​ዜና እረፍት | የኢ.እ.ፌ የመጀመሪያው የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ዲሚትሪ ስጎሎምቢስ አረፉ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሸን የመጀመሪያው የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ከነበሩት መካከል የነበሩት አቶ ዲሚትሪ ስጎሎምቢስ በተወለዱ በ99 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ስጎሎምቢስ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ ባለውለተኞች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን ኑሯቸውን ለረጅም ጊዜያት ባደረጉበት በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ ግዛት ህልፈተ ህይወታቸው ተሰምቷል፡፡

ስጎሎምቢስ በጅማ ከተማ ከግሪካዊያን ቤተሰቦች በ1911 የተወለዱ ሲሆን በኢትዮጵያ የክለብ ውድድር ሲጀመር ተሳታፊ ለነበረው የአዲስ አበባው ኦሎምፒያኮስ በክለብ ደረጃ እግርኳስ ተጫውተዋል፡፡ ስጎሎምቢስ ከእግርኳስ ከተገለሉ በኃላም ለረጅም ግዜያት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ የሰሩ ሲሆን ከ1941 – 1960ዎቹ ድረስም የፌድሬሽኑ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡ በ1958 ቱኒዚያ ባዘጋጀችው 5ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቡድን መሪ የነበሩት አቶ ዲሚትሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ፌድሬሽኑ የመተዳደሪ ደንቡን ሲያፀድቅ አባል ከነበሩ ፋና ወጊ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ዲሚትሪ ስጎሎምቢስ በእግርኳስ ብቻ ሳይወሰኑ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በ1950ዎቹ ሲቋቋም የመጀመርያው ፕሬዝደንት ፣ አንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ደግሞ ዋና ፀሃፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ስጎሎምቢስ ለረጅም ዓመታት በካሊፎርኒያ ኑሯቸው አድርገው ቆይተዋል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ በዲሚትሪ ስጎሎምቢስ ህልፈት የተሰማትን ሃዘን ትገልፃለች፡፡ ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸውም መፅናናትን ትመኛለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *