​ሴካፋ 2017: ኢትዮጵያ በ15 አመት ውስጥ ትልቁን ሽንፈት በቡሩንዲ አስተናግዳለች

በኬንያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታ ቡሩንዲ በአሳማኝ ሁኔታ ኢትዮጵያን 4-1 በማሸነፍ የምድቡን የበላይነት ጨብጣለች፡፡ ዋሊያዎቹ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በቡሩንዲ ተበልጠው ሶስት ሙሉ ነጥብን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድረገው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት፡፡ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው አዲስ ግደይ በሄኖክ አዱኛ ሲተካ ተመስገን ካስትሮ ለመጀመሪያ ግዜ ለብሄራዊ ቡደን ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡ ተመስገን ከግርማ በቀለ ጋር በመሃል ተከላካይነት ሲጣመር ቴዎድሬስ በቀለ ተጠባባቂ ሆኗል፡፡ 4-1-2-3 ቅርፅ ኢትዮጵያ ቡሩንዲን የገጠመች ሲሆን ቡሩንዲ የፊስተን አብዱልራዛቅ አለመኖርን ተከትሎ ላውዲት ማቩጎን በብቸኛ አጥቂነት ተጠቅማለች፡፡ ላውዲት ማቩጎን በማጥቃቱ እንዲያግዙት ከኃላው ሁለት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ሙሳ ሄሪማና እና ሻሲሪ ናሂማናን አሰልጣኝ ኒዩንጊኮ ኦሊቨር ተጠቅመዋል፡፡ በተለይ ሻሲሪ የተዳከመውን የኢትዮጵያን የመከላከል አደረጃጀት በማፈራረስ ሃገሩ ድል እንድትቀዳጅ ስኬታማ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡

የጨዋታው እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦች ተስተናግደውበታል፡፡ ኢትዮጵያ በጨዋታው ጅማሮ ላይ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት ስታደርግ ቡሩንዲ በበኩሏ በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ስትችል ታይቷል፡፡ ዋሊያዎቹ በተለይም በቀኝ መስመር የሚነሱ ኳሶች ዋነኛ የማጥቃት ምንጫቸው ቢሆንም አልፎ አልፎ ከመስመር የሚሻገሩት ኳሶችን እና ከመሃል የሚላኩት ረጅም ኳሶች በቀላሉ የቡሩንዲ ተካላከዮች እጅ እየገባ ለብሩንዲ የመልሶ ማጥቃት አመቺ አንዲሆን አስችሏል፡፡

በሰባተኛው ደቂቃ ማቩጎ ከመሃል ለብቻው ያገኘውን ኳስ ይዞ ወደ አደጋ ክልሉ ቢገባም እድሉን ከመጠቀሙ በፊት ተመስገን ደርሶ አስጥሎታል፡፡ ከደቂቃ በኃላ ሄኖክ አዱኛ ያሻገረው ኳስ አቤል ያለው በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም ሳይሳካለት ኳሷን የቡሩንዲ ተከላካዮች አውጥተውታል፡፡ በዘጠነኛው ደቂቃ ሄሪማና በማይታመን መልኩ በግቡ አፋፍ ያገኘውን ያለቀለት ኳስ ሳይጠበቅ ወደ ሰማይ ሰዶታል፡፡

በ24ኛው ደቂቃ አብዱልራህማን ሙባረክ ከርቀት የመታው ጠንካራ ምት ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ሲወጣ ከስድስት ደቂቃዎች በኃላ ከ17 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ፒየር ክዊዜራ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ቡሩንዲን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ቅጣት ምቱ የተሰጠበት መንገድ ኬንያዊው የመሃል ዳኛ አንቶኒ ኦግዋዮን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነበር፡፡

ዋሊያዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና መፍጠራቸው ወደ ግብ በተደጋጋሚ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል፡፡ ቡድኖቹ ለእረፍት ከማምራታቸው በፊትም ዳዋ ሆጤሳ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚል የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ዳዋ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱ ግን ልክ እንደቡሩንዲ ቅጣት ምት ውሳኔው አጠያያቂ ነበር፡፡

ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ ኦሊቨር በተደጋጋሚ ጥፋት ሲሰራ የነበረው ሙሳ ሄሪማናን በሴድሪክ ኡራሴንጋ በመቀየር የቡድናቸው ውጤት ማማር ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ ቡሩንዲ ከእረፍት መልስ ከመከላካል ይልቅ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰዳቸውም ግቦችን እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የግራ መስመር በኡራሴንጋ አማካኝነት የሚጀመሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ቡሩንዲ ፍፁም የሆነ ብልጫን ኢትዮጵያ ላይ ስትወስድ ዋሊያዎቹ ለብልጫው አፀፋውን የሚመልስ እቅድ አለመያዛቸው ይበልጥ በጨዋታው እንዲዳከሙ አድርጓቸዋል፡፡ በ52ኛው ደቂቃ ታሪክ ጌትነት ስህተት ቢሰራም አጠገቡ የተገኘው አበባው ኳሷን ወደ ውጪ ሲያወጣት ከደቂቃ በኃላ ኡራሴንጋ ከመስመር ያሻገረው ኳስ የታሪክ ስህተት ታክሎበት ወደ ግብነት ተቀይሯል፡፡ በዚህ ግብ የተቃቁት ቡሩንዲዎች ኢትዮጵያ በፍጥነት፣ ጉልበት እና የኳስ ቁጥጥር በመብለጥ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ናሂማና ግልፅ የማስቆጠር እድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ሲቀር በቀኝ መስመር የኢትዮጵያ ተከላካዮችን ሲረብሽ ያመሸው ሁሴን ሻባን ያለቀለት እድልን አምክኗል፡፡ በቡኩንጉ የተገኘው ደጋፊም በቡሩንዲ ተጫዋቾች ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴ ድጋፉን እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡

በ67ኛው ደቂቃ በሁለተኛው 45 ፈፅሞ ተዳክሞ የታየው ሄኖክ አዱኛ ሻባን ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ማቩጎ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል፡፡ በ73ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ልዩነቱን የማጥበብ እድል አግኝቶ ግብ ጠባቂው ጆናታን ናሂማና ሲያመክንበት በ75ኛው ደቂቃ አሁንም ሻባን በግንባሩ በመግጨት በቀላሉ ማስቆጠር የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።  በ77ኛው ደቂቃ ናሂማና በሳጥኑ ውስጥ ሻባን ያቀበለውን ኳስ በአግባቡ ተጠቅሞ የቡሩንዲን የግብ መጠን 4 አድርሷል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አሰልጣኝ አሸናፊ ሄኖክን በአበበ ጥላሁን በመቀየር ተመስገንን ከመሃል ተከላካይነት ወደ መስመር ተከላካይነት በመቀየር የኃላ መስመሩን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ውጤቱን ማጥበብ ሳይችሉ በቡሩንዲ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ኢትዮጵያ የዛሬ 15 አመት በታንዛንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የ2002 ሴካፋ ዋንጫ በዩጋንዳ 3-0 ከተረታች በኋላ በውድድሩ በ3 የግብ ልዩነት ስትሸነፍ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ቡሩንዲ ኢትዮጵያ ላይ ጫፋጭ የሆነ ድል በማስመዝገብ ምድቡን በአራት ነጥብ እና ሶስት ንፁ ግብ ሰትመራ ኢትዮጵያ በሶስት ነጥብ እና ያለምንም ግብ ሁለተኛ ነች፡፡ ነገ በዚሁ ምድብ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ይጫወታሉ፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *