​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከተማ ከ መቐለ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጎንደር ላይ ሊደረግ የነበረው የፋሲል ከተማ እና የመቐለ ከተማ ጨዋታ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ሊፈፀምበት ይችላል በሚል ጥርጣሬ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ተሸጋግሮ ዛሬ 10፡00 ላይ እንደሚደግ ይጠበቃል። ጨዋታውን እንደተለመደው በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።

ሽንፈት አልባው የፋሲል ከተማ የሊጉ ጉዞ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ምንም እንኳን ሶስት ጊዜ በተከታታይ ነጥብ ሲጋራ ቢቆይም ሳምንት መከላከያን 1-0 በመርታት ወደ ድል የተመለሰው የአሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ ቡድን በ15 ነጥቦች አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። መቐለ ከተማም በተመሳሳይ ከሁለት የአቻ ውጤቶች በኃላ ነበር በ10ኛው ሳምንት ድሬደዋ ከተማን 2-0 በመርታት ወደ አሸናፊነት የተመለሰው። እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ አንድ ጨዋታ የሚቀራቸው መቐለዎች 14 ነጥቦችን ሰብስበው 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ዛሬ በፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ የመሀል ዳኝነት የሚደረገው ጨዋታ ከሜዳ ላይ ፉክክሩ ይልቅ የደጋፊዎች የስነምግባር ጥሰት እንዳይከሰት ካሁኑ ስጋትን የሚጭር ሆኗል። እንደዛሬው ጨዋታ ሁሉ ወደ መዲናዋ ተዘዋውሮ ባሳለፍነው ሰኞ በተደረገው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና ወልዲያ ጨዋታ መገባደድ በኃላ በስቴድየም ዙሪያ ደጋፊዎች የፈጠሩት ግጭት የእግር ኳስ ቤተሰቡን እና ሌላውንም የከተማዋ ሕብረተሰብ ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ነበር። ይህ ሁኔታ ዛሬም ዳግም እንዳይከሰት የፀጥታ ሀላፊዎች ደጋፊዎች በስቴድየም ውስጥ የሚቀመጡበትን ርቀት ከማስፋት ባለፈ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላም ስታድየሙን ለቀው የሚወጡበትን ጊዜ በማለያየት እንዲሁም ሌሎች አማራጮችንም በመጠቀም ሰላማዊ የእግር ኳስ ቀን ሆኖ እንዲያልፍ ትልቅ ሀላፊነት ተጥሎባቸዋል። ደጋፊዎችም እግር ኳስን ብቻ መሰረት ያደረገ ድጋፍ ለክለቦቻቸው ሰጥተው እና ውጤቱን በፀጋ ተቀብለው በሰላም ወደየቤታቸው በማምራት የሚወዷቸው ክለቦቻቸው መልካም ስም እንዳይጎድፍ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ፋሲል ከተማ አይናለም ኃይለን በጉዳት ሲያጣ እያገገመ እንዳለ የተነገረው ይስሀቅ መኩሪያ ለዚህ ጨዋታ ብቁ መሆኑ አጠራጣሪ ሆኗል ። በሌላ በኩል በመከላከያው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው አብዱራህማን ሙባረክ በቅጣት ከጨዋታው ውጭ ነው፡፡ በመቐለ ከተማ በኩል ደግሞ ጉዳት ላይ የሚገኘው የመሀል ተከላካይ አሌክስ ተሰማ እና አማካዩ ሚካኤል አካፉ ለጨዋታው እንደማይደርሱ ሰምተናል።


ሁለቱ ቡድኖች በተለይ ግብ ካስቆጠሩ በኃላ በጥንቃቄ ተጫውቶ ውጤትን በማስጠበቅ ሂደት በኩል ባሳለፍነው ሳምንት ተሳክቶላቸው ወጥተዋል። ፋሲል ከተማ ብቸኛዋን የራምኬል ሎክ ጎል ካስቆጠረ በኃላ በመጠኑ ጥንቃቄን መርጦ ጨዋታዎን ሲጨርስ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፍ የቻለው መቐለ ከተማም በሁለተኛው አጋማሽ ተመሳሳይ አቀራረብ ነበረው። ይህ ሁኔታ በዛሬው ጨዋታ ላይ የሚንፀባረቅ ከሆነ ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥር ቡድን ባለ ድል የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። በአጨዋወት ረገድም ሁለቱ ቡድኖች መሀል ሜዳ ላይ የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመውሰድ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ይታወቃሉ። እንደ ኤርምያስ ኃይሉ አይነት ታታሪ የመስመር አጥቂዎች ያሉት ፋሲል ከተማ በዚህ ሂደት ውስጥ የአማካይ ክፍሉን ቁጥር ለማስተካከል ብዙ ሲቸገር አይታይም። ፋሲል በ4-3-3 አሰላለፍ ይጠቀም እንጂ የመስመር አጥቂዎቹ ቡድኑ ወደ መከላከል ሲሸጋገር መስመራቸውን ይዘው ወደ ኃላ በመመለስ እና የአማላይ ክፍሉን በማገዝ ተጋጣሚን አፍነው ኳስን ሲያስጥሉ ይታያሉ። እነዚህን ኳሶችም ይዘው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚፈጥባቸው ጊዜ አጭር የሚባል ነው። ግብ ሲያስቆጥሩ ደግሞ የእነዚህ የመስመር አጥቂዎች ሚና ይቀየር እና ቡድኑ የ4-2-3-1 ቅርፅ ሲይዝ ይታያል። ይህን አሰላለፍ የመጀመሪያ ምርጫው ያደረገው መቐለ ከተማም የማይለዋወጥ በሆነው የዐመለ ሚልኪያስ እና ሚካኤል ደስታ ጥምረት ለተከላካይ መስመሩ በቂ የሚባል ሽፋን በመስጠት እና የሚገኙ ኳሶችንም ወደ መስመር አማካዮቹ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና መድኃኔ ታደሰ በማሰራጨት ዕድሎችን ይፈጥራል። በዛሬውም ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች የመስመር አማካዮች እና የመስመር አጥቂዎች እንቅስቃሴ የጨዋታውን ሂደት የመወሰን አቅሙ ከፍ ያለ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ከዚህ ውጪ የፍሊፕ ዳውዚን ቦታ በመውሰድ ግብ ያስቆጠረው ራምኬል ሎክ ከፋሲል ከተማ በኩል እንዲሁም ጋይሳ አፖንግ ከመቐለ በኩል የመጨረሻ ዕድሎችን በመጠቀም እንዲሁም ዳዊት እስጢዳኖስ እና ያሬድ ከበደ ደግሞ ንፁህ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ሂደት ውስጥ ተጠባቂ የሚሆኑ ተጨዋቾች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *