ካፍ የኢትዮጵያን የቻን ዝግጁነት በቀጣዮቹ ወራት ይፈትሻል

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በካዛብላንካ ሞሮኮ ረቡዕ እለት ባደረገው ስብሰባ ስድስት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹ ውስጥ አንደኛው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) በ2020 ለማስተናገድ እድሉ የተሰጣት ኢትዮጵያን የተመለከተ ነው፡፡

የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ በመሩት ስብሰባ በ2018 የመጀመሪያ ሶስት ወራት (እስከ መጋቢት ድረስ) ስለኢትዮጵያ ዝግጅት የሚፈትሽ ቡድን እንደሚልክ አስታውቋል፡፡ ቡድኑ ሃገሪቱ ውስጥ ያሉት ስታዲየሞች ጥራት እና ለውድድሩ በግዜው የመድረስ እድላቸውን የሚፈትሽበት የመጀመሪያው ስራ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ስታዲየሞችን በመገንባት ላይ ብትገኝም በታሰበላቸው ግዜ ያለመጠናቀቅ ችግር በሰፊው የሚታይ ሲሆን በባህርዳር፣ ሀዋሳ እና መቀለ እየተገነቡ ያሉት ስታዲየሞች ባይጠናቀቁም ከወዲሁ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ (የባህርዳር እና ሀዋሳ ስታዲየሞች የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ ችለዋል፡፡) ከስታዲየሞች ባሻገር የትራንስፖርት፣ የሆቴል አቅርቦትም ከሚፈተሹ ሌሎችን አንኳር ጉዳዮች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በ2007 የሴካፋ ውድድርን ከማስተናገዷ በቀር በአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ካስተናገደች 17 ዓመት አልፏታል፡፡

ካፍ ከዚህም ባሻገር በአባል ሃገራት በኩል ለአርቢትሮች ሲሰጥ የነበረውን ክፍያ አስቀርቷል፡፡ ክፍያው ከዚህ ቀደም አባል ሃገራት ካፍ በሚሰጣቸው ገንዘብ ይከፍሉ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ካፍ በሚመራቸው ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አርቢትሮች ክፍያን እራሱን እንደሚቆጣጠር የተሰጠው ውሳኔ ያሳያል፡፡ ካፍ ውሳኔውን ያሳለፈው አባል ሃገራት ፌድሬሽኖች እና አርቢትሮች መካከል የሚፈጠረውን አላስፈላጊ መቃቃር እና የስነ-ምግባር ብልሹነት ለማስቀረት በማሰብ ነው፡፡

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የውድድር ወቅት ለመለወጥም ሲጠበቅ የነበረውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ውድድሩ በ2010 መጋቢት ጀምሮ ህዳር 2011 የሚያበቃ ሲሆን የቀጣዩ አመት ውድድር ታህሳስ 2011 ጀምሮ እስከግንቦት እንደሚዘልቅ ካፍ ወስኗል፡፡ እንዲሁም የ2012ቱ ውድድሮች መስከረም ይጀምሩ እና እስከግንቦት ድረስ የሚቆዩ ይሆናል፡፡ ይህም ካፍ የውድድሮቹን ወቅቶች ለመቀየር ያሳለፈውን ውሳኔ ወደ ተግባር የሚያሻግር ይሆናል፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአፍሪካ ሊጎች ከመስከረም – ግንቦት ያላውን ወቅት የሊግ ውድድሮችን ለማካሄድ የሚጠቀሙ በመሆናቸው የወቅቱ መለወጥ ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የተዘበራረቀ የፕሮግራም አወጣጥ ላለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ጥሩ የማንቂያ ደውል ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *