​ሪፖርት | ወላይታ ድቻ የአመቱን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የዕለተ ቅዳሜ ብቸኛ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በጃኮ አራፋት ጎል መከላከያን መርታት ችሏል ።

መከላከያ በጉዳት ያጣውን ሳሙኤል ታዬን በየተሻ ግዛው በመተካት እና ፊት መስመር ላይ በማሰለፍ በኤሌክትሪኩ ጨዋታ ከፊት ከምንይሉ ወንድሙ ጋር የተጣመረውን ሳሙኤል ሳሊሶን ወደ ግራ አማካይ መስመር በመመለስ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን ወላይታ ድቻ በበኩሉ ደደቢትን ከገጠበት ጨዋታ የቅርፅም ሆነ የተጨዋች ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች እንቅስቃሴ ሲጠቃለል ወላይታ ድቻ በአመዛኙ እንደወትሮው ጥንቃቄን የመረጠበት እንዲሁም መከላከያ ባገኘው የተሻለ የመሀል ሜዳ የበላይነት በመጠቀም ጫና ፈጥሮ የተጫወተበት ነበር።  የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ እየታየባቸው ዘልቀው ሳሙኤል ሳሊሶ በሀይሉ ግርማ የጨረፈለትን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ሞክሮ ፌቮ ባወጣበት አጋጣሚ ተነቃቅቷል። መከላከያዎች ከዚህች ሙከራ በኃላ በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ የቻሉ ሲሆን ኢማኑኤል ፌቮ የበሀይሉ ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰን ሙከራዎች ማዳን ሲችል የምንይሉ ወንድሙ የ39ኛ ደቂቃ የግንባር ኳስም በግቡ አናት ወጥታለች። በብዛት በራሳቸው ሜዳ ላይ ቀርተው ይታዩ የነበሩት ድቻዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰመድ አሊ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ካደረጋት እና ይድነቃቸው ካዳነበት ጠንካራ ሙከራ ውጪ ወደ መከላከያ ሳጥን ሲገቡ ቢታዩም ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ የጨዋታ ሚዛኑ ወደ ድቻዎች ያደላበት ነበር። በተለይ ቡድኑ በቀኝ መስመር አጥቂው ፀጋዬ ብርሀኑ በኩል ባጋደለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የመከላከያን የግብ ክልል ከመጀመሪያው በተሻለ መፈተሽ ችሏል። 54ኛው እና 59ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት ያገኛቸው ዕድሎች በዚህ በኩል ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ 59ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ በመሀል ተከላካዮቹ በምንተስኖት እና በአወል መሀል በተፈጠረው ሰፊ ክፍተት መሀል ተገኝቶ ከፀጋዬ የተቀበለው እና ያመከነው ኳስ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ነበር። ከዛ ውጪ 68ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ ቀኝ መስመር ሰብርም የገባው ፀጋዬ የፈጠረውን ንፁህ ዕድል ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ጃኮ አቀበለ ተብሎ ሲጠበቅ ራሱ ሞክሮ ይድነቃቸው በቀላሉ ያዳነበት ኳስ የሚጠቀስ ነው ። ከዕረፍት በፊት በብዙ አጋጣሚዎች ወደጎል ሲደርሱ የነበሩት መከላከያዎች በሁለተኛው አጋማሽ 57ኛው ደቂቃ ላይ ቴውድሮስ ታፈሰ ከቀኝ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት ምንተስኖት በግንባሩ ከሞከረበት እና በኃይሉ ግርማ 79ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ፌቮ ካዳነበት ኳስ ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በተቃራኒው ድቻዎች የተሻለ ጫና እየፈጠሩ ከቆዩ በኃላ 82ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝ ወደኃላ ለማቀበል የሞከረውን ያጠረ ኳስ ያገኘው ጃኮ አራፋት በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር ቀዳሚ አድርጓቸዋል። ከዚህ በኃላም ወደኃላ ያላፈገፈጉት ድቻዎች በጃኮ አማካይነት  ከመከላከያ የኃላ መስመር ጀርባ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአንፃሩ መከላከያዎች አቻ ለመሆን የሚያበቃቸውን ዕድል ተረጋግተው መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በ”ጦና ንቦች” አሸናፊነት ተጠናቋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት


አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ- መከላከያ
” ተጋጣሚያችን በሰባት ተጨዋቾችን ከኃላ አድርጎ ነበር የተጫወተው እኛ ደግሞ ኳስ ተቆጣጥረን በመጫወት ጎሎችን ለማስቆጠር ነበር የሞከርነው ። መጨረሻ ላይ ብንሸነፍም ጨዋታውና ውጤቱ የሚገናኝ አይደለም ። የተቃራኒ ቡድን አጨዋወት ዝግ ነበር እኛ ግብ የማስቆጠር ችግር አለብን እንጂ ጥሩ ተጫውተናል ። በዛ ላይ በተደጋጋሚ ይወድቁ ነበር ። ይህም የጨዋታውን ሪትም አበላሽቶታል ። ዳኛውም በሚገባ አልተቆጣጠረውም ”


አሰልጣኝ መሣይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ
” ከጨዋታ ጨዋታ የተወሰኑ ለውጦችን እያየን ነው ። ጥሩ የመከላከል አቅም አለን ። ተጋጣሚያችን ጠንካራ ነበር ። በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ የተሻሉ ነበሩ ። በሁለተኛው አጋማሽ ትኩረታችንን ጨምረን አሸንፈን ለመውጣት ችለናል ። ባጠቃላይ በራስ መተማመናችን ከፍ እያለ ነው ።  ከጊዮርጊስ ጋር ከነበረው ጨዋታ በኃላ ከደደቢት ጋር የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር ። በነበሩብን ክፍተቶች ላይ በመስራታችንም ለውጦች እያየን ነው ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *