​ሴካፋ 2017፡ ኬንያ ለሰባተኛ ጊዜ የሴካፋ ዋንጫን አሸንፋለች

ማቻኮስ በሚገኘው የኬንያታ ስታደዲየም በተደረገ የፍፃሜ ጨዋታ አዘጋጇ ኬንያ ዛንዚባርን በመለያ ምት 3-2 በመርታት የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫን ስታሸንፍ ቡሩንዲን የረታችው ዩጋንዳ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የነበረው ውድድርም ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ኬንያ ለሰባተኛ ግዜ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችላለች፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያዊው የፊፋ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው የመስመር ዳኛ ነበር፡፡

በፍፃሜው ጨዋታ የዛንዚባር አይበገሬነት እንዲሁም የኬንያ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ድንቅ ብቃት የታየበት ሆኗል፡፡ በመጀመሪያው 45 የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫነ የፈጠሩት ኬንያዎች በኦቬላ ኦቼንግ ግሩም ቅጣት ምት መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ሆኖም በጨዋታ እንቅስቃሴ ዛንዚባሮች በመጀመሪያው አጋማሽ ተሸለው ታይተዋል፡፡ ዛንዚባር በቅፅል ስማቸው ሂሮስ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የግብ እድሎችን በመፍጠር ደረጃ ግን የቀዘቀዙ ነበሩ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ዛንዚባር ኬንያ ላይ ፍፁም የሆነ ብልጫን ወስዳለች፡፡ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝም ለረጅም ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ሲጫወቱ ተስተውሏል፡፡ 90 ደቂቃው ከመጠናቀቁ ሶስት ደቂቃ በፊት ካሚስ ሙሳ ዛንዚባርን አቻ አድርጓል፡፡ የካሚስ ግብ ኬንያ በውድድሩ ያስተናገደችው የመጀመሪያ ግብ ነው፡፡

በተጨማሪው 90 ደቂቃ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየ ሲሆን የመከላከል ስህተቶች ተጨማሪ ሁለት ግቦችን እንዲቆጠሩ አስችሏል፡፡ መስኡድ ጁማ የዛንዘባሩ ግብ ጠባቂ መሃመድ አቡዱልራህማን የተሳሳተ የመልስ ምትን ተጠቅሞ በ97ኛው ደቂቃ ኬንያን ዳግም መሪ ሲያደርግ ከሶስት ደቂቃ በኃላ ካሚስ ሙሳ በጨዋታው ሁለተኛውን እንዲሁም የዛንዚባርን የአቻነት ግብ የኬንያ ተከላካዮች ስህተትን ተከትሎ አስቆጥሯል፡፡

አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት አምርተው ኬንያ 3-2 አሸንፋለች፡፡ የኬንያው ግብ ጠባቂ ፖትሪክ ማታሲ ሶስት የመለያ ምቶችን በማምከን የጨዋታው ኮከብ ሆኗል።

ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ ዩጋንዳ ከኃላ በመነሳት ቡሩንዲን 2-1 ረታለች፡፡ ሻሲር ናሂማና የመታውን ኳስ ቅጣት ምት የዩጋንዳው ግብ ጠባቂ ቤንጃሚን ኦቻን ከእጁ ላይ አምልጦት ቡሩንዲ የመጀመሪያውን አጋማሽ መምራት ችላለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ሳዳም ጁማ በ49 እና 76ኛው ደቂቃ አከታትሎ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ዩጋንዳ ሶስተኛ ደረጃን ማግኘት ችላለች፡፡

የኬንያው ግብ ጠባቂ ማታሲ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እና ግብ ጠባቂ ሽልማትን ሲያሸንፍ የዩጋንዳው ዴሪክ ንስምባቢ በአራት ግቦች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኗል፡፡

በካካሜጋ ቡኩንጉ ስታዲየም፣ ማቻኮስ ኬንያታ ስታዲየም እና ኪሲሙ ሞይ ስታድየም የተደረገው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ላይ 9 ሃገራት መካፈል ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *