​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ወልድያ

ሐሙስ ፣ ቅዳሜ እና እሁድ ሰባት ጨዋታዎች የተደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪሚምር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም በሚያስተናግደው አንድ ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል። እኛም በዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል

እንደ መጀመሪያው መርሀ ግብር ቢሆን ዓዲግራት ላይ መደረግ የነበረበት ይህ ጨዋታ ፌዴሬሽኑ ከእግር ኳስ ውጪ የሆኑ ግጭቶችን ሊያስተናግዱ ከሚችሉ ጨዋታዎች አንዱ በመሆኑ ዛሬ በ10፡00 ሰዓት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ እንዲደረግ ተወስኗል። ትናንት ከተደረጉ ጨዋታዎች በኃላ ወልዋሎ በ11 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከዚህኛው ሌላ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት ወልድያ ደግሞ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ 12ኛ ደረጃን ይዟል። አጀማመሩ የአመቱ ክስተት ቡድን ሊሆን ነው ያስባለለት ወልዋሎ ሊጉ ሁለተኛ ወሩን ከያዘ ጅምሮ በሰንጠረዡ ቁልቁል መንሸራተቱን ቀጥሏል። ኢትዮ ኤሌክትሪክን እና ኢትዮጵያ ቡናን አከታትሎ ካሸነፈ በኃላ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያገኘው ክለቡ ማስቆጠር የቻለውም አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። ተጋጣሚው ወልድያ ደግሞ ሊጉ ሲጀምር አዳማ ከተማን ካሸነፈ በኃላ ከድል ርቆ ቢሰነብትም የዛሬ ሳምንት አርባ ምንጭን መርታት ችሏል። በፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ መሀል ዳኝነት የሚደረገው የዛሬው ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱም ለወልድያ ጥሩ አጋጥሚን የሚፈጥር ይሆናል። በገለልተኛ ሜዳ እንደመደረጉም ቡድኖቹ በማሸነፍ ላይ ተመስርተው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የወልዋሎ ዓ.የው የቀኝ መስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን እንዲሁም የወልድያዎቹ አማረ በቀለ እና ብሩክ ቃልቦሬ በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ናቸው።  ወልድያ በኩል በድጋሜ ቀለል ያለ ጉዳት የገጠመው አዳሙ መሀመድ እና ተስፋዬ አለባቸው በዛሬው ጨዋታ ሊሰለፉ የሚችልበት ዕድል ሲኖር የወልዋሎ ዓ.ዩ ስብስብ ግን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።  


በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ መልክ ባለው አቀራርብ ኳስን በመቆጣጠር ከመሀል አማካዮቻቸው በሚመነጩ ዕድሎች ላይ ተመስርተው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በ4-2-3-1 አምስት አማካዮችን የሚጠቀመው ወልድያ በተለይም ፍፁም ገ/ማርያም የሚሰለፍበት የግራው የቡድኑ ወገን ፊት ላይ በብቸኛ አጥቂነት ከሚጫወተው አንዷለም ንጉሴ ጋር  የማጥቃት እንቅስቃሴው ዋነኛ አማራጭ ይመስላል። በሌላ ወገን ደግሞ ሲያጠቃ ወደ ቀኝ መስመር አጥቂውን ፕሪንስ ሰቨሪንሆ የሚያደላው የ4-3-3 አሰላለፍ ተጠቃሚው ወልዋሎ ዕድሎችን በብዛት ሲፈጥር የሚታየው በዚሁ አቅጣጫ ነው። በመሆኑም የወልዋሎን የቀኝ መስመር ከወልድያ የግራ ክፍል የሚያገናኘው የሜዳው ኮሪደር ላይ የሚኖረው እንቅስቃሴ ጨዋታውን የመወሰን ኃይሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል። ከዚህ ውጪ ወልድያዎች የሚኖራቸውን የአማካይ ክፍል የቁጥር ብልጫ ለማካካስ የወልዋሎ የመስመር አጥቂዎች የዋልዮሽ እንቅስቃሴ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህ ውስጥ የተጨዋቾች ምርጫ ልዩነት ከሌለ  በአሰልጣኝ ብርሀነ ገ/እግዚአብሄር ቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ሁለቱ አማካዮች አፈወርቅ ሀይሉ እና ዋለልኝ ገብሬ ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር የሚኖራቸውንን የቅብብል ግንኙነት ለማቋረጥ የወልድያዎቹ ሀብታሙ ሸዋለም እና ሁለቱ ያሬዶች ድርሻ ሚና ከፍ ያለ እንደሚሆን ይጠበቃል። ኳስ ቡድኖቹ  ወደሚመርጧቸው የማጥቂያ መስመሮች ከመሄዷ በፊት መሀል ሜዳው ላይ የሚኖረውን ፍልሚያ ማሸነፍ የሚችለው ቡድን ክፍተቶችን የማግኘት ዕድልም ይኖረዋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *