​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

በአዲስ አበባ ፣ አርባምንጭ ፣ ይርጋለም እና መቐለ የሚስተናገዱት የዛሬ የሊጉ  ጨዋታዎች በዓሉን እግር ኳሳዊ መንፈስ እንደሚያላብሱት ይጠበቃል። አምስቱን ጨዋታዎች የተመለከተው ዳሰሳችንም እንደሚከተለው ቀርቧል

መከላከያ ከ ፋሲል ከተማ

ታህሳስ ወር ከገባ በኃላ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ ከአራት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን ያሳካው መከላከያ በሶስቱ ጨዋታዎች ደግሞ መረቡን ሳያስደፍር ከሜዳ መውጣት ችሏል። ቡድኑ ሊጉን ከጀመረበት ደካማ አቋም በማገገም ላይ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ ፋሲል ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታም እስከ አራተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል የሚሰጠው ይሆናል። ሆኖም ተጋጣሚው ፋሲል ከተማን ስንመለከት ደግሞ እስካሁን ሽንፈት ካልገጠማቸው ሶስት ቡድኖች መሀከል አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን። ካላቸው 12 ነጥቦች ሰባቱን ከሜዳቸው ውጪ የሰበሰቡት ፋሲሎች ዘንድሮም በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ ያላቸውን ጥንካሬ በማሳየቱ ገፍተውበታል። ፋሲሎች በፌደራል ዳኛ ቢኒዬም ወርቅአገኘው የሚመራውን የዛሬውን ጨዋታም ማሸነፍ ከቻሉ ትላንት አዳማዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸንፈው የተቀመጡበትን የሶስተኝነት ደረጃ የሚረከቡበት ዕድል ይኖራል።

መከላከያ የረዥም ጊዜ ጉዳት ያለበትን አዲሱ ተስፋዬን ፣ አዲስ አዳጊው አብነት ይገለጡን እና ሳሙኤል ታዬን በጉዳት ሳቢያ የማይጠቀም ሲሆን ሳሙኤል ሳሊሶን ግን ከቅጣት መልስ የሚያገኝ ይሆናል። በአንፃሩ በፋሲል ከተማ በኩል በጉዳት የማይኖሩት አማካዩ ይስሀቅ መኩሪያ እና ሳምንት  ድሬደዋ ላይ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው አይናለም ኃይለ እንደሆኑ ሰምተናል።

መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደነበረው የሳምንቱ ጨዋታ ወደኃላ ያፈገፈገ አቀራረብ እንደማይኖረው ይታሰባል። የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ እና የሰሞኑ ውጤት የተሻለ የራስ መተማመን እንደሚፈጥርለት የሚጠበቀው የቡድኑ የአማካይ መስመርም በአማካይ የሚኖረው ቦታ አያያዝ ወደ ተጋጣሚው ሜዳ ያዘነበለ እና ለአጥቂዎቹ የሚቀርብ ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ ቡድኑ በ4-4-2 አሰላለፍ በሁለተኛ አጥቂነት የሚጠቀመው ተጨዋች ማራኪ ወርቁ/አቅሌሲያስ ግርማ ሚና ወሳኝ ይሆናል። ሁለቱም ተጨዋቾች ወደ መስመር አማካዮቹ በመቅረብ እና ኳሶችን በመቀበል ለምንይሉ ወንድሙ ለማድረስ የሚሞክሩበት መንገድ ምንይሉ ቡድኑ ጥሩ በሆነባቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን እንዲያስቆጥር ትልቅ እገዛ ነበራቸው። ከሜዳቸው ውጪ መሀል ሜዳ ላይ በኳስ ቁጥጥር ብዙ ጊዜ የማያጠፉት ፋሲሎች ደግሞ በፈጣን ሽግግር ከአማካዮቻቸው በ4-3-3 ከፊት በግራ እና በቀኝ ወደሚገኙት መስመር አጥቂዎቻቸው በሚላኩ ኳሶች ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። በዚህ በኩል የዳዊት እስጢፋኖስ መኖር የመጨረሻ ኳሶችን በማድረሱ በኩል ወሳኝ ሲሆን የመስመር አጥቂዎቹ ለተጋጣሚ ሜዳ የቀረበ አቋቋምም ለመልሶ ማጥቃቱ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። ሆኖም መከላከያዎች ሊያገኙት ከሚችሉት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር አንፃር የፋሲል መስመር አጥቂዎች የመከላከል ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ጨዋታውን የመወሰን አቅም የሚኖራቸው እንቅስቃሴዎችም ከመከላከያዎች የመስመር አማካዮች እና ከፋሲሎች የአጥቂ አማካዮች በሚነሱ ኳሶች ላይ የሚመሰረቱ እንደሚሆኑ ይታሰባል።

መቐለ ከተማ ከ ድሬደዋ ከተማ

የሊጉ አዲስ ቡድን መቐለ ከተማ መጥፎ ከማይባል የውድድር ዘመን ጅማሮው በኃላ 6ኛው ሳምንት ላይ በሜዳው በደደቢት ቢሸነፍም በሳምንቱ ወላይታ ድቻን ከሜዳው ውጪ ድል በማድረግ ምላሽ ሰጥቷል። በመቀጠል ግን ቡድኑ ወደ ቀደመው የአቻ ውጤቶቹ ነው የተመለሰው። ያም ቢሆን በተለይ ከሳምንት በፊት ከሀዋሳ ይዞ የተመለሰው አንድ ነጥብ ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር ሲታይ ዋጋው ከፍ ያለ ነበር። በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ካሸነፈ በኃላ ዳግም ወደ ድል መመለስ ያልቻለው ድሬደዋ ከተማ በምክትል አሰልጣኙ ስምዖን አባይ እየተመራ ካደረጋቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘት ችሏል። በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴውድሮስ ምትኩ መሪነት የሚደረገው ጨዋታ እስካሁን አምስት ጊዜ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁ ቡድኖች የሚገናኙበት በመሆኑ ለየት የሚል ሲሆን መሸናነፍ ከቻሉ ግን አሸናፊው ቡድን ሶስት ደረጃዎች ከፍ የማለት ዕድል የሚያገኝ ይሆናል።

በመቐለ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩ ተጨዋቾች በብዛት ያገገሙ ሲሆን አሌክስ ተሰማ ግን ለጨዋታው የማይደርስ ይሆናል። ዘነበ ከበደን እና ሀብታሙ ወልዴን በረዥም ጊዜ ጉዳት ያጣው ድሬደዋ ከተማ ደግሞ የመስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ በተጨማሪነት ከጨዋታው ውጪ ሆኖበታል።

አሁንም በኩዋሜ አትራም እና ዳኛቸው በቀለ የፊት አጥቂ ጥምረት ግብ ለማግኘት እየተቸገረ የሚገኘው ድሬደዋ በጨዋታው በቀደመ ገፅታው በተለየ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የሚያሳይበት እንደሚሆን ይታመናል። ቡድኑ ለብዙ ሳምንታት ወደኃላ እያፈገፈገ በጥንቃቄ ሲጫወት የቆየ መሆኑ ከወገብ በላይ የሚኖረውን ክፍል በሚገባ ለማዋሀድ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። በ4-1-3-2 ከተከላካይ አማካዩ ኢማኑኤል ላርያ ፊት ሳምንት ግብ ባስቆጠረው ዘላለም ኢሳያስ መሪነት የሚጣመሩት ሶስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮችን በመጠቀም ዕድል ለመፍጠር ሲሞክሩ የሚታዩት ብርቱካናማዎቹ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ዘልቀው ለመግባት ሲቸገሩ ይስተዋላሉ። መቐለዎች በ4-2-3-1 የሚጠቀሙት የሁለት ተከላካይ አማካዮች ጥምረት ደግሞ ይህን የቡድኑን ድክመት ይበልጥ ሊያጎላው ይችላል። እዚህ ቦታ ላይ የሚኖረው ፍልሚያም ከጨዋታው ወሳኝ ሁነቶች መሀከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። የመቐለ ከተማው ፈጣሪ ተጨዋች ያሬድ ከበደ ከድሬደዋዉ የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ላርያ ጋር የሚኖረው ፉክክርም ለባለሜዳዎቹ ወሳኝ ነው። ከያሬድ ግራ እና ቀኝ የሚሰለፉት አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና መድሀኔ ታደሰም ፊት ላይ ካሉት አማካዮች ብዙ ሽፋን የማያገኘው ላርያ ግራ እና ቀኝ ባሉ ቦታዎች ላይ ከድሬ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚገናኙበት ነጥብ የመቐለዋች ዋነኛ የማጥቃት መነሻ የሆነውን ቦታ ፍሪያማነት የሚወስን ይሆናል። እነዚህ ጉዳዮች በጥቅሉ ጨዋታው የአማካይ ክፍል ብልጫን ለመሰድ የሚችል ቡድንን ባለድል ሊያደርግ እንደሚችል የሚጠቁሙ ናቸው።

ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

ዛሬ ከሚደረጉ ጨዋታዎች ሁሉ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው የእነዚህ ሁለት የደቡብ ክልል ክለቦች የሚያደርጉት የዱራዋ ወይንም የወንድማማቾ ደርቢ ነው። አምና 8ኛው ሳምንት ላይ በይርጋለም ሲገናኙ 3-1 ማሸነፍ ችሎ የነበረው ሲዳማ ቡና አመቱን ሌላ መልክ ይዞ በውጤት ማጣት ከጀመረ በኃላ ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር በሌላ የደርቢ ጨዋታ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን ያጣጣመው። ሆኖም ሳምንት ከሜዳው ውጪ አዳማ ከተማን ገጥሞ ነጥብ መጋራቱ የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ 9ኛው ሳምንትን በአቻ ውጤት ያሳለፈው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳው ላይ ነጥብ ሲጥል ለመጀመሪያ ጊዜም ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ፈፅሟል። ፌደራል ዳኛ ሀ/ሚካኤል አረአያ የሚመራው የዛሬው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን እስከ ሶስት እንዲሁም ሲዳማ ቡናን እስከ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ለማለት የሚያስችላቸው ነው። 

በሲዳማ በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም የፊት አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ቅጣቱን ባለማጠናቀቁ ለዚህ ጨዋታ አይደርስም። በሌላ በኩል የሀዋሳዎቹ ላውረንስ ላርቴ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ተክለማርያም ሻንቆ እና ያቡን ዊሊያም ጉዳት ላይ ሲሆኑ ፍቀረየሱስ ተወልደብርሀን ደግሞ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

ከእስካሁኑ የውድድር ጊዜያቸው ባለፈ ጎሎችን ለማግኘት ከሚጠቀሙበት መንገድም አኳያ ሁለቱ ቡድኖች ልዩነታቸው የሰፋ ነው። ሀዋሳ ከተማ የአማካዮቹን ክህሎት በመጠቀም በተጋጣሚ ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎች ሲፈጥር ሲዳማ ደግሞ የመስመር አጥቂዎቹን ማዕከል ባደረገ የመልሶ ማጥቃት ጥቃት ሲሰነዝር ይታያል። ሲዳማዎች በአዲስ ግደይ እና አብዱልጢፍ መሀመድ ፍጥነት በመጠቀም ደካማውን የሀዋሳ የተከላካይ መስመር ከማጥቃት ባሻገር የሀዋሳዎች ግራ እና ቀኝ ተከላካዮችን የማጥቃት ተሳትፎም በመገደቡ በኩል የተሻለ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። ሆኖም የሀዋሳ የመስመር አጥቂዎችም ተመሳሳይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉበት አቅም አላቸው። በዚህም የቡድኖቹ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች ከመስመር አጥቂዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው ጊዜውን እና ስኬቱን የጠበቀ ቅብብል ወሳኝ ይሆናል። ከሲዳማ ቡና በኩል ፍፁም ተፈሪ እንዲሁም በሀዋሳ ወገን የታፈሰ ሰለሞን በዚህ ረገድ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ከፍ ያለ የመሆን ዕድል አለው። ከምንም በላይ ግን የደርቢ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን የተጨዋቾች ታታሪነት ክፍተቶችን በመፍጠር እና በመከላከሉም ረገድ የሚኖረው ውጤት ከታክቲካዊ ጉዳዮች በላይ ውጤቱን የመወሰን አቅም ይኖረዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ደደቢት

በሊጉ ግርጌ እና በሊጉ መሪ መሀከል የሚደረገው ይህ ጨዋታ በፌደራል ዳኛ አክሊሉ ወ/ማርያም የሚዳኝ ሲሆን በተለያየ ፅንፍ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ማገናኘቱ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል። በሌላ ንፅፅር ደግሞ ጨዋታው ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በተሸነፈ እና አራት ጨዋታዎችን በመደዳ ባሸነፈ ቡድን መሀከል የሚደረግ ነው።  በክለቡ የአሰልጣኞች ስታፍ እና አመራር ላይ ስር ነቀል ለውጥ ያደረገው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ እዮብ ማለን በዋና አሰልጣኝነት እንደቀጠረ ትናንት ያስነበብን ሲሆን ቡድኑ በበርካታ ለውጥ ውስጥ ሆኖ ጠንካራውን ደደቢትን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ ግን የሚመሩት ለረዥም ጊዜ በጉዳት ላይ ይገኝ በነበረው የቡድኑ አምበል አማኑኤል ጎበና እና በግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ አማካይነት ይሆናል። ደደቢትን ስንመለከት ደግሞ በሰሞንኛ አቋሙ በልጦ ካሸነፈባቸው ጨዋታዎች ውጪም በአብዛኛው ደቂቃዎች ብልጫ ተወስዶበትም እንኳን ድል ማድረግ የቻለባቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች የቡድኑን የዘንድሮ ጥንካሬ እንዳሳንዩ ማወቅ ይቻላል። ይህ ጨዋታም ደደቢት መሪነቱን በሶስት ነጥቦች ርቀት ላይ እየተከተለው ያለውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመራቅ የሚያደርገው ሲሆን ባለሜዳው አርባምንጭ ደግሞ አራተኛ ሽንፈት ላለማስተናገድ እና የቡድኑን መንፈስ በውጤት ለማረጋጋት የሚሞክርበት እንደሚሆን ይታመናል።

የአርባምንጭ ከተማዎቹ ተሾመ ታደሰ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ታዲዮስ ወልዴ  እና ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳ  እንዲሁም ቀዶ ጥገና በማድረጉ ለረዥም ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ የሚጠበቀው ወንደሰን ሚልኪያስ በጉዳት እንዲሁም ገ/ሚካኤል ያዕቆብ በቅጣት ጨዋታው ያልፋቸዋል። በሌላ በኩል  ወንድሜነህ ዘሪሁን ከጉዳት መልስ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ እንደሚመለስ የሚገመት ሲሆን ደደቢት ወደ ስፍራው የተጓዘው ጉዳት ላይ የሚገኘውን ብርሀኑ ቦጋለን ብቻ ሳይዝ እንደሆነ ታውቋል።

በለውጦች የተከበበው አርባምንጭ ከተማ ምንም እንኳን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ቢገኝም ከዚህ ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። በብዛት ተመሳሳይ ለውጦችን በሚያስተናግዱ ክለቦች ውስጥ የሚታየው መነሳሳት እና በተጨዋቾች መሀል የሚኖረው መግባባት ቡድኑ በሜዳ ላይ የሚኖረውን ውጤት በፍጥነት እንዲለወጥ ሲያስችል ይታያል። ጨዋታው በሜዳው እንደመደረጉም መጠን ቡድኑ ከዚህ ሀሳብ ተጠቃሚ እንዲሆን ሊያስችለው ይችላል። በሌላ በኩል የደደቢትን የቅርብ ጊዜ ጥንካሬ ለማንሳት ሊጉን እየመራ መሆኑ እና ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛት ማየት በቂ ነው። ሆኖም የቡድኑ የአጥቂ አማካዮች ካላቸው የግል ብቃት እና ከሶስቱ የፊት አጥቂዎች ጋር የፈጠሩት ጥምረት የሰመረ ቢሆንም በመከላከሉ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ በተለይም በአቤል እንዳለ በኩል በእጅጉ መሻሻል ይኖርበታል። ቡድኑ እስካሁን የመከላከል ሚዛኑን በሚስትባቸው አጋጣሚዎች ከተጋጣሚ የአጠቃቀም ችግር እና ከሚያስቆጥራቸው ግቦች ብዛት አኳያ ችግር ላይ ባይወድቅም እነዚህን የበላይነቶች በማያገኝበት ወቅት ግን ሊቸገር የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ይህ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በአጠቃላይ የክለባቸው ከባቢ ጥሩ ሁኔታ ላይ የማይገኙ ክለቦችን የሚያገናኝ ነው። በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ስር ወልድያን በማሸነፍ ያገገመ የመሰለው ኢትዮጵያ ቡና በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ደደቢት በደረሰበት ሽንፈት ዳግም ወደ አጠያያቂ አቋሙ ተመልሷል። ዛሬ በፌደራል ዳኛ ሰለሞን ገ/ሚካኤል የመሀል ዳኝነት 10 ሰዐት ላይ የሚጀምረውን ይህን ጨዋታ ቡድኑ በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆኖ የሚያደርገው እንደሚሆን ይጠበቃል። የተጋጣሚው የወላይታ ድቻም ጉዳይ ከቡና እምብዛም አይለይም። በርግጥ ሶስት ተከታታይ ሽንፈቶችን ካስተናገዱ በኃላ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ባሰናበቱ ማግስት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በአወዛጋቢ ጨዋታ አሸንፈው ወደ 14ኛ ደረጃ ከፍ ቢሉም የቡድኑን መሻሻል ለማረጋገጥ አሸናፊነታቸው መቀጠል ይኖርበታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ቡናም ሆኑ ወላይታ ድቻ በእስካሁኑ አቋማቸው ደስተኛ ያላልሆነውን ደጋፊያቸውን ለመካስ የሚፋለሙበት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አክሊሉ አያናው ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ ክሪዚስቶም ንታንቢ እና አለማየው ሙለታ አሁንም ከጉዳት ያልተመለሱ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ናቸው። በወላይታ ዲቻ በኩል ደግሞ ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ተመስገን ዱባ እና እርቂሁን ተስፋዬ በጉዳት እንዲሁም ተስፉ ኤልያስ በቅጣት የማይሰለፉ ይሆናል።

ጨዋታው ባለሜዳው ኢትዮጽያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ያለብዙ ችግር የሚያገኝበት አይነት ነው በተለይም በድቻ በኩል ተከላካይ መስመሩ ፊት ከሚጣመሩት ኃይማኖት ወርቁ እና አብዱልሰመድ አሊ ፊት እስከ ጃኮ አራፋት ድረስ ባለው ቦታ ላይ የቡና አማካዮች የተሻለ የመቀባበያ ክፍተት እንደሚያገኙ ይጠበቃል። በተመሳሳይ በሶስቱ የድቻ ተከላካዮች ግራ እና ቀኝ የሚኖረው ቦታ ላይ የቡድኑ የመስመር ተመላላሾች ወደኃላ የተሳበ አቋቋም ከፊቱ ለኢትዮጵያ ቡና የመስመር አማካዮች ቦታ ቢተውም ከጀርባው ለመገኘት ግን አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገመታል። ይህም በመሆኑ ጨዋታው በተለይ ኢትዮጵያ ቡና በሽግግሮች ወቅት ክፍተቶችን የመጠቀም ብቃቱ የሚፈተንበት ይሆናል። ቡድኑ የድቻ የኃላ መስመር የአምስት ተጨዋቾች ቅርፅን ከመያዙ በፊት የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር ከተከላካዮቹ ጀርባ የመግባት ግዴታ ይኖርበታል። የወላይታ ድቻ ዋነኛ ጥንካሬ የሆነው ጃኮ አራፋትም ወደ መሀል ሜዳው ተጠግቶ ከሚከላከለው የኢትዮጵያ ቡና ተከላከይ መስመር ጀርባ ለመግባት በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተተባቂ ይሆናል። በተለይ በቅብብል ወቅት ስህተትን ሲሰራ የሚታየውን የቡና የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ቶጎዋዊው አጥቂ ጃኮ ሊፈትነው እንደሚችል ይታሰባል።

                                                                          

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *