ኢትዮጵያውያን በውጪ: አለማየሁን ተዋወቁት

በበርካታ ሃገራት ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በትልቅ ደረጃ እግርኳስን ሲጫወቱ መመልከት እየተለመደ ነው፡፡ በዛሬው መሰናዷችንም በዴንማርኩ ታላቅ ክለብ ብሮንቢ ወጣት ቡድን እየተጫወተ የሚገኝ ትውልደ ኢትዮጵያዊን እናስተዋውቃችሁ፡፡   

በሙሉ ስሙ ሉዊስ አለማየሁ ቡሽ-ዊኪ ይባላል፡፡ የተወለደበትን ከተማ እና ወላጆቹን የማያውቅ ሲሆን ከተወለደ በኃላ በገበያ ቦታ ተጥሎ በፖሊስ ተገኝቶ ለማዘር ቴሬሳ የህፃናት ማሳደጊያ መሰጠቱን ያስረዳል፡፡ ዴንማርካዊያኑ የቡሽ-ዊኪ ቤተሰብም ከህፃናት ማሳደጊያው በጉዲፈቻ ወስደውት በቤልጅየም እና ዴንማርክ ነው ያደገው፡፡

ለዴንማርኩ ብሮንቢ ክለብ ከ19 ዓመት በታች ቡድን የሚጫወተው አለማየሁ ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦቹ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 8 ቀን 1992 ነበር የተወለደው፡፡ በ16 ወሩም (ግንቦት 18/1993) ለቡሽ-ዊኪ ቤተሰብ በጉዲፈቻ ተሰጥቷል፡፡ አለማየሁ ስለትውልድ እና እድገቱ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ያስረዳል፡፡ “በተወለድኩ በ16 ወሬ ነበር በጉዲፈቻነት ለአሳዳጊዎቼ የተሰጠሁት፡፡ በማደጎ የተወሰድኩት ከአዲስ አበባ ሲሆን ቀጥታ ወደ ዴንማርክ መዲና ኮፐንሃገን ነበር ከቤተሰቦቼ ጋር ያመራሁት፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ዓመታት የኖርኩት በብራስልስ ቤልጂየም ነበር፡፡ ከሶስት ዓመታት የብራስልስ ቆይታ በኃላ ቤተሰቦቼ ተመልሰው ወደ ኮፐንሃገን መኖርን መምረጣቸው ተከትሎ ሙሉ የልጅነት ጊዜውን (ከ4 ዓመቴ ጀምሮ) በዴንማርክ ነው ያሳለፍኩት፡፡” ይላል አለማየሁ፡፡

አለማየሁ ብዙዎች እግርኳስን በሚጀምሩበት መንገድ መጫወት የጀመረ ሲሆን ትምህርት ከጀመረ በኃላ በ2000 (እ.ኤ.አ 2008) ለመጀመሪያ ግዜ ወደ መዲናው ቡድን ቦልድክለብ 1893 (ቢ-93) የታዳጊዎች ቡድን ስር መጫወት ጀመረ፡፡ ከአራት ዓመታት የቦልድክለብ ቆይታ በኃላም በ2004 (እ.ኤ.አ. በ2012) በዴንማርክ ሊግ ለሚወዳደረው የኮበንሀቨን ቦልድክለብ የታዳጊዎች ቡድን ለመቀላቀል በቃ፡፡ ቢሆንም አለማየሁ ከኮበንሀቨን ቦልድክለብ የሁለት አመታት ቆይታ በኃላ ወደ ኃያሉ እና በምዕራብ ኮፐንሃገን ወደሚገኘው ብሮንድባይ በ2006 (2014) አምርቷል፡፡ “እግርኳስን ሁሌም እጫወት ነበር፡፡ በውስጤ ያለነገር ነው፡፡ በታዳጊ ማሰልጠኛ ስገባ ለመጀመሪያ ግዜ የተቀላቀልኩት ቢ-93 በ2008 ነው፡፡ በብሮንድባይ ታዳጊ ቡድን ከመጫወቴ በፊት ለኮበንሀቨን ቦልድክለብ (ኬቢ) ነው የተጫወትኩት፡፡ ከ2014 ወዲህ ግን በብሮንድባይ ታዳጊ ቡድን እየተጫወትኩ ነው፡፡ ለኬቤ ለቀቀኩበት ዋነኛው ምክንያት ክለቡ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ቡድን ቢኖረውም ወደ ሊያሳድገኝ ባለመቻሉ በእግርኳስ ህይወቴ የተሻለ የመጫወት እድልን ለማግኘት ወደ ብሮንድባይ አምርቻለው፡፡”

የግራ መስመር አማካይ እና የፊት አጥቂ ሆኖ መጫወት የሚችለው የ17 ዓመቱ አለማየሁ ወደ ባሳለፍነው ነሃሴ ወደ ብሮንድባይ ከ19 ዓመት በታች ቡድን ማደግ ችሏል፡፡ “አሁን ላይ በብሮንድባይ ከ19 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ነው የምጫወተው፡፡ ወደ ቡድኑ ያደግኩት ነሃሴ ወር ላይ ሲሆን አብዛኞቹ የቡድን አጋሮቼ በእድሜ ይበልጡኛል፡፡ ይሁንና በተክለ ሰውነት ረገድ ልዩነት የለንም፡፡”

አለማየሁ ስለኢትዮጵያ የሚያስታውሰው የልጅነት ትዝታ ባይኖረውም ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር ያለው ስሜት አስገራሚ ነው፡፡ ከትውልድ ሃገሩ ጋር ያለውን የጠበቀ ቁርኝነትን ለማሳየት በስሙ ላይ ጭምር ለውጥ ማድረጉንም ይናገራል፡፡ “ሙሉ ስሜ ሉዊስ አለማየሁ ቡሽ ዊኪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ሲጠሩኝ አለማየሁ እንዲሉኝ ነው የምፈልገው፡፡ ስለዚህም በዚህ ስም መጠራቴን እወደዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ቤተሰቦቼ የሚጠሩኝ በቅፅል ስሜ አለማየሁ ነው፡፡ በጉዲፈቻ ከተሰጠው በኃላ ኢትዮጵያ ሁለት ግዜ የመመለስ እድል አጋጥሞኛል፡፡ ሶስት ዓመቴ እያለሁ እና በ11 ዓመቴ ታናሽ እህቴን (ሳራ) በጉዲፈቻ ቤተሰቦቼ ለማሳደግ ሲወስዱ መጥቼ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም ለእኔ የተለየ ቦታ አላት፡፡ ኢትዮጵያ መነሻዬ ነች፤ ለእኔ ሁሉም ነገር የጀመረበት ቦታ፡፡ በቅኝ ግዛት ካልተገዛች፣ የቡና እና የድንቅነሽ (ሉሲ) መገኛ ሃገር በመፈጠሬ ኩራት ይሰማኛል፡፡” የሚለው አለማየሁ ከ20 እና ከ23 ዓመት ብሄራዊ ቡድኖች ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያን መልበስንም ያልማል፡፡ “ከትውልድ ሃገሬ ጋር ያለኝ ጠንካራ ትስስር እና ለእግርኳስ ካለኝ ፍቅር የተነሳ በታዳጊ ደረጃ ኢትዮጵያን ለመወከል አልማለው፡፡” ይላል፡፡

አለማየሁ ከአሳዳጊዎቹ እና ከማደጎ እህቱ ጋር

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው አለማየሁ በዴንማርክ እንደማደጉ ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ ብዙ አጋጣሚዎች የደረሰበት ቢሆንም በተወሰነ ወልኩ አፍሪካዊ በመሆኑ በተክለሰውነት ረገድ መጠቀሙን ያስረዳል፡፡ ነገሮችን በአዎንታዊ ጎኑ መመልከት ብቻ እንደሚፈልግም ይናገራል፡፡ “ከተወሰኑ የዘረኝነት ችግሮች ውጪ እምብዛም በቆዳ ቀለሜ አድሎ ተደርጎብኝ አያውቅም፡፡ ስላገጠሙኝ ችግሮች በስፋት ማንሳት ብችል አሁን ላይ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ወደ ስላጋጠሙኝ አዎንታዊ ነገር ብናገር እወዳለው፡፡ አንዳንድ የክለብ ጓደኞቼ ከመጡበት ጎሳ ምክንያት መገልል ሲደርስባቸው አስተውያለው፡፡ እንደኔ ግን ትውልደ አፍሪካዊ መሆኔ የጠቀመኝ ጎን አለ፡፡ ሰውነቴ በፍጥነት ነው ያደገው፡፡ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ብቻ ነው በፍጥነት የሚበልጡኝን ተጫዋቾች የገጠሙኩት፣ ይህም ከአፍሪካዊነቴ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡”

የማንቼስተር ሲቲ ደጋፊ እንደሆነ የሚናገረው አለማየሁ የአርጀንቲናዊው አጥቂ ሰርጂዮ አጉዌሮ እና የቀድሞ የሴኔጋል ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን እና ሳርስቦርግ ተጫዋች ከርፒን ዲያታ አድናቂ ነው፡፡ በተለይ ዲያታን ሲጫወት መመልከቱ መነሳሳትን እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡ “በዚህ እድሜው የተጓዘው ርቀት በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ እንደ ሳርስበርግ ያለክለብ መቀላቀል መቻሉም አስገራሚ ነው፡፡ ክረምት ላይ እሱን በመመልከቴ ብቻ የተለየ ነገር ለማድረግ አነሳስቶኛል፡፡”

አለማየሁ እምብዛም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና የክለብ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ባለማግኘታቸው የመከታተል እድሉን አለማግኘቱን ይጠቁማል፡፡ “እምብዛም የኢትዮጵያን ጨዋታዎች የመከታተል አልቻልኩም፡፡ ግን ባለፉት ግዜያት በቅርበት ለመከታተል ሞክሪያለው፡፡ ብዙም ጨዋታ ባለመመልከቴ የማደንቀው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች አሁን ላይ ባይኖርም በቤልጄየም ሌሬስ የተጫወተው ሳላዲን ሰዒድን አደንቃለው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *