮጵያ በውድድር ዘመኑ መጠናቀቂያ ላይ ዳግም ለሁለተኛ ጊዜ ቡድኑን ለማሰልጠን በተስማሙት ሰርቢያዊዉ አንጋፋ አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች እየተመሩ ቡድናቸው እንደአዲስ በማዋቀር ላይ ይገኛሉ፡፡

በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሁለቱ የመስመር ተከላዮች አብዱልከሪም መሀመድ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም አህመድ ረሺድን ወደ ድሬዳዋ ከተማ  ካመሩ በኃላ ክለቡ ይህንን ክፍተት ለመድፈን አለማየሁ ሙለታን ከአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ቶማስ ስምረቱን ከወላይታ ድቻ ማስፈረማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ አለማየሁ ሙለታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ካደገበት የውድድር ዘመን አንስቶ በዋና ቡድኑ ውስጥ ወጣ ገባ እያለ በመሰለፍ ለቡድኑ በቀኝና በግራ የተከላካይ ስፍራ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል፡፡ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ጅማሮ ከሊጉ በጊዜ የተሰናበተውን አዲስ አበባ ከተማን መቀላቀል ቢችልም በክለቡ ተጫዋቾችን እያፈራረቁ የመጠቀም አካሄድ ምክንያት እምብዛም ስኬታማ የሆነ የውድድር ዘመንን ማሳለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡

ሌላኛው በተከላካይ ስፍራ ላይ ቡድኑን የተቀላቀለው ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ሱሉልታ ከተማን ለቆ ወላይታ ድቻን ከተቀላቀለ በኃላ በመጀመሪያ የውድድር ዘመን ድንቅ ጊዜያትን ማሳለፍ ቢችልም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከጉዳት ጋር በተያያዘ እምብዛም ቡድኑን ማገልገል ሳይችል ቀርቷል፡፡ ነገርግን በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪው ወላይታ ድቻ የሶስት የመሀል ተከላካይ ጥምረት ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት ችሏል፡፡

ሌላው በክረምቱ ኢትዮጵያ ቡና የተቀላቀለው የወላይታ ድቻው ግብጠባቂ ወንደሰን አሸናፊ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በወላይታ ድቻ በተለይ በመጀመሪያው የውድድር አመት በ8 ጨዋታዎች ላይ ግቡን ሳያስደፍር ስኬታማ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል፡፡ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ ግብ ጠባቂ ወንደሰን አሸናፊ ክለቡን ለቆ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያመራው ዮሀንስ በዛብህ በመተካት የቤኒናዊው ግብጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ ተተኪ በመሆን በክለቡ ቆይታ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

እስካሁን ድረስ በክለቡ ይፋ በተደረገው መሠረት ቤኒናዊዉ ግብጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ ለተጨማሪ ሁለት አመታት በክለቡ የሚያቆየው አዲስ ውል የተፈራረመ ሲሆን ሌሎች ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር እየተደራደሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ቡድኑ የተከላካይ መስመሩን ለማጠናከር በማሰብ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከዳሽን ቢራ ወደ ፋሲል ከተማ ከተቀላለበት ጊዜ አንስቶ በግራ ተከላካይ መስመር እጅግ ድንቅ የሆነ አመትን ያሳለፈውን አምሳሉ ጥላሁን ወደ ቡድናቸው ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ሲሆን ተጫዋቹን ለማስፈረም የመጨረሻው ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን የሶከር ኢትዮጵያ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

በሌላ ዜና ሠርቢያዊው አሰልጣኝ ከቡድኑ የእድሜ እርከን ቡድኖች ያድጋሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች በተጨማሪ ከከፍተኛ ሊግ እና የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድርን ለመከታተል ድሬዳዋ የሚገኙት አሰልጣኙ በቀጣይ ቀናት ከነዚህ ውድድሮች ላይ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን እንደአዲስ ለመገንባት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *