​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ቻን የማምራት ዕድሉን ያጠበበ ሽንፈት በሜዳው አስተናግዷል

ሞሮኮ በምታስተናግደው የ2018ቱ የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ላይ ለመሳተፍ ዳግም የማጣሪያ ዕድል ያገኙት ዋልያዎቹ ሩዋንዳን ባስተናገዱበት የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለት ጊዜ የመምራት ዕድል ቢያገኙም በስተመጨረሻ 3-2 በሆነ ውጤት ተረተዋል።

በጥሩ ፍጥነት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና መልካም ፉክክር የታየበት ነበር። ገና በ4ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ ከመሀል ሜዳ ያሻገረውን ኳስ በመጠቀም አቡበከር ሳኒ ባደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ተነቃቅተው የጀመሩት ዋልያዎቹ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ተሽለው ታይተዋል። በተለይም በአማካይ ክፍል ላይ የተጣመሩት ሙሉአለም መስፍን ፣ መስዑድ መሀመድ እና ሳምሶን ጥላሁን ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ቡድኑ መሀል ሜዳው ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲኖረው እና የመስመር አጥቂዎቹን በቀላሉ በተደጋጋሚ ቅብብሎች እንዲያገኝ ያስቻለ ነበር።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ አጥቅተው ለመጫወት ድፍረት የነበራቸው ሩዋንዳዎችም 12ኛው ደቂቃ ላይ በቡድኑ የአጥቂ አማካይ ጃቤል ማኒሺሙዌ አማካይነት ከረጅም ርቀት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በሶስት የመሀል ተከላካዮች የሚጠቀመው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን የመስመር ተመላላሾች ለማጥቃት በሚሄዱበት አጋጣሚ የሚተውትን ክፍተት በመጠቀም ዋልያዎቹ በተለይም አስቻለው ግርማ በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል። 17ኛው ደቂቃ ላይም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ መስዑድ መሀመድ መሬት ለመሬት የላከለተን ኳስ ተጠቅሞ አስቻለው ግርማ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ። ከግቧ መቆጠር በኃላ ሩዋንዳዎች ይበልጥ ገፍተው በመጫወት በብዙ አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ መግባት ችለዋል። በተለይም 22ኛው ደቂቃ ላይ የፊት አጥቂው ኢነሰንት ንሹቲ ከለዐለም ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሞከረውና ለዐለም ያዳነበት ኳስ ቡድኑ እጅጉን ለጎል የቀረበበት አጋጣሚ ነበር ። የኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቡድንም በተወሰኑ አጋጣሚዎች በአንድ ሁለት ቅብብሎች የሩዋንዳዎች ሳጥን ውስጥ ቢገባም ንፁህ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችል የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አሁንም ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ዋልያዎቹ ነበሩ። በዚህም 52ኛው ደቂቃ ላይ የመስዑድን የተመጠነ ኳስ አቡበከር በግንባሩ ሞክሮ በዕለቱ ጥሩ ብቃት ያሳየው ግብ ጠባቂው ኤሪክ ለጥቂት ያዳነበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። ከዚህች ሙከራ 3 ደቂቃዎች በኃላ ግን ከግቡ በግምት 20 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት የቀኝ መስመር ተመላላሹ ኤሪክ ሩታንጋ በሚያስገርም ሁኔታ በቀጥታ መትቶ ለዐለምን ምንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ እድል ሳይሰጠው ኳሷን ከመረብ ማገናኘት ቻለ።

በዚህ ጎል አቻ መሆን የቻሉት አማቩቢዎቹ  አሁንም ከማጥቃት ወደኃላ አላሉም። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየም የአማካይ ክፍላቸውን ወደፊት በማስጠጋት ተወስዶባቸው የነበረውን የመሀል ክፍል የባላይነት መቀነስም ችለው ነበር። ሆኖም ቀጣዩን ግብ ማስቆጠር የቻሉት ዋልያዎቹ ነበሩ። 68ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘው የማዕዘን ምት ባጭር ቅብብል ተጀምሮ በሳምሶን አማካይነት ሲሻማ ጌታነህ በግንባሩ ሞክሮ ግብጠባቂው ስላወጣበት ሌላ የማዕዘን ምት ያገኙት ዋልያዎቹ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በአቡበከር ሳኒ የግንባር ኳስ ለሁለተኛ ጊዜ መሪ መሆን ቻሉ። ከዚህ ግብ በኃላም ዋልያዎቹ በአቡበከር ጌታነህ እና ሳምሶን አማካይነት ዕድሎችን ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይ ሳምሶን በፍሬው ሰለሞን ተቀይሮ ከመውጣቱ በፊት ከግቡ አፋፍ ላይ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገኝቶ ያመከነው ኳስ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር።

የተቀሩት ደቂቃዎች የጨዋታው አጠቃላይ መንፈስና ውጤት በፍጥነት የተቀየረባቸው እንዲሁም  ለአሰልጣኝ አንቶኒ ሄይ እና ቡድናቸው እጅግ በጣም ወሳኝ የነበሩ ናቸው። 78ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተላከውና ያልተሳካ የነበረውን ኳስ ለዐለም ብርሀኑ ከያዘው በኃላ በመልቀቁ አቅራቢያው የነበረው ሞሀጅር ሀኪዚማና በቀላሉ በማስቆጠር ሩዋንዳን ዳግም አቻ ማድረግ ቻለ። ይህ ከሆነ ከ2 ደቂቃዎች በኃላም ከግራ መስመር ወደግብ የተላከውን ኳስ ለዐለም ሲያድነው ከሁለተኛው ግብ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ተቀይሮ የገባው አቢዲ ቢራማሂር አግኝቶ ሶስተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል ። ሁለቱ ተከታታይ ግቦችም ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጎ ለነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅስም ሰባሪ ነበሩ።  ቀጣዮቹ 10 ደቂቃዎችም አዲስ ነገር ሳይስተዋልባቸው ጨዋታው በእንግዳዎቹ የበላይነት ተጠናቋል። በዚህም መሰረት ሩዋንዳ ሰፊ የማለፍ ዕድልን ይዛ ሳምንት ኪጋሊ ላይ ኢትዮጵያን የምታስተናግድ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *