መሳይ ተፈሪ ከወላይታ ድቻ አሰልጣኝነታቸው ተነሱ

ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና ረዳታቸው ግዛቸው ጌታቸውን ከዋናው ቡድን አሰልጣኝነት ማሰናበቱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታወቁ፡፡

ወላይታ ድቻን ከ2001 ጀምሮ ሲያሰለጥኑ የቆዩትና አምና የጥሎ ማለፉን ዋንጫ እንዲያነሳ የረዱት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድኑ በውጤት ቀውስ ውስጥ መሆኑን ተከትሎ እንዲሰናበቱ መወሰኑን አቶ አሰፋ ገልፀዋል፡፡

ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኝ ስንብቱ በተጨማሪ ረዳት አሰልጣኙ ግዛቸው ጌታቸውን ወደ ወጣት ቡድኑ አሰልጣኝነት ወርዶ እንዲሰራ ሲወስን የቡድን መሪ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት አቶ አሰፋ ሀሊሶ በስራ አስኪያጅነት ብቻ እንዲሰሩ እንዲሁም ሐብታሙ ኃይለሚካኤል ከቴክኒክ ዳይሬክተርነታቸው ጎን ለጎን የቡድን መሪነቱን ደርበው እንዲሰሩም ተወስኗል፡፡

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከስንብቱ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በድቻ ለነበራቸው መልካም የስራ ጊዜያት ክለቡን አመስግነዋል፡፡ ‹‹ በክለቡ በነበረኝ ጊዜያት ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ለ9 አመታት በነበረኝ ረጅም ቆይታም ከቡድኑ ጋር ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ ስቀጠር እንደተደሰትኩት ሁሉ ስሰናበትም በደስታ ነው ከቡድኑ ጋር የምለያየው፡፡ ከጎኔ ለነበሩት እና ላገዙኝ የክለቡ አመራሮች እና ደጋፊዎች ሁሉ በፈጣሪ ስም አመሰግናለሁ፡፡ በቀጣይም ቡድኑ ውጤት እንዲያስመዘገብ እና ለቀጣዩ አሰልጣኝም መልካም እድል እንዲገጥመው እመኛለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ወደ ዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ተሸጋግሮ የነበረው አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ ቡድኑን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣንነት እንዲመሩ ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡ አሰልጣኝ ዘነበ የ17 አመት በታች ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሲሰሩ የቆዩ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ደለለኝ ደቻሳ ደግሞ የአሰልጣኝ ዘነበ ረዳት ሆነው እንደሚሰሩ ከክለቡ ያገገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በሊጉ በማሰልጠን ላይ ከነበሩ አሰልጣኞች መካከል ለረጅም አመት በአንድ ክለብ ቀዳሚ የነበሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስማቸው ከአርባምንጭ ከተማ ዋና አሰልጣኝነት ጋር በስፋት ተያይዞ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *