​ሪፖርት | ቻምፒዮኖቹ በጭማሪ ደቂቃ ጎል በመቐለ ከመሸነፍ ተርተፈዋል

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው መቐለ ከተማ የተገናኙበት የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተደምድመዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ዛሬ በ97 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ግብ ጠባቂ ለነበሩት ታደሰ ጌጡ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

እንግዳዎቹ መቐለዎች ሳምንት ወልዋሎ ዓ.ዩን ከገጠሙበት ቡድን በተለየ ቀኝ መስመር ተከላካይ ላይ ዳንኤል አድሀኖምን ሲጠቀሙ የቦታው ተሰላፊ የነበረውን አቼምፖንግ አሞስን አጥቂ መስመር ላይ ወስደውት በ4-2-3-1 አቀራረብ ጨዋታውን ጀምረዋል። የሁለቱ ሳምንታት የሊግ ጨዋታዎች በቀሪ ጨዋታነት የተያዙለት ቅዱስ ጊዮርጊስም በተለመደው የ4-3-3 አሰላለፍ ወደሜዳ ገብቷል።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ መልኩ ኳስ መስርተው በመጫወት ዕድሎችን ለመፍጠር በሞከሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በተለይ ከሜዳቸው መጥተው የተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ በፍጥነቱ እጅግ ዘገምተኛ የሆነ የኳስ ቅብብል ላይ መመስረታቸው ለጨዋታው ሙከራ አልባነት ዋና ምክንያት ሆኖ ታይቷል።

13ኛው እና 18ኛው ደቂቃ ላይ በአሉላ ግርማ እና አብዱልከሪም መሀመድ አማካይነት ከረጅም ርቀት ከተደረጉ ሙከራዎች እና 25ኛው ደቂቃ ላይ ከታየው አበባው ቡታኮ ቅጣት ምት ውጪ ሌላ አጋጣሚ መፍጠር ያልቻለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ከአዲሱ አጨዋወት ጋር ለመላመድ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል ተስተውሏል። ጊዮርጊሶች ኳስ ከሜዳቸው መስርተው ለመውጣት ሲሞክሩ ከሚኖራቸው በሜዳው ቁመት እጅግ የተለጠጠ የተጨዋቾች ቦታ አያያዝ ምክንያት ምንም እንኳን አመዛኙን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወስዱም አጥቂዎቻቸውን በአጭር ቅብብሎች ማገኘት እንዲቸግራቸው ሆነዋል። አልፎ አልፎ አቡበከር ወደመሀል መጥቶ ኳስ ለመቀበል ጥረት ካደረገባቸው አጋጣሚዎች ውጪም ሶስቱ የጊዮርጊስ አጥቂዎች ከመቐለ አራት ተከላካዮች ጋር ተለጥፈው ይታዩ ነበር። ይህ በመሆኑም የጊዮርጊስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ከራሱ የሜዳ ክልል እና ከመሀል ሜዳው ክብ ማለፍ ሳይችል ቀርቶ አሜ መሀመድ ኳስ ያገኝ የነበረው አልፎ አልፎ ከአበባው በሚጣሉ ረጅም ኳሶች ነበር። የቡድኑ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎችም ተጋጣሚያቸው በመስመሮች መሀከል በሚተወው ክፍተቶች ላይ እየተገኙ የመቀባበያ አማራጮችን ለመፍጠር አለመሞከራቸው የቡድኑን የጨዋታ ፍሰት ይበልጥ ገድቦት አምሽቷል።

የጊዮርጊስ የኩስ ቁጥጥር እምብዛም ወደ ሜዳቸው ዘልቆ ባይገባም መቐለ ከተማዎች በማጥቃቱ ረገድ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደ ቡድን የነበራቸው እንቅስቃሴም አመርቂ አልነበረም። በተከላካይ መስመሩ እና በአማካይ ተከላካዮቹ እንዲሁም ከአጥቂው ጀርባ ባሉት አማካዮች እና በተከላካይ አማካዮቹ መሀል ሰፊ ክፍተት ሲተው የነበረው የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ተጋጣሚው እነዚህን ክፍተቶች አለመጠቀሙ እንጂ ዋጋ ሊከፍልበት ሚችልበት ዕድል ነበር። ቡድኑ በማጥቃት ወቅት በቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ላይ ሲገኝም በቁጥር ተበልጦ እና ያለ መስመር ተከላካዮቹ እገዛ መሆኑ አንድም ሙከራ ሳያደርግ የመጀመሪያው አጋማሽ እንዲጠናቀቅ ምክንያት ሆኖታል። ሆኖም የቀይ እና ነጭ ለባሾቹ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች በመከላከል ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ከፍ ማለቱ በራሱ ቡድኑ በቀላሉ እንዳይሰበር ያገዘ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር መቐለዎች ያሬድ ከበደን በጋይሳ አፖንግ ቀይረው በማስገባት እና ፊት ላይ ከአቼምፖንግ አሞስ ጋር አጣምረውታል። በዚህ መልኩ ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ፊት ሁለቱን ጉልበተኛ አጥቂዎች በመጠቀም እና ኳሶችን ለንሱ በማድረስ ላይ የተመሰረት እንቅስቃሴን መምረጡ ከመጀመሪያው በተሻለ ጉልበት እንዲኖረው አድርጓል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አሉላ ግርማን ቀይሮ የገባው ጋዲሳ መብራቴ ከአሉላ በተሻለ ለኒኪማ ቀርቦ በመጫወት የመጀመሪያ አጋማሽ የቡድኑን ክፍተት ለመሙላት ሞክሯል። ሆኖም ጨዋታው እንደመጀመሪያው ሁሉ ጥርት ያሉ የጎል ዕድሎች በቁጥር በዝተው ሊታዩበት አልቻሉም። 49ኛው ጋይሳ አፖንግ እንዲሁም 59ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ቢሆኑ ያን ያህል አስደንጋጭ የሚባሉ አልነበሩም።

63ኛው ደቂቃ ላይ አቼንፖንግ አሞስ በምንተስኖት አዳነ በመጠለፉ ምክንያት መቐለዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አምና በከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ያጠናቀቀው አማኑኤል ገ/ሚካኤል አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ጊዮርጊሶች የአቻነት ግብ ፍለጋ ብዙ ሰዐታቸውን በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ሲያጠፉ መቐለዎች ጋይሳ አፖንግን ከፊት በማድረግ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን እየጠበቁ በጥልቀት መከላከልን መርጠዋል። ሆኖም 90ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አበባው ቡታኮ ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ አስቆጥሮ መቐለዎችን የመጀመሪያ የሊግ ድላቸውን ከማጣጣም ገቷቸዋል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *