አንደኛ ሊግ | ደሴ ከተማ እና ሀምበሪቾ ለፍጻሜ ደረሱ

የኢትዮዽያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ደሴ ከተማ እና ሀምበሪቾ ተጋጣሚያቸውን በማሸነፍ ለፍፃሜ ደርሰዋል፡፡
08:00 ላይ የተጫወቱት ደሴ ከተማ እና መቂ ከተማ ሲሆኑ በጨዋታ መደበኛ ክፍለ ጊዜ 2-2 ተጠናቆ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶች ደሴ ከተማ 4-2 በማሸነፍ ለፍፃሜው ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል።
በምድብ ሀ ሁለቱንም ጨዋታ ከጥሩ ብቃት ጋር በማሸነፍ ስድስት ነጥብ ይዞ አንደኛ በመሆን ለዛሬው ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ያለፈው መቂ ከተማ ዛሬም ያንኑ ጥንካሬ በመድገም በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቀሴ እና የጎል ሙከራ በማድረግ የተሻለ የነበረ ሲሆን በተለይም ተመስገን ባይሳ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምባት ቀርቷል። ደሴዎች በበኩላቸው በእዮብ ካህሳይ የግል ጥረት ታግዘው የግብ እድል ለመፍጠር ችለው ነበር፡፡


በውድድሩ ላይ ጥሩ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች መሆኑን ያሳየው ዝነኛው ጋዲሳ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኄኖክ ሙልጌታ ወደ ጎልነት በመቀየር መቂን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ ። የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ደሴዎችን አቻ ማድረግ የሚችል የጎል አጋጣሚ ተስፋ ወሰን ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጭ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽም በመቂ 1-0 መሪነት ነበር የተጠናቀቀው፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ደሴዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል እድል ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ባለበት ሰአት የደሴ ግብ ጠባቂ ስህተትን ተጠቅመው መቂዎች ተቀይሮ በገባው በላይ ያደሳ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ ደሴዎች ያደረጉት የተጨዋች ቅያሪ ሰምሮላቸው የጨዋታው ኮከብ በሆነው ሐብታሙ ገብሬ አከታትሎ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል፡፡


መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2-2 በመጠናቀቁ ወደ ፍፃሜ አላፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ደሴ ከተማ 4-2 አሸንፎ ለመሸነፍ ተቃርቦ የነበረውን ጨዋታ በድል በመወጣት ለፍፃሜው አላፊ መሆን ችሏል ።
10:00 ላይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ሁለተኛ ጨዋታ ሀምበሪቾ የካ ክፍለከተማን 2-0 በማሸነፍ ሌላኛው የፍፃሜ ተፋላሚ መሆን ችሏል። በውድድሩ ደካማ አቋም ያሳየው የካ እና ጠንካራውን ሀምበሪቾ ባገናኘው ጨዋታ የካዎች የተሻለ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ሀምበሪቾዎች በምድባቸው ካከናወኑት ሁለቱ ጨዋታ አቋሟቸው ወርዶ ታይቷል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽም የረባ የጎል ሙከራ እና ሳቢ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳይታይበት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።
ከእረፍት መልስም እንደመጀመርያው ሁሉ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም የተሻለ ነገር ያልታየበት ጨዋታ ነበር።
በአንፃራዊነት ወደ ጎል በመድረስ ከየካዎች ተሽለው የነበሩት ሀምበሪቾዎች መሳይ መላኩ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘውን ፍ/ቅ/ምት በሚሊዮን ሰለሞን አማካኘነት አስቆጥረዋል፡፡
ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ የካዎች ተጭነው ቢጫወቱም ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አላዛር አድማሱ በመጨረሻው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ ሀምበሪቾ 2-0 በማሸነፍ እሁድ ለሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ አላፊ መሆን ችሏል ።
የኢትዮዽያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር እሁድ ፍፃሜውን ሲያገኝ 08:00 ላይ መቂ ከ የካ ክፍለከተማ ለደረጃ ፤ 10:00 ላይ ደግሞ ሀምበሪቾ ከ ደሴ ከተማ ለፍፃሜ ዋንጫ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *