​ሪፖርት | ደደቢት እና ወላይታ ድቻ ነጥብ በመጋራት ሊጉን ጀምረዋል

በሳምንቱ መጨረሻ በጀመረው የአዲሱ የውድድር አመት አዲስ አበባ ስታድየም ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደው የደደቢት እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከነበረው የቡድኖቹ ፈጣን እንቅስቃሴ በኃላ በአዝናኝነትም በግብ ሙከራም እየወረደ ነበር የሄደው። 4ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተመላላሹ ያሬድ ዳዊት አሻምቶት ፀጋዬ ብርሀኑ በግንባሩ ከሞከረው ኳስ በኃላ እምብዛም ጠንካራ የሚባል ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ድቻዎች የተለመደ የመከላከል ጥንካሪያቸው አብሯቸው ነበር ። ያም ቢሆን ግን የመስመር ተመላላሾቻቸው የተሻለ ወደፊት ገፍተው ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል። ነገር ግን የመስመር ተመላላሾቹ እንቅስቃሴ ከቡድኑ ሽግግሮች ጋር የተናበበ ባለመሆኑ ቡድኑ ከኃላ ኳስ ለመመስረት ሲሞክር ከመሀል ተከላካዮቹ ብዙ እየራቁ ሲወጡ እንዲሁም ኳስ የፊት አጥቂዎቹ ጋር በሚደርስበት ጊዜ ደግሞ ወደ ኃላ እየቀሩ ይታዩ ነበር። የመስመር አጥቂዎቹም የመስመር ተመላላሾቹ ወደኃላ ሲቀሩ ወደ አማካይ ክፍሉ ለመቅረብ አለመሞከራቸው የቡድኑን የኳስ ስርጭት አዳክሞት ታይቷል። በዚህ ረገድ የፊት አጥቂው ጃኮ አራፋት ወደ አማካይ ክፍሉ እየቀረበ ኳስ ለመቀበል ያደርግ የነበረው ጥረት የሚጠቀስ ነው።

ትላንት በብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ላይ ያየነውን ጌታነህ ከበደን ባልተጠበቀ ሁኔታ ያሰለፉት ደደቢቶች ፊት ላይ ከአቤል ያለው ጋር ቢያጣመሩትም ከሶስቱ የድቻ ተከላካዮች ጋር በብዛት ተነጥለው ይታዩ የነበሩት ሁለቱ አጥቂዎች ንፁህ የግብ ዕድል ማግኘት ተቸግረው ታይተዋል። አቤል አልፎ አልፎ ወደ መስመር እየወጣ ከመስመር አማካዮቹ ጋር ሊገናኝ ሲሞክር ቢታይም ቡድኑ በሁለቱ መስመሮች የነበረው አስፈሪነት ግን እጅግ ቀንሶ ታይቷል። የደደቢት ፈጣሪ አማካይ ፋሲካ አስፋውም መሀል ሜዳ ላይ በድቻ አማካዮች ኃይማኖት ወርቁ እና አብዱልሰመድ አሊ እንቅስቃሴ እየታፈነ በነፃነት መንቀሳቀስ ሳይችል ቀርቷል። ከመስመር ተከላካዮቹ ጋር በመናበብ አጥብበው ወደመሀል በመግባቱ በኩል ደካማ የነበሩት የመስመር አማካዮችም እንቅስቃሴ ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ እንዲወሰድበት ምክንያት ሆኗል። እናም በረጅሙ ይላኩ የነበሩ ኳሶች ላይ ለመመርኮዝ የተገደደው ደደቢት 30ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቴ ካደረገው የረጅም ርቀት ሙከራ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻለም።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በብዙ መለኪያዎች የተሻለ ነበር። በተለይም የጨዋታው ፍጥነት በመጠኑ መጨመሩና የተደረጉትም ም9ከራዎች መበርከት ጨዋታው አይን እንዲስብ ምክንያት ነበሩ ። ዕንግዳዎቹ ድቻዎች የደደቢትን የመሀል ሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች በመቁረጥ በሁለቱ መስመሮች በኩል ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንደማድረጋቸው መጠን የበረከቱ የግብ ሙከራ ባያደርጉም በተወሰነ መልኩ የክሌመንትን ግብ መፈተን ችለዋል። በተለይም 47ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ብርሀኑ ከጃኮ አራፋት የተላከለትን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረውና 71ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ጃኮ አራፋት ከሳጥኑ ውስጥ ሞክሮት የግቡ አግዳሚ ያወጣበት አጋጣሚ ተጠቃሾች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ በተለይ ሽመክት ጉግሳን ወደመሀል እያጠበበ በመግባት እንዲጫወት ያደረጉት ደደቢቶች በቀኝ በኩል ከመጀመሪያው የተሻለ ጫና መፍጠር ቢችሉም ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚረዳ ግብ ማስቆጠር ግን አልሆነላቸውም። በተከታታይ ቀናት ሙሉ 90 ደቂቃ የተጫወተው ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታቸው እና ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ በግንባሩ ለማስቆጠር የሞከራቸው ኳሶች ደደቢትን ወደሸናፊነት ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። 86ኛው ደቂቃ ላይም ስዩም ተስፋዬ ወደጎል ያሻማት ኳስ እቅጣጫዋን ወደመረቡ ብታደርግም ፌቮ ለጥቂት አውጥቷታል። በጥቅሉ ጥሩ ፉክክር የታየበት ሁለተኛ አጋማሽ በዚህ መልክ ሲገባደድ ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

በሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ሲቀጥሉ ቅዳሜ 11 30 ላይ ወላይታ ድቻ መከላከያን ስገጥም እሁድ 9፡00 ላይ ደደቢት ከ አዳማ ከተማ ይገናኛል ።

የአሰልጣኞች አስተያየት

የደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ

“የጨዋታ እንቅስቃሴው አይከፋም፡፡ ተጋጣሚ ቡድን በመከላከል ረገድ አቻ ወጥቷል፣ ሰብረን ልንገባ አልቻልንም፡፡ ኳስ ይዘን የመጫወት እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነው ግን ወደ ግብ ያደርግናቸው ሙከራዎች አልተጠቅምንባቸውም፡፡ እንቅስቃሴው ጥሩ ነው፡፡”

“እኛ ለማጥቃት ከፍተን ነው የምንጫወተው፤ ተጋጣሚ ደግሞ በመከላከል የታጠረ ስለነበር ይህን ለማስከፍት ሞክረናል፡፡ እነሱ በመልሶ ማጥቃት ነበር የሚመጡት፡፡ ከእኛ ተሽለው ሳይሆን እኛ ለማጥቃት ብዙን ግዜ ወደ ፊት እንሄድ ስለነበረ ነው፡፡”

“የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው፡፡ ያገኘነው ውጤት ጥሩ ነው፡፡”

የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ

“ጨዋታው ጥሩ ነው፡፡ እንዳያችሁት በጥንቃዌ ነው የተጫወትነው፡፡ ከአሸናፊዎች አሸናፊ በኃላ ስንሰራቸው የነበሩ ነገሮች አሉ፡፡ ያየናቸውን ነገሮች ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡ ደደቢት ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ግን እንደነበረው ጥንቃቄ እና እንደፈጠርነው የግብ አጋጣሚዎች ከዚህ የተሻለ ቢሆን መልካም ነበር፡፡”

“የተወሰኑ ጨዋታዎችን አጥተን ነው የመጣነው ይህ ደግሞ በራስ መተማመን ይፈልጋል፡፡ ይህም አንድ ነገር ነው በራስ መተማመናችንን ያሳድገዋል፡፡ ስንከላከል ጠንካራ ነን የግብ አጋጣሚም እና ክፍተት አንፈጥርም በመሃልም ያለን ነገር ጠንካራ ነው፡፡ በፍጥነት ወደ ባላጋራ ሜዳ ስንገባም በቀላሉ ነው የግብ አጋጣሚዎችን የምንፈጥረው፡፡ በቀጣይ የምናገኛቸው አጋጣሚዎች በአግባቡ ተጠቅመን አሸንፈን ለመውጣት እንሰራለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *