​ሪፖርት | በደቡብ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት በውዝግቦች የታጀበው የደቡብ ደርቢ በያቡን ዊልያም ጎል በባለሜዳዎቹ ሀዋሰ ከተማዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው አስቀድሞ በስታድየሙ ዙሪያ ረጃጅም ሰልፎች የነበሩ ሲሆን የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ማህበር የስቴዲየሙን ፀጥታ ለመቆጣጠር ያዋቀራቸውን ስነ ስርአት አስከባሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልክተናል። በሁለቱም ክለቦች በኩል አስገራሚ የድጋፍ ድባብን ያስተናገደው ጨዋታም ከታየበት ጥሩ ፉክክር  ባለፈ ያልተገቡ የተጫዋቾች ሽኩቻዎች እና የደጋፊ ረብሻን ተከትሎ በተፈጠረ የድንጋይ መወራወር ምክንያት የተከሰቱ ጉዳቶችንም ጭምር አሳይቶን አልፏል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ፊሽካ አብሳሪነት የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪዎቹን 20 ደቂቃዎች እልህ የቀላቀለ እንቅስቃሴን ያስተናገደ ነበር። ልክ ሁለቱ አስር ደቂቃዎች እንዳበቁ ሀዋሳ ከተማዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ተሽለው ታይተዋል። በተለይም በ23ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተ/ማርያም ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አዲስአለም ተስፋዬ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ ኳሷ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት ሙከራ ሀይቆቹን ቀዳሚ ልታደርግ የተቃረበች ነበረች። 27ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ ፍሬው ሰለሞን ያሾለከለትን ኳስ በመጠቀም ሞክሮ ኢማኑኤል ፌቮ በቅልጥፍና ያዳነበት ሲሆን ዳዊት በድጋሚ ከታፈሰ ሰለሞን በደረሰው ኳስ ከፌቮ ጋር ቢገናኝም ሙከራው ወደላይ ተነስቶበታል። በሌላ አጋጣሚም አዲስአለም ያሻማው እና ያቡን ዊልያም ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስም የሀዋሳ ከተማ የማጥቃት ስትራቴጂ ጥንካሬ  እና በተደጋጋሚ ለጎል መቃረብን የሚያመለክት ነበር። በአንፃሩ የወላይታ ድቻዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በጃኮ አራፋት የግል ብቃት ላይ የተመሰረተ ነበር። የተጫዋቹ እንቅስቃሴ ለሀዋሳ ከተማ የተከላካይ ክፍል ፈተና ሆኖ ቢታይም የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳይስተናገድበት ነበር የተጠናቀቀው።

የሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም በበርካታ ካርዶች የታጀበ እንዲሁም አጨቃጫቂ የዳኝነት ውሳኔን ያስተናገደ እና ቁጥራቸው የበረከቱ የሜዳ ላይ ግጭቶች ያሳየ ነበር። ሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ በላይም በደጋፊዎች መሀከል በተነሳ ረብሻ ምክንያት የወረደው የድንጋይ ዕሩምታ የጨዋታው መአብይ ክስተት ሆኗል። ሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴም እንደ መጀመሪያው ሁሉ ሀዋሳ ከተማዎች ጫና ፈጥሮ በመጫወቱ እና የግብ ሙከራዎችን በማድረጉ በኩል የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። የድቻዎች የማጥቃት ሂደት ግን አሁንም በጃኮ አራፋት ላይ የተንጠለጠለ ነበር።

66ኛው እና 68ኛው ደቂቃ ላይ ከታፈሰ ሰለሞን የተነሱኳሶች ለፍሬው ሰለሞን እና ደስታ ዮሀንስ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ግብ መሆን ግን አልቻሉም። የድቻው የፊት አጥቂ ጃኮ አራፋት ከግቡ ጠርዝ ላይ አክርሮ ሞክሮ ተክለማሪያም ያዳነበት አጋጣሚም ሌላው የጨዋታው ጠንካራ ሙከራ ነበር።

76ኛው ደቂቃ ላይ  አማካዩ ኃይማኖት ወርቁ በፀጋአብ ዮሴፍ ላይ የኃይል አጨዋወትን ተጠቅሟ በሚል ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በቀይ ካርድ ካስስወጡበት ቅጽበት ጀምሮ የጨዋታው መንፈስ ተቀይሮ አላስፈላጊ ድርጊቶች ተከስተዋል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎም የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በተቃውሞ የውሀ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን ወደ ሜዳ ሲወረውሩ ተስተውሏል። ጨዋታው በዚህ መንፈስ ቀጥሎ 86ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከግራ መስመር በረጅሙ ያሻማትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን አመቻችቶ ለያቡን ዊሊያም ሲሰጠው ዊሊያም በግንባሩ አስቆጥሮ ሀዋሳን ቀዳሚ አደረገ፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ወላይታ ድቻዎች ጎሏ ከጨዋታ ውጭ ናት በሚል ተቃውሟቸውን በረዳት ዳኛው ላይ በማሰማት ላይ እያሉ ኳስ ከመሀል ሜዳ እንደተጀመረች በተለምዶ ካታንጋ ተብሎ በሚጠራው የስታድየሙ ክፍል አካባቢ በተነሳ የደጋፊዎች የድንጋይ ውርወራ በርካታ ተመልካቾች ላይ ጉዳት ደርሷል። ለፀጥታ ሀይሎች ፈታኝ በነበረው በዚህ ጊዜ በተነሳው ግርግር ምክንያት ጨዋታው ለ18 ያህል ደቂቃዎች ተቋርጧል ፡፡ ጨዋታው ካቆመበት ሲቀጥልም ድቻዎች የጎሉን ከጨዋታ ውጪ መሆን አስመልክተው የረዳት ዳኛውን ፌ/ዳ ይበቃል ደሳለኝን ውሳኔ በመቃወም ክስ አስመዝግበዋል።

ከፍተኛ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈት የታየበትይህ ጨዋታም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል ፡፡ በዚህም መሰረት ሀዋሳ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ወላይታ ድቻን አሸንፏል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

” ጨዋታው ሁለታችንም ተሸንፈን እንደመምጣታችን ውጥረት የበዛበት ነበር። በተለይ እኛ ከእረፍት በፊት ብዙም የግብ አጋጣሚ አልነበረንም። በሁለተኛው ግማሽ ግን በጥንቃቄ የተሞላ እንቅስቃሴ ነበረን። ከረፍት መልስ መሻሻሎችን አሳይተናል። ባለሜዳ እንደመሆናችን ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። የጎላ ዕድል መፍጠር ባንችልም የተሻለን ነበርን። ማጥቃት ላይም ሆነ መከላከል ላይ ያለን ነገር ጥሩ ነበር ማለት እችላለው። ከሜዳ ውጭ ያለብንን የማሸነፍ ችግር ለመቅረፍም እንሞክራለን። በተነሱት ያልተገቡ ረብሻዎች ግን በተገኘው ነገር ሁሉ ሆድ መባባሱ ጥሩ ነው ብዬ አላስብም። የሚጠቅመንን እንጂ የሚጎዳንን ተግባር በሜዳ ላይ ማሳየት የለብንም። ይህ ለኛ አይጠቅመንም። መሻሻል አለበት። ለሀገራችን ኳስ ምናስብ ከሆነ ይህ አሳዛኝ ነው፡፡ ”

መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ

” ያው በጨዋታው እነሱ የተሻሉ ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ጥሩ ነበሩ። ነገሮችን እኛም ለማስተካከል ጥረት አድርገናል። ነገር ግን በመጨረሻ ደቂቃ ላይ አስቆጥረው አሸንፈውናል ም። ቀይ ካርዱም በጣም ተገቢ ነው ብዬ አስባለው። ጎሉም ቢሆን ለኔ ባይታየኝም ዳኛው ጎል ብሎ ወስኗል። በዳኝነቱም ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ዳኛው ህጉን ነው የሚተረጎመው። እኛ ግን ተቀብለን ራሳችንን ነው ማየት ያለብን። በዳኝነቱ ቅሬታ ባይኖረኝም ዳኞች ግን ምን ጊዜም ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። የፈለግነውን አላገኘንም የነሱም አጨዋወት ተመሳሳይ ስለነበረ እነሱ በሁለተኛው አጋማሽ ካገቡት ውጪ ይህ ሚባል ነገር አልፈጠሩብንም። በቀጣይ መስተካከል አለብን። የተፈጠረው ረብሻ ግን አሳዛኝ ነው። በዳኝነት ስተት ይኖራል። ድንጋይ መወራወር ግን አግባብነት የለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *