​የስፔኑ ሶክስና የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚን ለማስተዳደር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ውል ፈፀመ

በመጋቢት 2009 የተመረቀው የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚን እንዲያስተዳድሩለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የእግርኳስ አካዳሚዎችን ካወዳደረ በኃላ ከስፔኑ ሶክስና የእግርኳስ ማህበር ጋር ዛሬ በሸራተን አዲስ የመግባቢያ ሰነድ ውል ተፈራርሟል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሶክስና የአምስት ዓመት ውል የሰጠ ሲሆን 50 ለሚሆኑ ታዳጊዎች ስልጠናውን በመስጠት ማዕከሉ ወደ ስራ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን፣ ሶክስና እና ኢ ፎር ኢ የተባለ የስፔን ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያማክር ድርጅት የመግባቢያ ሰነዱን ዛሬ ፈርመዋል፡፡ በፊርማው ስነ-ስርዓት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገብረመስቀል እንደተናገሩት የእግርኳስ አካዳሚ መገንባት የክለባቸው የረጅም ግዜ ምኞት እንደነበር ገልፀዋል፡፡ “ ለኢትዮጵያው ቀደምት ክለብ የወጣቶች አካዳሚ መገንባት ሁሌም ህልማችን ነበር፡፡ ይህ ምሽት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪካዊ ነው፡፡ ምክንያቱም አካዳሚያችንን ሶክስና እንዲያስተዳድረው የተስማማንበት እለት ስለሆነ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ወሳኝ የሆነ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በስፔን እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነትም የሚያስቀጥል ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የሶክስና የእግርኳስ ማዕከል ምክትል ፕሬዝደንት ዴቪድ ሎፔዝ በበኩላቸው ውሉ የተሳካ እንዲሆን ያስቻሏቸውን አካላት አመስግነዋል፡፡ “በዚህ ጥሩ ግዜ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሶክስና የእግርኳስ አስተዳደር ድርጅት ነው፡፡ በስፔን፣ ቻይና እና ሆንግ ኮንግ ቢሮዎች ያሉን ሲሆን አሁን በቅርቡ በኢትዮጵያም ይኖረናል፡፡ ድርጅታችን በታዳጊዎች ስልጠና ፕሮግራሞች ላይ በልዩነት የሚሰራ ነው፡፡ ለእኛ በኢትዮጵያው ምርጥ ክለብ እንዲሁም በአፍሪካ ከምርጥ ክለቦች ተርታ በሚመደበው ቅዱስ ጊዮርጊስ መመረጥ መቻላችን ትልቅ ክብር ነው፡፡ የዚህ አስገራሚ ፕሮጀክት አካል እንድንሆን ያስቻሉንን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ተስጥኦ ሁሉም ቦታ አለ፤ በኢትዮጵያም ተፈልጎ ለመገኘት የሚገባው ብዙ ተስጥኦ እንዳለ እናምናለን፡፡ የእኛም የመጀመሪያ ስራ እነኚህን ተስጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች ጋር በመሆን የመለየት ስራ ነው፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አካዳሚ የሚሆን የአምስት አመት ስትራቴጂም የምንቀርፅ ነው የሚሆነው፡፡”

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሶክስና እንዲገናኙ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው የስፔኑ ኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅት የሆነው ኢ ፎር ኢ ሲሆን የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሁሊዮ ፓዞ  በንግግራቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለታዳጊዎች ስልጠና የሚረዳውን አጋር ድርጅት ይፈልግ እንደነበረ ጠቁመው ሶክስና ለዚሁ ብቁ ሆኖ በመገኘቱ ይህ ውል ሊፈፀም እንደቻለ አስረድትዋል፡፡

በማድሪድ የእግርኳስ ማዕከል ያለው ሶክስና በቻይና የጉዋንዡ ኤቨርንግራንዴ ክለብን አካዳሚን ማስተዳደር ሲችል በአፍሪካ የታዳጊዎች ስልጠና ፕሮግራም ላይ ሲሳተፍ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ ለ50 ታዳጊዎች ስልጠናው የሚሰጥ ሲሆን በመጀመሪያው አመት 359ሺ ዩሮ ወጪ ይደረጋል፡፡ በሁለተኛው አመት ወጪው ጨምሮ 679ሺ ዩሮ የሚሆን ሲሆን እንደአካዳሚው የቅበላ አቅም ወጪው እየጨመረ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡ ከአምስት አመት በኃላ የእውቀት ሽግግር ተደርጎ ኢትዮጵዊያን ባለሙያዎች አካዳሚውን እንዲመሩ እንደሚፈልግ አቶ አብነት ተናግረዋል፡፡ በአካዳሚው እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ቡድን መካከል ስለሚኖረው ግንኙት የሶክስና እና የስፖርት ማህበሩ ውይይት እንደሚያደርጉ ሎፔዝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

(ከሶክስና ምክትል ፕሬዝደንት ዴቪድ ሎፔዝ እና ኢ ፎር ኢ ዋና ስራ አስኪያጅ ሁሊዮ ፓዞ ለጋዜጠኞች ስለውሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች የሰጡትን ሰፋ ያለ አስተያየት አርብ ይዘን እንመለሳለን፡፡)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *