ዛምቢያ፣ ጋቦን እና ኬፕ ቨርድ ያልተጠበቁ አሸናፊዎች ሆነዋል

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉት ወሳኝ ጨዋታዎች ማክሰኞም ተካሂደዋል፡፡ ዛምቢያ የአልጄሪያ በሜዳዋ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የ26 ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዞን ስትገታ በ10 ተጫዋች የተጫወተችው ጋቦን ከሜዳዋ ውጪ ኮትዲቯርን ረታለች፡፡ ኬፕ ቨርድ በቀናት ልዩነት ከደቡብ አፍሪካ ላይ ስድስት ወሳኝ ነጥቦችን ሰብስባ የማጣሪያ ጉዟዋን ስታስተካክል ግብፅ የምድብ መሪነቷን ከዩጋንዳ ተቀብላለች፡፡ ጋና ኮንጎ ብራዛቪል ላይ የግብ ናዳ ስታወርድ ጠንካራ ፉክክር በተሰተናገደባቸው ጨዋታዎች ቡርኪና ፋሶ ከሴኔጋል እንዲሁም ዲ.ሪ. ኮንጎ ከቱኒዚያ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በምድብ አንድ ቱኒዚያ በሁለተኛው 45 በደቂቃ ልዩነት አከታትላ ያስቆረቻቸው ሁለት ግቦች ከኪንሻሳ ወሳኝ ነጥብ ይዞ እንድትመለስ አስችሏታል፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ቱኒዚያ 2 አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ኮንጎ እስከ77ኛው ደቂቃ 2-0 መምራት ችላ ነበር፡፡ ቻንስል ምቤምባ እና ፖል ሆዜ ፖኩ ለኮንጎ ሲያስቆጥሩ ዊልፍሬድ ሞክ በራሱ ግብ ላይ እና የኤስፔራንሱ አኒስ ባድሪ ለቱኒዚያ ወሳኝ ነጥብን አስገኝተዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ በምድቡ የሚገኙት ጊኒ እና ሊቢያ ከማጣሪያው ውጪ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ምድቡን ቱኒዚያ በ10 ነጥብ ስትመራ ኮንጎ በ7 ትከተላለች፡፡

 

በምድብ ሁለት ዛምቢያ ከሜዳዋ ውጪ አልጄሪያን በመርታት ከናይጄሪያ ጋር የነበራትን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ አጥብባለች፡፡ ኮንስታንታይን ላይ በተደረገው ጨዋታ አልጄሪያ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ በሜዳዋ ከ2007 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ተሸንፋለች፡፡ ፓስተን ዳካ በ67ኛው ደቂቃ የቺፖሎፖሎዎቹን የድል ግብ አስገኝቷል፡፡ ዳካ የዛምቢያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አባል የነበረ ተስፈኛ የፊት መስመር ተጫዋች ነው፡፡ በጨዋታው ሪያድ ማህሬዝ የፍፁም ቅጣት ምት አምክኗል፡፡ በ2007 በጊኒ 2-0 ከተሸነፈች በኃላ በሜዳዋ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተሸንፋ የማታውቀው አልጄሪያ ከማጣሪያው ውጪ መሆኗንም አረጋግጣለች፡፡ ምድቡን ናይጄሪያ በ10 ነጥብ ስትመራ በ3 የምታንሰው ዛምቢያ ሁለተኛ ነች፡፡

በምድብ ሶስት ማክስኞ የተመዘገቡት ውጤቶች ተከትሎ በመሪዎቹ መካከል ያለው መቀራረብ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎችም ከባድ ፉክክር እንደሚስተናግድባቸው ይጠበቃል፡፡ ሊበርቪል ላይ ከቀናት በፊት በኮትዲቯር 3-0 የተሸነፈችው ጋቦን ከሜዳዋ ውጨ ኮትዲቯርን በ10 ተጫዋች 2-1 አሸንፋለች፡፡ አክል ሚዬ እና ማርዮ ለሚና ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ጋቦን 2-0 ስትመራ በመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሎይድ ፓሉን በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ማክስዌል ኮርኔ ለዝሆኖቹ ልዩነቱን ያጠበበትን ግብ በ58ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡ ኮትዲቯር በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም ተጨማሪ ግብን ለማስቆጠር አልቻሉም፡፡

ባማኮ ላይ ማሊ ሞሮኮን ነጥብ አስጥላለች፡፡ ያለግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ የማሊው ግብ ጠባቂ ጂጉዊ ዲያራ ጥሩ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ዲያራ በሁለተኛው አጋማሽ የአትላስ አንበሶቹ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምትንም መመልስ ችሏል፡፡ ከቀናት በፊት ሞሮኮ ማሊን 6-0 ስትረታ ኮከብ የነበረው ሃኪል ዚየች የፍፁም ቅጣት ምት አምክኗል፡፡ ሞሮኮ የምድቡን መሪነት መረከብ የምትችልበትን እድል አምክናለች፡፡ ምድቡን ኮትዲቯር በ7 ነጥብ ስትመራ ሞሮኮ በ6 እንዲሁም ጋቦን በ5 ነጥብ ይከተላሉ፡፡ ማሊ በ2 ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች፡፡

 

በምድብ አራት ኬፕ ቨርድ ደቡብ አፍሪካን 2-1 ስታሸንፍ ቡርኪና ፋሶ እና ሴኔጋል 2 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ደርበን ላይ ኬፕ ቨርድ ደቡብ አፍሪካ በጋሪ ሮድሪጌዝ ሁለት ግቦች አሸንፋለች፡፡ አንዲል ጃሊ ባፋና ባፋናን ከባዶ መሸነፍ ያዳነች ግብ በ89ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡
ኢሱፉ ዳዮ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመጀመሪያው አጋማሽ በተሰናበተበት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ በ10 ተጫዋች የተጫወተችው ቡርኪናፋሶ ከሴኔጋል ጋር ነጥብ ተጋርታለች፡፡ በርትራንድ ትራኦሬ ለቡርኪናፋሶ እንዲሁም ኢስማኤላ ሳር ለሴኔጋል ባስቆጠሯቸው ግቦች ቡድኖቹ 1 አቻ የመጀመሪያ አጋማሽን ጨርሰዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ሳድዮ ማኔ የቴራንጋ አንበሶቹን ቀዳሚ ሲያደርግ ፓፔ ሰይዱ ንዳዬ በራሱ ግብ ላይ በ88ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ቡርኪና ፋሶ ነጥብ ተጋርታለች፡፡ ምድቡን ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርድ በእኩል 6 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሲመሩት ሴኔጋል በ5 እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በ4 ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በምድብ አምስት ግብፅ ዩጋንዳን 1-0 በማሸነፍ የምድብ መሪነቷን ስትይዝ ጋና ኮንጎ ብራዛቪልን 5-1 አሸንፋለች፡፡ አሌክሳንደሪያ ላይ ግብፅ በመሃመድ ሳላህ ብቸኛ ግብ ዩጋንዳን 1-0 አሸንፋለች፡፡ በጨዋታው ዴኒስ ኦኒያንጎ ያለቀላቸው የግብ እድሎች በማምከን አሁንም በአፍሪካ ምርጥ ግብ ጠባቂነቱን አስመክሯል፡፡ ክሬንሶቹ በጨዋታው ጥሩ ቢንቀሳቀሱም ግብ ሊያስቆጥሩ አልቻሉም፡፡
ጋናን በቶማስ ፓርቴ ሃት-ትሪክ እና በሬችመንድ ቦአኬ ሁለት ግቦች ኮንጎን 5-1 አሸንፋለች፡፡ የኮንጎን ማስተዛዘኛ ግብ ኤመርሰን አዬት በመጀመሪያው አጋማሽ አስገኝቷል፡፡ ምድቡን ግብፅ በ9 ነጥብ ስትመራ ዩጋንዳ በ7 እንዲሁም ጋና በ5 ትከተላለች፡፡ ግርጌ ላይ የምትገኘው ኮንጎ ከማጣሪያው ተሰናብታለች፡፡

ውጤቶች

ካሜሮን 1-1 ናይጄሪያ
ሊቢያ 1-0 ጊኒ
ኮንጎ ሪፐብሊክ 1-5 ጋና
ኮትዲቯር 1-2 ጋቦን
ቡርኪና ፋሶ 2-2 ሴኔጋል
ዲ.ሪ. ኮንጎ 2-2 ቱኒዚያ
ማሊ 0-0 ሞሮኮ
ደቡብ አፍሪካ 1-2 ኬፕ ቨርድ
ግብፅ 1-0 ዩጋንዳ
አልጄሪያ 0-1 ዛምቢያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *