​ሴካፋ 2017፡ ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ነጥብ ተጋርታ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ እድሏን አጨልማለች

በኬንያ አዘጋጅነት እየተደረገ ባለው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታ በካካሜጋ ዩጋንዳን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን አጠናቅቋል፡፡ ቡኩንጉ ስታዲየም ላይ በተደረገ ጨዋታ ዋሊያዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም በሁለተኛው 45 መከላከልን ብቻ መሰረት አድርገው መጫወታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡሩንዲን ከገጠመው ቡድን ውስጥ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ ታሪክ ጌትነትን ተክቶ በብሄራዊ ቡድን መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ ሲያደርግ አበበ ጥላሁን፣ ፍሬው ሰለሞን፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና ጉዳት ላይ የነበረው ቴዎድሮስ በቀለ ሌሎች ወደ መጀመርያው አሰላለፍ የተካተቱ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢስተናገድም በተለይ ኢትዮጵያ በአዝጋሚ የመከላከል ሽግግር ምክንያት ተጋላጭ የሆኑት ሁለቱ የዩጋንዳ የመስመር ተከላካዮችን ጫና ውስጥ ሲከቱ እና የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ ይህም እንቅስቃሴ ዋሊያዎቹን ስኬታማ ከማድረግ ባለፈ ግብ በማስቆጠረም ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡

ጨዋታው በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ በሴካፋው ውድድር ለኢትዮጵያ ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ብሩክ ቃልቦሬ ከመሃል ያሻገረውን ኳስ አቤል ያለው ተቆጣጥሮ በመውጣት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ኢስማኤል ዋቴንጋ አናት ላይ ቢያሳልፍም ኳስ ኢላማውን ባለመጠበቋ ግብ መሆን አልቻለችም፡፡ በአምስተኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር የተሰጠውን ቅጣት ምት የዋሊያዎቹ አምበል አበባው ቡታቆ መቶ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል፡፡ ኢትዮጵያ በጨዋታው ላይ ዩጋንዳ ላይ ጫና በማሳደር በ22ኛው ደቂቃ በአቡበከር ሳኒ ግብ ቀዳሚ መሆን ችላለች፡፡ በቀኝ መስመር ተመስገን ካስትሮ አይዛክ ሙሌሚን በማለፍ ወደ አደጋ ክልሉ ያሻገረውን ኳስ ዳዋ ሆጤሳ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ቢመልስበትም በቅርብ ርቀት የነበረው አቡበከር ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ዋሊያዎቹን መሪ አድርጓል፡፡

በግቡ የተነቃቁት ዋሊያዎቹ የግቡ ሙከራ ማድረጋቸውን በመቀጠል ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ዳዋ ከርቀት የመታውን ጠንካራ ምት ዋቴንጋ ሲተፋው አቤል ተቀብሎ ቢያስቆጥርም ኬንያዊው አርቢትር ጥፋት ተሰርቷል በሚል ግቧን ሳያፀድቁ ቀርተዋል፡፡ ይህም በዋሊያዎቹ የቡድን አባላት ላይ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ በ27ኛው ደቂቃ ክሬንሶቹ በተከላካይ አማካዩ ታዲዮ ሉዋንጋ አቻ የመሆን እድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ዩጋንዳ በረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ለአጥቂዎቻቸው በተለይም ለሁድ ካዌሳ ለማድረስ ቢሞክሩም ጥሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ተከላካዮችን ግን ማለፍ አልቻሉም ነበር፡፡

በሁለተኛው 45 የዩጋንዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና በርካታ የማስጠንቂቂያ ካርዶች የተመዘዙበት ነበር፡፡ በተለይ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ሁለት የዩጋንዳ ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል፡፡ ሚልተን ካሪሳ በ46ኛው ደቂቃ የሞከረውን ሙከራ ተክለማሪም በግሩም ሁኔታ አምክኖበታል፡፡ ዩጋንዳዎች በወሰዱት ብልጫ በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው መጫወት ሲቀጥሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ በመከላከል ተጠምዷል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ ካሪሳ አሁንም የሞከረውን ኳስ ተክለማርያም ሲያመክንበት ከሶስት ደቂቃ በኃላ ሙሌሚ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ሆኖም የቁጥር ብልጫው ዋሊያዎቹን ነጥብ ከመጋራት አላዳናቸውም። በ86ኛው ደቂቃ ዴሪክ ንሲምባቢ ተክለማሪም በአግባቡ ማውጣት ያልቻለውን ኳስ ተጠቅሞ ዩጋንዳን አቻ አድርጓል፡፡

ዋሊያዎቹ ዳግም ወደ ጨዋታው ለመመለስ እና ለማሸነፍ ያልተሳኩ ሁለት ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ አበባው ያሻገረውን ቅጣት ምት አበበ ቢሞክርም የዩጋንዳ ተከላካዮች ከመስመር ላይ ሲያወጣበት ዳዋ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አናት ወጥቷል፡፡ ቲሞቲ አዎኒ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ በቀይ ሲሰናበት ዩጋንዳዎች የአቻ ውጤቱን አስጠብቀው በመውጣት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማምራታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ አባላት በውጤቱ በመከፋት በተለይም በመጀመሪያው 45 ያልፀደቀችው ግብ አግባብ አይደለም በሚል የጨዋታው አርቢትሮች ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከምድብ መሰናበቷ ገና ያለየለት ሲሆን ደቡብ ሱዳን ቡሩንዲን ከ3-0 በላይ ካሸነፈች ዋሊያዎቹ ለግማሽ ፍፃሜ ሊያመሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በሁለት ጨዋታ ስምንት ግብ ያስተናገደችው ደቡብ ሱዳን ቡሩንዲን የማሸነፍ እድሏ ካላቸው ወቅታዊ አቋም አንፃር የጠበበ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አራት ነጥብ ይዛ ሶስተኛ ስትሆን ዩጋንዳ በአምስት ነጥብ እና ቡሩንዲ በአራት ነጥብ ምድቡን ይመራሉ፡፡ ነገ ደቡብ ሱዳን ቡሩንዲን ካካሜጋ ላይ ትገጠማለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *