​ሴካፋ 2017፡ ዛንዚባር ሳትጠበቅ ከ22 ዓመታት በኋላ ለፍፃሜ ደርሳለች

በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ዛሬ ሲታወቁ የውድድሩ ክስተት የሆነችው ዛንዚባር ዩጋንዳን 2-1 በማሸነፍ እሁድ ለሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ አዘጋጇን ኬንያን ለመግጠም ቀርባለች፡፡ ዛንዚባር የውድድሩን የሪከርድ አሸናፊ እና የወቅቱ ቻምፒዮን ዩጋንዳን ነው ኪሲሙ ላይ መርታት የቻለችው፡፡

ዛንዚባር በአብዱልአዚዝ ማካሜ የ23ኛ ደቂቃ ግብ መሪ ስትሆን ዩጋንዳ በውድድሩ ጥሩ ግዜ ባላለፈው ድሪክ ንስምባቢ ግብ በ29ኛው ግብ አቻ አድርጋለች፡፡ ሙዳጢር ያያ ያሻገረውን የማዕዘን ምት የክሬንሶቹ ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ ነበር ማካሜ በቀላሉ ዛንዚባርን 1-0 መሪ ያደረገው፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር ባስተናገደው ጨዋታ ዩጋንዳ ንስምባቢ ከመስመር ሆኖ ባስቆጠረው ግብ ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ዩጋንዳ ጆሴፍ ናሱቡጋ በአደጋ ክልል ውስጥ በሰራው ጥፋት በ56ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት መሃመድ ኢሳ ወደ ግብነት ቀይሮ ዛንዚባርን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ የቁጥር ብልጫ ያገኙት ዛንዚባሮች መሪነታችው በማስጠበቅ ከ22 ዓመት በኃላ ለፍፃሜ ደርሳለች፡፡ በሁለት ጨዋታ ብቻ ሶስት የቀይ ካርዶች የተመዘዘቡት የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ለዋንጫ የተጠበቀ የነበረ ቢሆንም በአቋም መውረድ የሳሳው የተከላካይ ክፍሉ እና የአሰልጣኝ ሞሰስ ባሴና የታክቲክ ስህተቶች ቡድኑ የዋንጫ ክብሩን እንዳያስጠበቅ አድርጎታል፡፡ ዛንዚባር በ1995 ዩጋንዳን በፍፀሜው አሸንፋ ዋንጫ ካነሳች በኃላ በተደጋጋሚ በተሳተፈችበት የሴካፋ ዋንጫ ከምድብ በፍጥነት በመሰናበት የምትታወቅ ነበረች፡፡

የአንድ ግዜ የሴካፋ ቻምፒዮኗ ዛንዚባር እሁድ ማቻኮስ ላይ ኬንያን በፍፃሜ ስትገጥም ለደረጃ ቡሩንዲ እና ዩጋንዳ ይገናኛሉ፡፡ ዛንዚባር እና ኬንያ እንዲሁም ቡሩንዲ እና ዩጋንዳ በተመሳሳይ በምድብ ጨዋታ ተገናኝተው ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *