​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሸገር ደርቢ ቀድሞ ከወጣለት ፕሮግራም ለውጥ ተደርጎበት ከእሁድ ወደ ማክሰኞ ተዘዋውሯል። በዚህም መሰረት ነገ 11፡00 ላይ ጨዋታው እንደሚደረግ እየተጠበቀ ሲገኝ ሶከር ኢትዮጵያም በቅድመ ጨዋታ ዳሰሳዋ ተጠባቂውን ፍልሚያ እንደሚከተለው ተመልክታዋለች።


ቦታ | አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን | ሰኞ ታህሳስ 02 2010

ሰዐት | 11፡00

ዳኞች

ዋና ዳኛ – በአምላክ ተሰማ

ረዳት ዳኞች – ክንፈ ይልማ እና ተመስገን ሳሙኤል


የቅርብ ጊዜ ውጤቶች

ኢትዮጵያ ቡና | ተሸ-አሸ-አቻ-አሸ

ቅዱስ ጊዮርጊስ | አሸ- አሸ-አቻ


በሳምንቱ መጨረሻ የተደረጉ ጨዋታዎችን ውጤት ጨምሮ ሁለቱ ቡድኖች ነገ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ በዕኩል ሰባት ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስት ጨዋታዎችን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5ኛ እንዲሁም አራት ጨዋታዎችን ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን በማሸነፉ እና አንዱን አቻ በመለያየቱ የሰበሰባቸው ነጥቦች ብዛት በአማካይ ሲሰላ ከየትኛውም የሊጉ ክለብ በላይ ያስቀምጠዋል። ኢትዮጵያ ቡናም በመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ጨዋታዎቹ ተመሳሳይ ስኬት የነበረው ቢሆንም ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ያደረገውን ጨዋታ መሸነፉ በአማካይም ሆነ በድምር ነጥብ ብዛት የሊጉ የበላይ ሆኖ ደርቢውን የመጠበቅ ዕድሉን አጥቷል። አምና 8ኛ ሳምንት ላይ በሊጉ በተገናኙበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በኢኮ ፌቨር ብቸኛ ግብ ሲያሸንፍ ውጤቱ ለክለቡ በውድድር ዘመኑ የተገኘ ሁለተኛ ድል ለቅድስ ጊዮርጊስ ደግሞ የአመቱ ሁለተኛ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቦ ነበር። ዘንድሮስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስተኛ ተከታታይ ድል ያስመዘግባል ወይስ ኢትዮጽያ ቡና ወልዋሎ ላይ ካስተናገደው ሽንፈት በኃላ ወደማሸነፍ ይመለሳል አልያም ሁለቱም በአመቱ ለሁለተኛ ጊዜ የአቻ ውጤትን ይዘው ይወጣሉ የሚለው ጥያቄ ነገ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።


በጨዋታው ምን ይጠበቃል ?

እስካሁን በተደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱም ቡድኖች በየራሳቸው መንገድ ሽግግር ላይ እንደሆኑ መናገር ይቻላል። ክለቦቹ በአዲስ አሰልጣኞች አመቱን መጀመራቸው በፊት ከነበራቸው የጨዋታ አቀራረብ እና የተጨዋቾች አጠቃቀም ላይ ለውጦችን እንዲያደርጉ አድርጓል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ቫስ ፒኒቶ ይዘውት የመጡት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት በሂደት ባለፉት ጊዚያት በአመዛኙ በቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ የተመሰረተውን የክለቡን አጨዋወት እስከ ወዲያኛው የመቀየር ሀሳብ ያለው ይመስላል። አመቱን ኢትዮጵያ ቡናን ይዘው የጀመሩት አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒችም የቡድኑን አጨዋወት ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር ያሰቡ ባይመስሉም ቡድኑ ከዚህ ይጠቀማቸው ከነበሩ አሰላለፎች በተለየ የ4-4-2 ዳይመንድ ተጠቃሚ መሆናቸው ቡና ራሱን በአጨዋወት ለውጥ ውስጥ እንዲያገኘው ያደረገ ነበር።

በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ያለፉት ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በውጤት ረገድ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ የሚባል ጊዜን እያሳለፉ ቢሆንም ለውጦቹ በሚፈለገው መጠን እየታዩ ነው ለማለት ግን ጊዜው ገና ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በየጨዋታው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ ለመሆን ሲሞክር እና ዕድሎችንም በዚሁ መንገድ ለማግኘት ሲጥር ቢታይም እስካሁን የተገኙት የቡድኑ ጎሎች እና አስፈሪ ሙከራዎች በብዛት ከቀጥተኛ አጨዋወት የሚገኙ ናቸው። ቡድኑ የሚይዘው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትም ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ዘልቆ የሚገባ እና ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ዋነኛ የሙከራ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ጊዜ እንደሚያስፈልገው መናገር ይቻላል። ሆኖም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአመታት የገነባው የአሸናፊነት ስነልቦና ጥቂት ዕድሎችን ቢያገኝም እና ቀድሞ ግብ አስተናግዶ በተጋጣሚዎች ቢፈተንም ውጤት ይዞ ከመውጣት ግን አልተገታም። ለዚህ ከመቐለ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጋር የተደረጉትን ጨዋታዎች ምሳሌ አድርጎ ማንሳት ይቻላል። ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስንመጣ የአሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች በጊዜ ከቡድኑ መለየት ብዙ ክፍተት ቢኖርበትም ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ  ከቅርፅ ለውጡ ጋር እየተላመደ የነበረውን ቡድን ትልቅ ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው። ለአብነት በ4-4-2 ዳይመንድ ትግበራ ወቅት ወሳኝ ናቸው ተብለው ከሚታሰት ሀሳቦች መሀከል የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ወሳኝ ከሆኑት የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ እና ለቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ከሆነው በዳይመንዱ ጫፍ ላይ ከሚገኘው ተጨዋች የቦታ አጠባበቅ ጋር ተያይዞ አሰልጣኙ በነበሩባቸው ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ የተሻሉ ለውጦችን ሲያሳይ መቆየቱን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም ሂደትም በቀደሙት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና እስከተጋጣሚው ሳጥን ድረስ በመዝለቅ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ዕድገት እያሳየ መጥቶ በወልዋሎው ጨዋታ ላይ እጅግ ተዳክሞ መታየቱ የአሰልጣኙ ከዚህ በኃላ አለመኖር ተፅዕኖው ቀላል እንደማይሆን ያሳየ ነበር።

በዚህ መልኩ ቡድኖቹ ነገ በሜዳ ላይ ሲገናኙ የምጠበቁ ነጥቦችን ስንመለከት ደግሞ በዋነኛነት አማካይ ክፍል ላይ ከሚኖረውን ፍልሚያ ማነሳት ይኖርብናል። በብዛት ሶስት አማካዮችን የሚጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ  ወደመሀል ከጠበበው የኢትዮጵያ ቡና የዳይመንድ አማካይ ክፍል ጋር ሲገናኝ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለማግኘት ብዙ በማጥቃት ላይ ከማይሳተፉት የመስመር ተከላካዮቹ እና በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ጊዚያቸውን ከሚያሳልፉት የመስመር አጥቂዎቹ ሊያገኝ የሚገባው እገዛ ወሳኝ ይሆናል። ኢትዮጵያ ቡናም በያዘው አጨዋወት በማጥቃት ሂደት ላይ በሚሆንበት ወቅት የመስመር ተከላካዮቹን እርዳታ የማግኘት ግዴታ ቢኖርበትም በሁለቱ መስመሮች አስራት ቱንጆ እና አስናቀ ሞገስ በሜዳው ቁመት እስከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክልል ድረስ ሊኖራቸው የሚገባው ፈጣን እንቅስቃሴ ከቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ኢብራሂማ ፎፋና እና ጋዲሳ መብራቴ ወደጎን የተለጠጠ የቦታ አያያዝ ጋር ሲገናኝ ምን ያህል ስኬታማ ይሆናል የሚለው በጨዋታው ተጠባቂ ነጥብ ነው። ሌላው የዳይመንዱ ጫፍ ላይ የሚሰለፈው ኤልያስ ማሞ ከሙሉአለም መስፍን ጀርባ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ መስመር ሊኖረው የሚገባው ቦታ አያያዝ ላይ የሁለቱ የፊት አጥቂዎች የጎንዮሽ እንቅስቃሴ የሚኖረው አስተዋፅዖ በሳላዲን ባርጌችም ከሚመራው ከፈረሰኞቹ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ጋር ሲገናኝ ማን የበላይ ይሆናል የሚለውም የጨዋታውን ውጤት የሚወስን ይሆናል። በተቃራኒው የቅዱስ ጊዮርጊስን የፊት መስመር የሚመራው አሜ መሀመድ ከተጋጣሚው የመሀል ተከላካዮች ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ እንዲሁም የአብዱል ከሪም ኒኪማ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ከ አክሊሉ ዋለልኝ ጋር የሚገናኝባቸው የጨዋታ ሂደቶችም ተጠባቂ ናቸው።


የእርስ በእርስ ግንኙነት ሪኮርድ (1991-2009)

ተገናኙ – 36

ኢትዮጵያ ቡና አሸነፈ – 6 (24 ጎል)

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸነፈ – 17 (48 ጎል)

አቻ – 13


የቡድን ዜናዎች

የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አበባው ቡጣቆ እና አቡበከር ሳኒ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናው ሳምሶን ጥላሁን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ኬንያ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ዋልያዎቹ በሴካፋ ያላቸው ቆይታ የተገባደደ የመምሰሉ ጉዳይ ተጨዋቾቹ ለነገው ጨዋታ ወደ ክለባቸው ይመለሱ ይሆን ? የሚል ጥያቄን አስነስቷል። በጉዳት በኩል ሳልሀዲን ሰይድ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ለአለም ብርሀኑ እና ታደለ መንገሻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ክሪዚስቶም ንታንቢ እና መስዑድ መሀመድ ከኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው ላይ የማይገኙ ይሆናል። እዚህ ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚነሳው መልካም ዜና የደጉ ደበበ እና አስቻለው ግርማ ወደ ሜዳ መመለስ ነው።


ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ♦)

ሀሪሰን ሄሱ

አስራት ቱንጆ – ቶማስ ስምረቱ – አክሊሉ አየነው – አስናቀ ሞገስ

እያሱ ታምሩ – አክሊሉ ዋለልኝ – ኤልያስ ማሞ – አማኑኤል ዮሃንስ

ሳሙኤል ሳኑሚ – በረከት ይስሀቅ


ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

አብዱልከሪም መሀመድ – ሳላዲን ባርጌቾ – አስቻለው ታመነ – መሀሪ መና

ምንተስኖት አዳነ – ሙሉአለም መስፍን – አብዱልከሪም ኒኪማ

ጋዲሳ መብራቴ – አሜ መሀመድ – ኢብራሂማ ፎፋና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *