ዩራጓይ 2018 | የኢትዮጵያ ከ17 አመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማጣርያ ጨዋታውን ነገ ከናጄርያ ጋር ያደርጋል

በአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣርያ አንደኛ ዙር ኢትዮጵያ ናይጄርያን ትገጥማለች፡፡ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ የመጀመርያ ጨዋታ (First Leg) ነው፡፡

ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድናችን የቅድመ ማጣርያ ዙር ጨዋታውን በጥቅምት ወር መጨረሻ ከኬንያ ጋር ለማድረግ እጣ ቢወጣለትም ኬንያ በቂ የዝግጅት ጊዜ ባለማግኘት እና በሌሎች ምክንያቶች አልሳተፍም ማለቷን ተከትሎ ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ዙር በፎርፊ ማለፍ ችሏል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከቀጣይ ተጋጣሚው ናይጄሪያ ጋር ለሚኖርበት የማጣርያ ጨዋታ በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ እየተመራ በኢትዮዽያ ሆቴል ማረፊያውን አድርጎ 22 ተጨዋቾችን በመያዝ በተጠናከረ ሁኔታ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ቡድኑ ዘግይተው የተቀላቀሉ 3 ተጫዋቾችን በማካተት ዛሬ ረፋድ ላይ የመጨረሻ ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታድየም የሰራ ሲሆን ከጨዋታው አስቀድሞ የሚጠቀምባቸውን 18 ተጨዋቾች ነገ ጠዋት ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  የመከላከያዋ አጥቂ የምስራች ላቀው በብሽሽት ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ስትሆን የሁለት ተጨዋቾች የፓስፖርት ጉዳይ ባለማለቁ ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆነዋል፡፡ የተቀሩት 22 ተጫዋቾች ግን በሙሉ ጤነኝነት ለነገው ጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠናል።


አሰልጣኝ ሰላም ዘራይ የነገውን ጨዋታ አስመልክቶ ለሶከር ኢትዮዽያ የሰጠችውን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል

ቡድኑ ዝግጅት

‹‹ ከባለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ ዝግጅታችንን እያደረግን እንገኛለን፡፡ ኬንያ ከውድድሩ በመውጣቷ ምክንያት ተጫዋቾቼ ወደ የክለቦቻቸው አምርተው ነበር፡፡ አሁን ከናይጄሪያ ጋር ላለብን ጨዋታ መልሰን በመጥራት በነበረብን ድክመት ላይ በተቻለን መጠን በጥሩ ሁኔታ እየሰራን ነው።››


ዘግይተው ስለገቡ ተጨዋቾች

‹‹ ያነሳሀው ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም አሁን ባየሁት የናይጄሪያ ቡድን ውስጥ አምስት ተጨዋቾች ባለፈው በነበረው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የነበሩና በድጋሚ የተጠሩ ናቸው። ከ17 አመት በታች ውድድር ዋናው አላማው ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ማሳደግ እንደመሆኑ ቀጣይነት ያለው ስራ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ሀገር አዲስ ፊት ይመጣና እነዛን አፍርሶ ሌላ ፊት ይመጣል፡፡ እንደተባለው እነዚህ ልጆች ከሁለት አመት በፊት ከ17 አመት ቢጫወቱም በካፍ አንደር ኤጅ ስለሆኑ ፓስፖርቱን ስለሚያጫውታቸውና ልምዳቸው ስለሚጠቅም ወደ ቡድኑ ጠርተናቸዋል። ››


ስለ ተጋጣሚ ቡድናችን

‹‹ ቡድኑን በአጠቃላይ ስገመግመው በጣም በራስ መተማመን ያላቸው እና እርግጠኛ ሆነው ለማሸነፍ እንደመጡ ያሳያል፡፡ ይህን በመልካም ነገር ነው የምወስደው፡፡ አኛ አድቫንቴጃችን ለመጠቀም የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።››


ስህተቶችን ላለመስራት የሚደረግ ጥንቃቄ

‹‹ የምንገጥመው ናይጄሪያን ብቻ አይደለም ፤ ያለፈውን ታሪካችንንም ጭምር ነው፡፡ ከናይጄሪያ ይልቅ ሁልጊዜ የሚከብደን ያለፈው ታሪካችን ነው፡፡ በጨዋታው ላይ ስህተቶችን ላለመስራት ብዙ አውርተናል ተነጋግረናል፡፡ በሜዳችን እድሎችን ለሌሎች ቡድኖች አሳልፎ ላለመስጠት የምንችለውን ለማድረግ እንጥራለን።››

የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ናይጄሪያ 30 የልዑካን ቡድን በመያዝ ሐሙስ አአ የገቡ ሲሆን ለሦስት ተከታታይ ቀናት ልምምዳቸውን ሰርተዋል፡፡ ወደ አአ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ከናይጄርያ የ15 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና የአቡጃ ሴቶች ምርጥ ቡድን ጋር ያደረጉ ሲሆን ሁለቱንም በድል ተወጥተዋል፡፡


ጨዋታውን የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከታንዛኒያ ሲመደቡ የጨዋታው ኮምሽነር ከኬንያ ነው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *