ወላይታ ድቻ ሶስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት በሜዳው ደደቢትን 4-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠውና የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን በመሆን በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአፍሪካ ኮፌድሬሽን ካፕ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው ወላይታ ድቻ የክለቡን ለማጠናከር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በቀጣይ የውድድር ዘመን በሊጉም ሆነ በኮፌደሬሽን ዋንጫ ጠንካራ ተፍካካሪ ለመሆን ተጫዋቾች ማስፈረም መጀመሩን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ለወላይቻ ድቻ በ2005 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲያድግ እንዲሁም በቀጣዩ አመት በሊጉ አስገራሚ ግስጋሴን ሲያደርግ በክለቡ ቁልፍ ሚና የነበረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ እሸቱ መና እምብዛም ውጤታማ ካልነበረ የሁለት አመታት የአዳማ ከተማ ቆይታ በኃላ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል፡፡

በተጨማሪም በሀዋሳ ከተማ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ ለ5 አመታት ቆይታ ያደረገው የግራ መስመር ተከላካዩ ተስፋ ኤልያስም ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት ለድቻ ለመጫወት ተስማምቷል፡፡ ተስፋ በግራ መስመር ተከላካይነትም ሆነ አማካይነት መጫወት የሚልችል በመሆኑ ቡድኑን የለቀቀው ፈቱዲን ጀማልን ክፍተት ለመድፈን ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሌላኛው ለወላይታ ድቻ ለመጫወት የተስማማው የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረው ኃይማኖት ወርቁ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት አመታት ለሀዋሳ ከተማ መጫወት የቻለው ኃይማኖት ከሀዋሳ ከተማ ጋር የነበረው የውል ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ስሙ በስፋት ከፋሲል ከተማ ጋር ሲያያዝ ቢቆይም በስተመጨረሻም ወላይታ ድቻን ተቀላቅሏል፡፡

በተያያዘም ክለቡን ለቆ ወደ ድሬዳዋ ከተማ እንዳመራ ሲነገር የነበረው ተከላካዩ አናጋው ባደግ ከክለቡ ጋር የሚያቆየውን ውል ሊፈርም እንደሚችል ታውቋል፡፡

ክለቡ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብጠባቂ የነበረውን ናይጄሪያዊውን ግብጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮን እንዲሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ እምብዛም ስኬታማ የውድድር ዘመን ያላሳለፈው አሳልፈው መኮንን ከማስፍረሙ በተጨማሪ ወደ አራት የሚጠጉ ተጫዋቾችን ከተስፋ ቡድኑ ወደ ዋናው እንደሚያሳድግ ይጠበቃል፡፡

በቀጣይ አመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ መድረክ ተካፋይ ወላይታ ድቻ ተጫዋቾች የነበሩት ግብጠባቂው ወንድወሠን አሸናፊ እና ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ክለቡን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሲያመሩ በተመሳሳይ የተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ወደ ሲዳማ ቡና እንዲሁም አጥቂው አላዛር ፋሲካ ወደ አዳማ ከተማ ማቅናታቸው ተረጋግጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *