ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ደደቢት በአሸናፊነት ሲቀጥል ንግድ ባንክ እና ሲዳማ ቡናም አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ እሁድ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ ደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሲዳማ ቡና ሶስት ተጥብ ይዘው የወጡበትን ድል አስመዝግበዋል።

አአ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤሌክትሪክን ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 1-0 አሸንፏል። ጨዋታው በተጀመረ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታምነሽ ሲሳይ ከማእዘን ያሻማችውን ኳስ በመጠቀም ጥሩአንቺ መንገሻ በግንባር በመግጨት የጨዋታው ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ለመውጣት ተቸግረው በተስተዋለበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ምንም አይነት የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በአንጻሩ ንግድ ባንኮች እንደነበራቸው የጨዋታ ብልጫ የሜዳው የመጨረሻ ክፍል ላይ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ትክክል አለመሆናቸው እንጂ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር በተገባቸው ነበር፡፡ በተለይ በሁለት አጋጣሚዎች ረሂማ ዘርጋው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች ሾልካ በመውጣት ከኤሌክትሪኳ ግብ ጠባቂ ጋር 1ለ1 ተገናኝታ ያመከነቻቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ። በተመሳሳይ በ31ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው አምበሏ ረሂማ ዘርጋው ህይወት ዳንጊሶ ያሻማችውን የቅጣት ምት ገጭታ ብትሞክርም ኳሱ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወደ ውጪ ወጥቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ተጭነው ቢጫወቱም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በዚህ አጋማሽ ሌላው ለየት ያለው ክስተት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አጥቂዋ ሽታዬ ሲሳይን በቀኝ የመስመር ተከላካይነት ሲጠቀምባት መስተዋሉ ነበር።

ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ፀሃይነሽ ዱላ አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ጎሎች ባለሜዳው ሲዳማ 2-0 መምራት ሲችል ከእረፍት መልስ ቱቱ በላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጥራ ልዩነቱን ወደ አንድ አጥብባለች።

ወደ ድሬዳዋ የተጓዘው ደደቢት በ100% አሸናፊነት በመቀጠል ድሬዳዋ ከተማን 3-0 መርታት ችሏል። ሎዛ አበራ ወደ ግብ አስቆጣሪነት ስትመለስ ሰናይት ባሩዳ እና እፀገነት ብዙነህ ሌሎቹ ግበረ አስቆጣሪዎች ናቸው።

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *