​አቶ ተክለወይኒ ከእጩነት ሲነሱ ሌሎች ክልሎችም እጩዎቻቸው የተወከሉበትን መንገድ እያጤኑ ነው

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብዙ የተጠበቀው ጠቅላላ ጉባዔን ካካሄደ በኋላ ምርጫው ለ45 ቀናት እንዲራዘም መወሰኑ ትኩሳቱን ለተጨማሪ ጊዜያት ያባባሰው መስሏል፡፡ ጉባዔው ተጠናቆ ብዙም ሳይቆይም ከወዲሁ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡

ከጠቅላላ ጉባዔው ዋዜማ አንስቶ አስገራሚ የሆኑ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ከፊፋ ጋር በግል የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች ፣ የማህተም እገዳ ፣ በስራ አስፈፃሚዎች እና በፕሬዝዳንቱ መካከል ከቡጢ መሰናዘር እስከ የውሀ ኮዳ መወራወር የደረሰ ክፍፍል እስከ ጠቅላላ ጉባዔው መዳረሻ ዘልቋል። በሁለት ቀን ውሎው ምንም እንኳ የኮዳዎች መወራወር ባይኖርም የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ ጉባዔው ሊደረግበት ስለታሰበው ቦታ ያደረጉት አወዛጋቢ ንግግር የስፖርት ቤተሰቡን ያሳዘነ ተግባር ሆኖ አልፏል። ጉባዔው ሰመራ እነንዲካሄድ የታሰበው የሚድያ “ጭፍጨፋ”ን ለመሸሽ እንደሆነ ፣ በመጀመርያ አስበው የነበረው መቀለ ከተማ ላይ እንዲካሄድ መሆኑን መናገራቸው እና የጉባዔው መቀለ መካሄድን አስፈላጊነት ከከተማው ቆነጃጅት ጋር ማያያዛቸው ውግዘት አስከትሎባቸዋል፡፡

ታዲያ ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ምሽቱን የትግራይ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ እጩ የነበሩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋን ማንሳቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ያቀረበው ምክንያትም ያደረጉት ንግግር ክልሉን የማይወክል ነው የሚል ነው፡፡

የአቶ ተክለወይኒን ከእጩነት መነሳት ተከትሎ ሌሎች ክልሎች የዕጩ ተወካዮቻቸውን ሁኔታ ለማጤን እያሰቡ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ በተለይ ዛሬ በድሬዳዋ መገናኛ ብዙሀን ሲገለፅ እንደተሰማው ከሆነ በከተማ አስተዳድሩ እጩ ሆነው የቀረበት አቶ አበበ ገላጋይ በከተማው ነዋሪ ከፍተኛ ትችት እየቀረበባቸው እንደሆነ እና እጩ ሆነው የተላኩበት መንገድም አሳማኝ እንዳልሆነ ተነግሯል፡፡ ይህን ተከትሎም በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ የድሬዳዋ ከተማ አመራሮች በአቶ አበበ ጉዳይ ላይ ሊወስኑ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው።

ድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክልሎችም የትግራይ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ ያነቃቸው ይመስላሉ፡፡ በቀጣይም አስቀድመው እጩ ሆነው በቀረቡ ተወካዮች የተመረጡበትን መንገድ ሊያጤኑበት እንደሆነም ሰምተናል።

የአቶ ተክለወይኒ አሰፋን ከእጩ ተወካይነታቸው ያነሳው የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ መሆኑ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለው በሚል ወደ ህግ ሊያመሩ እንደሚችል እየተሰማ ይገኛል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *