​ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ሲዳማ ቡና 

በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ያጣው ሲዳማ ቡና በሀዋሳ ከተማ ፓራዳይዝ ሆቴል መቀመጫውን አድርጎ የአዲሱ የውድድር ዘመን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ከቅርብ አመታት ጀምሮ በሊጉ መልካም የሚባል የውድድር አመት ያሳለፉ  ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን በመገንባት ጥንካሬውን እያሳየ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በ2009 የውድድር አመት ለቡድኑ ውጤት ማማር ትልቁን ሚና የተወጡ ሰባት ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቹን ማጣቱ በዘንድሮ የውድድር አመት ሊቸገር እንደሚችል የብዙ የስፖርት ቤተሰብ ግምት ሆኗል ።

ሲዳማ ቡና በ2009 የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አመት ከ30 ጨዋታ 13 ሲያሸንፍ 7 ተሸንፎ 10 ጨዋታን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ 30 ጎል አስቆጥሮ 22 ጎል ተቆጥሮበት በ49 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ስኬታማ የውድድር አመት አሳልፎ እንደነበረ ይታወቃል ።
በሲዳማ ቡና ውስጥ ዘንድሮ የማንመለከታቸው ተጨዋቾች ለዐለም ብርሃኑ ፣ ወሰኑ ማአዜ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ሙሉአለም መስፍን ፣ ሰንደይ ሙትኩ ፣ ላኪ ሳኒ ፣ ኤሪክ ሙራንዳ ፣ በረከት አዲሱ ( በቅጣት) ናቸው ።


ሲዳማ ቡና በለቀቁበት ተጨዋቾች ምትክ ክለቡን ለማጠናከር ከሀገር ውስጥም ከውጭ በርከት ያሉ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ አምጥቷል። በዘንድሮ አመት በሲዳማ ቡና መለያ የምንመለከታቸው አዲስ ፈራሚዎች ፈቱዲን ጀማል ( ተከላካይ/ወላይታ ድቻ) ፣ ሐብታሙ ገዛኸኝ ( አጥቂ/ ደቡብ ፖሊስ) ፣ ወንድሜነህ አይናለም ( አማካይ/ሀዋሳ ከተማ) ፣ አምሀ በለጠ (አማካይ/ድሬዳዋ ከተማ) ፣ ባዬ ገዛኸኝ ( አጥቂ/መከላከያ) ሲሆኑ ምስጋናው ወ/ዮሐንስ ከሲዳማ ቡና ጋር በዝግጅት ወቅት አብሮ እየሰራ ቢገኝም እስካሁን ፊርማውን አለማኖሩን ለማወቅ ችለናል።

ባለፉት ጊዜያት በአንጻራዊነት የተሳኩ የውጭ ተጫዋቾች ዝውውር ያካሄደው ሲዳማ ቡና አራት ተጨዋቾችን አስፈርሟል፡፡ መሐመድ አብዱለቲፍ ( አጥቂ/ጋና) ፣ ኮናቴ ማማዱ ቢን ኢሱን ( አማካይ/ኮትዲቯር) ፣ ኬኔዲ አሺያ ( ተከላካይ/ጋና) እና ሚካኤል አናአን ( አጥቂ/ጋና) የረሙት ተጫዋቾች ናቸው።
ሲዳማ ቡና በ2009 የውድድር አመት ከ17 እና ከ20 አመት በታች ቡድኑ በሊጉ ላይ ተሳታፊ ያልነበረ ቢሆንም ቀድሞ ከነበረው ታዳጊ ቡድኑ አምስት ተጨዋቾችን ወደ አሳድጎ የሙከራ ጊዜ እየሰጠ ይገኛል፡፡ እነሱም አዲስ ተሰፋዬ (አምና ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት ተጫውቷል) ፣ ሚካኤል ሀዲሽ ፣ ለይኩን ነጋሽ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና አባይነህ አመሉ ናቸው ።


ሲዳማዎች በምክትል አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ እየተመሩ በሀዋሳ ከተማ መቀጫቸውን በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዳቸውን በተሳካ ሁኔታ እያደረጉ ሲገኝ አዲስ ግደይ እና ፍፁም ተፈሪ በግል ጉዳይ ምክንያት በዝግጅቱ ላይ ያልተመለከትናቸው ተጨዋች ናቸው። የተቀሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ግን በዝግጅት ላይ ተገኝተዋል።
በቡድኑ ወቅታዊ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በተመለከተ ከምክትል አሰልጣኝ ዘራይ ጋር ባደረግነው ቆይታ እንደተናገሩት ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በመልቀቁ እንደማይቸገር ገልጸዋል፡፡ ” አዲስ ያስፈረምናቸው እና ከታች ያሳደግናቸውን ጨምሮ ዝግጅታቸውን ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በቀን ሁለት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የለቀቅናቸው ተጫዋቾችም ይሄን ያህል ተፅዕኖ አያደርጉብንም፡፡ ከወጡት ሰባት ተጨዋቾች አራቱ ብቻ ነበሩ ወሳኝ ተጨዋቾች፡፡ ያም ቢሆን እነሱን የሚተኩ አቅም ያላቸው ተጨዋቾች ከሀገር ውስጥም ከውጭ በማስመጣት ቡድኑን እንደ አዲስ እየገነባን ስለሆነ ይሄን ያህል በቡድን ውስጥ የሚፈጥረው ስጋት የለም፡፡ አዲስ ያመጣናቸው ተጨዋቾች በዝግጅት ወቅት እንዳየናቸው ከሆነ በሚገባ የእነሱን ቦታ መሸፈን የሚችሉ በመሆኑ የሚያሰጋን ነገር የለም፡፡ ” ብለዋል፡፡


አሰልጣኝ ዘርአይ የቡድናቸው ያለፈው አመት ችግርን ማሻሻል ላይ አተኩረው ዝግጅታቸውን እያከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡  ” አምና ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን ነበረን፡፡ ወደ ዋንጫው ፉክክርም መግባት ችለን ነበር፡፡ ሆኖም እንደ ድክመት ያየነው በተለይ ወደ መጨረሻዎቹ ሳምንታት ሁነኛ ጨራሽ አጥቂ አልነበረንም፡፡ ይሄ ደግሞ በቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ስለፈጠረ ዘንድሮ በሀገራችን አለ የሚባል አጥቂ ባዬ ገዛኸኝን አስፈርመናል፡፡ ከውጭ ያመጣናቸውም ጥሩ ያደርጋሉ ብለን እናስባለን፡፡ ” በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።
ይህን ዝግጅት ባጠናከርንበት ወቅት ለስልጠና ወደ ሞሮኮ በመሄዳቸው ምክንያት ያልነበሩት የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ  ስልጠናቸውን አጠናቀው መመለሳቸውን ተከትሎ ከነገ ጀምሮ  ወደ ስራቸው እንደሚመለሱ ሰምተናል።

ሲዳማ ቡና በቀጥታ ወደ ውድድር ከመግባቱ አስቀድሞ መስከረም 13 በሚጀምረው የደቡብ ካስትል ካፕ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ሲዳማ ያለፈው አመት የውድድሩ አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *