​አሰልጣኝ አብርሀም ተክለኃይማኖት የታዳጊዎች እግርኳስ ትምህርት ቤት ሊከፍቱ ነው

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም ተክለኃይማኖት በያዝነው ዓመት በመቐለ የእግርኳስ ትምህርት ቤት ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

እንደ አብርሃም ተ/ሃይማኖት ገለፃ ከሆነ ትምህርት ቤቱ የታሰበው ልክ እንደ ቀለም ትምህርት ካሪኩለም ተቀርጾለት በክፍል ውስጥ እና በተግባር ስልጠና በመስጠት ተጫዋቾችን ማብቃት ነው። ” በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ያለው የስልጠና አሰጣጥ ስርአት በስልጠና ላይ ሳይሆን በውድድሮች ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ እኛም ይህንን ለመቀየር ብሎም በታክቲክ አረዳድ እና በቴክኒክ የዳበሩ ተጫዋቾች በመፍጠር ከሌላው አለም ተወዳዳሪ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለመቅረፅ በዝግጅት ላይ ነን። ” ሲሉ አክለዋል።

በቀጣይ ከመቐለው ትምህርት ቤት ባለፈ በሙሉ ትግራይ ክልል ፕሮጀክቱን በማስፋፋት በ52 የትግራይ ክልል ወረዳዎች 5000 ህፃናትን አቅፎ ለመሥራት የ5 አመት እቅድ መውጣቱን የገለፁ ሲሆን ለዚህ ፕሮጀክት የሚውል 30 ሚልዮን ብር ድጋፍ ከትግራይ ክልል ጠይቀው መልሱን በመጠባበቅ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ኢ/ር አብርሀም ተክለኃይማኖት ከ1990ዎቹ መጀመርያ አንስቶ በጉና ንግድ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ መተሀራ ስኳር ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ደደቢት በአሰልጣኝት የሰሩ ሲሆን ከ5 አመት ወዲህ የታዳጊዎች እግርኳስ ስልጠናዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *