​ጅማ አባ ቡና ግርማ ሐብተዮሀንስን የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር የተለያየው ጅማ አባ ቡና ግርማ ሐብተዮሀንስን ቀጣዩ የክኩቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡

አሰልጣኝ ግርማ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድንን በማጣርያ ጨዋታዎች ከመሩ በኋላ ከስራ ርቀው ከሰነበቱ በኋላ ያለፉትን 6 ወራት በሰበታ ከተማ ያሳለፉ ሲሆን በዛሬው እለት ከክለቡ ቦርድ ጋር ያደረጉትን ድርድር በስምምነት አጠናቀው ለአንድ አመት የክለቡ አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡

የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ አሰልጣኝ በወጣት ተጫዋቾች ቡድን በመገንባት የሚታወቁ ሲሆን ሙገር ሲሚንቶ በ2007 ከሊጉ እስኪወርድ ድረስ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ችለው ነበር፡፡

ከጅማ አባቡና ጋር በተያያዘ ዜና ክለቡ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያስገባው ክስ ምላሽ አገኘም አላገኘም ህልውናው የሚቀጥል መሆኑን ክለቡ ማረጋገጫ የሰጠ ሲሆን ክሱ ተገቢውን ምላሽ እስኪያገኝ ግን ጥረቱን እንደማያቋርጥ እና ጉዳዩን እስከሚመለከቱ አለምአቀፍ የእግርኳስ አካላት ድረስ ይዞ እንደሚጓዝ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ዙርያ በአሁኑ ሰአት ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም ውሳኔው በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ይደረጋል ተብሏል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *