​የእለቱ ዜናዎች | ሀሙስ ህዳር 28 ቀን 2010

አስመራጭ ኮሚቴ

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ በውዝግብ መታመሱን ቀጥሏል። ትናንት በነበረው ዘገባችን ዘጠኝ አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ለሦስት ቀን ባደረገው ስብሰባ በልዩነት ፣ በድምፅ ብልጫ እና አስገራሚ የሆኑ የህግ አተገባበር ክፍተት ተጨምሮበት መጠናቀቁን ገልፀን ነበር። በይበልጥ በቀጣዩ  ሳምንት በሚጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ይስተናገዱበታል ተብሎ ይጠበቃል። ዛሬ ማምሻውን እንደተሰማው ደግሞ ሦስት አባለት በሚገኙበት የይግባኝ ሰሚ (አቤቱታ ሰሚ) ኮሚቴ አንዱ ተወካይ ባልተገኘበት ስብሰባውን ቢጀምሩም ምክንያቱ ባልታወቀ ጉዳይ ስብሰባውን አቋርጠው እንደወጡ እየተነገረ ይገኛል። ታህሳስ 16 በአፋር ክልል ሰመራ ላይ ከሚደረገው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ በፊት ከወዲሁ ልዩነቶች እየተንፀባረቁ መምጣታቸው ምርጫው ነፃ ፣ ታአማኒነት ያለው እና ገለልተኛ የመሆኑን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል።


የስፖርታዊ ጨዋነት የምክክር መድረክ 

እሁድ 10:00 ላይ ከሚደረገው ከኢትዮዽያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሸገር ደርቢ ጨዋታ በፊት የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ያሳሰባቸው የሁለቱ ክለቦች አመራሮች እና ደጋፊዎች ዛሬ በኢትዮዽያ ሆቴል ከ04:00 ጀምሮ የምክክር ጉባኤ አካሂደዋል። ጉባኤውን በዋናነት ያዘጋጁት የየክለቦቹ አመራሮች እንደተናገሩት ከሆነ ይህን የውይይት መድረክ ከማዘጋጀታቸው በፊት የእግርኳሱ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሰል መድረኮችን እንዲያዘጋጅ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢያስገቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። ውይይቱ በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን አንደኛው የእሁዱ ጨዋታ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምን መደረግ አለበት የሚል ነው። ሌላው በዘላቂነት በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ተከታታይነት ያላቸው መድረኮችን ስለመፍጠር ነው። በየሜዳው የሚፈጠረው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሮች ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ከመድረኩም ሆነ ከተሳታፊዎች በስፋት የተነሳ ሲሆን የክለቦቹ አመራሮች እና ደጋፊዎች ለእሁዱ ጨዋታም ሆነ በቀጣይነቱም ላይ አብረው ሊሰሩ እንደሚገባ በመነጋገር ጉባኤው ፍፃሜውን አግኝቷል። ከውይይቱ ባሻገር የብዙ የስፖርት ቤተሰብ ጥያቄ የሆነው መሬት ላይ ወርዶ በተግባር እንዲታይ መሰራት ይኖርበታል። የእግርኳስ ሜዳዎች ለህፃናት ፣ ሴቶች ፣ አካል ጉዳተኞች እና አዛውንቶች አመቺ እና ሰላማዊ መዝናኛ እንዲሆኑ መሰራትም አለባቸው ተብሏል።


የፌዴሬሽኑ መግለጫ

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለስፖርታዊ ጨዋነት ትኩረት እንዲሰጥ በጥብቅ ባሳሰበበት መግለጫው በ5ኛ ሳምንት ወልድያ ላይ ወልድያ ከመቐለ ከተማ ሊያደርጉት ከነበረው ጨዋታ በፊት በተፈጠረ ረብሻ ፌዴሬሽኑ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት በእጅጉ እንዳዘነ ገልጿል። ለጨዋታው መቋረጥ ምክንያት የሆነውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልንም በእጅጉ እንደሚያወግዝ አስታውቋል። በዕለቱ ለደረሰው ጉዳት የመንግስት አካላት ጉዳዩን በማጣራት ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ በማመመን ፌዴሬሽኑ ለሚያደርጋቸው ውድድሮች ሁሉ የክለቦች አመራሮች እና ደጋፊዎች ለስፖርታዊ ጨዋነት መከበር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልክቱን አስተላልፏል።


የዳኞች የአካል ብቃት ፈተና

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ስታድየም በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ለሚያጫውቱ ዳኞች ብቻ ሲሰጥ የቆየው የአካል ብቃት ፈተና ዛሬ ተጠናቋል። አብዛኛዎቹ ማለት በሚያስችል መልኩ የአካል ብቃት ፈተናውን ማለፋቸው ሲገለፅ ሌሎች ፈተናውን ያልወሰዱ የፕሪምየር ሊግ ዳኞች ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚወስዱ ሰምተናል። ዳኞቹ የሁለት ቀኑን ፈተና ሳይወስዱ እንዲያጫውቱ ይመደባሉ ወይስ አይመደቡም የሚለው ጉዳይ ወደ ፊት የሚታወቅ ይሆናል።


የሸገር ደርቢ

እሁድ 10:00 ላይ በአአ ስታድየም በኢትዮዽያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የሚካሄደውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ የሚመሩት ዳኞች ተለይተው ታውቀዋል። በወቅቱ በካፍ እና ፊፋ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ የመዳኘት ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት እንዲመራው ሲመረጥ የእርሱ ረዳት በመሆን የሚያገለግሉት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንፈ ይልማ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል መሆናቸው ታውቋል።


*ጥቆማ

ሰናይ መስማት የተሳናቸው የእግርኳስ ክለብ ከኢትዮዽያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 አመት በታች የወንዶች ቡድን ጋር እሁድ ከሸገር ደርቢ ጨዋታ አስቀድሞ የወዳጅነት ጨዋታ ሊካሄድ እንደሆነ ሰምተናል። በኢትዮዽያ እግርኳስ ታሪክ የመጀመርያ እንደሆነ የሚነገርለት ሰናይ መስማት የተሳናቸው የእግርኳስ ክለብ ከዚህ ቀደም ከካናዳ እና ከደቡብ ኮርያ ከመጡ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጉ ይታወቃል።


የመፅሀፍ ምርቃት

“ስፖርታዊ ስነ ምግባር ” በሚል ርዕስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስራ አስኪያጅ በሆኑት አቶ ሰለሞን በቀለ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዳሜ ህዳር 30 ከ03:30 ጀምሮ በሸራተን አዲስ ሰሜን አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ የሚመረቅ ይሆናል።


1ኛ ሊግ ውድድር

65 ክለቦች በአምስት ምድብ ተከፍለው የሚወዳደሩበት የኢትዮዽያ 1ኛ ሊግ ውድድር ባልተሟላ መልኩ በተወሰኑ ቡድኖች መካከል በሚደረጉ  ጨዋታዎች ታህሳስ 1 ቀን እንደሚጀምር ሰምተናል። ጨዋታዎቹ ባልተሟላ ሁኔታ የሚካሄዱት ክለቦች አስቀድመው የዳኞች እና የታዛቢዎችን ክፍያ ከፍለው ባለማጠናቀቃቸው ምክንያት እንደሆነ ታዉቋል።


የአዲስ አበባ ስታድየም

እድሜ ጠገቡ  የአዲስ አበባ ስታድየም እድሜው ገፍቶ እርጅና ቢጫጫነውም አሁንም በብቸኝነት ትልልቅ ውድድሮችን እያስተናገደ ይገኛል።  በስታድየሙ ከሚገኙና በእድሜ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ካቆሙ ቁሳቁሶች መሀል አንዱ የሆነው የድምፅ ማጉያ ስራውን እንዲጀምር በማሰብ የእድሳትና የመሳርያ ለውጥ ተደርጎለት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *