ሴካፋ 2017 ፡ ‹‹ ከደቡብ ሱዳን የምናደርገው ጨዋታ ቀላል አይሆንም ›› አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ

በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ምድብ ሁለት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ 9፡00 ሰዓት ላይ ደቡብ ሱዳንን ካካሜጋ በሚገኘው ቡኩንጉ ስታዲየም ይገጥማል፡፡

ዋሊያዎቹ ከሐሙስ አመሻሽ ጀምሮ በምዕራባዊ ኬንያ በምትገኘው ካካሜጋ ከትመው ልምምዳቸውን ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የቡድኑ ለጨዋታ ያላው ስሜት እና ተነሳሽነት መልካም የሚባል እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ ጨምረው ከሩዋንዳ ጋር ከነበረው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ግጥሚያ በኋላ ለሴካፋው ተሻሽሎ ለመቅረብ እንደተሞከረ አስረድተዋል፡፡ “ልጆቹ ተነሳስነታቸው ጥሩ ነው፡፡ ወጣቶች ስለሆኑ የተሻለ ስራ ይሰራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከሩዋንዳ ጋር ምንም እንኳን ውጤቱ በሽንፈት ቢጠናቀቅም ቡድናችን ጥሩ ነበር፡፡ ቡድኑ ሃገር ቤትም ይሁን ከሃገር ቤት ውጪ ያደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው፡፡ ህዝቡ ምንም ይሁን ምን ከብሄራዊ ቡድኑ ጎን ነው፡፡ ህዝቡ ላደረገልን ነገር እናመስግናለን፡፡”

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳንን ጋር በሴካፋ የምድብ ጨዋታ ስትገናኝ ይህ ለሶስተኛ ግዜ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ ከውስን መረጃዎች ውጪ ስለተጋጣሚያቸው በቂ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ “ብዙዎቹ የውጪ ቡድኖች የማጥቂያ መነሻቸው የመስመር አጨዋወት ነው፡፡ እሁድ እና ሰኞ የተደረጉ ጨዋታዎች ተመልክተን ብዙ ግዜ የማጥቂያ መነሻቸው መስመር መሆኑን አይተናል፡፡ ይህንን ለመዝጋት አስበናል፡፡ ተጋጣሚያችን ምን ይዞ እንደሚመጣ አላወቅንም እንግዲህ፡፡ ሜዳ በምናደርገው እንቅስቃሴ የምናደርጋቸው ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን መስመሩን ለመዝጋት አስበናል፡፡”

አማካዩ ተስፋዬ አለባቸው ከዛሬ ጨዋታ ውጪ መሆኑ ታውቋል፡፡ ተጫዋቹ ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ ማድረግ ቢጀምርም ለጨዋታው ግን አይደርስም፡፡ “የሃኪሞቹ ውሳኔ ነው፡፡ ወደዚህ ይዘነው ስንመጣ አንድ ጨዋታ ሊያልፈው እንደሚችል ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ ውድድሩ እንደሚታወቀው የምድብ ነው፡፡ ቀጥሎም ጥሎ ማለፎች ይኖራሉ፡፡ በቦታው የእሱ ዓይነት አጨዋወት ባህሪ ያለው ተጫዋች እንፈልግ ስለነበረ እንዲሁም ሌሎች ተጫዋች ቢኖሩም ከአንድ ክለብ ከሁለት በላይ ተጫዋቾች መምረጥ ስላልተቻለ ያለን አማራጭ በእሱ መቀጠል ነው፡፡”

ቡሩንዲ ከዩጋንዳ ጋር አቻ መለያየቷን ተክትሎ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ቡድኖች ተርታ የሚሰለፈው ደቡብ ሱዳን ቀላል ተጋጣሚ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው አሰልጣኝ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡ “እግርኳስ ሜዳ ላይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ተወዳጅ የሚያደርገውም ይህ ባህሪው ነው፡፡ ማን ቀደሞ ያሸነፋል ብሎ መገመት ከባድ ነው፡፡ ውድድሩ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል፡፡ ምክንያቱም አዲስ ጉልበት ይዞ የሚመጣ ቡድን (ደቡብ ሱዳን) ነው፡፡ ቀላል አይሆንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ጠንካራ ተወዳዳሪ ይሆናል ብለን ነው ያሰብነው፡፡ እነሱ ለማሸነፍ ነው ሜዳ የሚገቡት፡፡ የኛም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ጥሩ ጨዋታ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለው፡፡” ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *