ሪፖርት | ደደቢት መብረሩን ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር 11ኛ ሳምንት ሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ በአዲስአበባ ስታዲየም እና በክልል ከተሞች ቀጥሎ ሲውል አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ወልዋሎ ዓ.ዩ ን ያስተናገደው ደደቢት 4ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ በመሪነቱ ቀጥሏል፡፡

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባሳለፍነው ሳምንት አርባምንጭን 2ለ1 በረታው የቡድን ስብስባቸው ላይ ምንም አይነት ቅያሬ ሳያደርጉ በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርጽ ጨዋታውን ሲጀምሩ በአንጻሩ እንግዶቹ ወልዋሎዎች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከወልዲያ ጋር 0ለ0 ከተለያየው ቡድናቸው ውስጥ በጉዳት ተቀይሮ በወጣው ኤፍሬም ጌታቸው ሮቤል ግርማን ፣ በመስመር አጥቂው ከድር ሳልህ  አማካዩን ዋለልኝ ገብሬን በተጨማሪም ፊት መስመር ላይ ሌላው ጉዳት ገጥሞት የነበረውን እዮብ ወልደማርያምን በሙሉአለም ጥላሁን ተክተው በማስገባት በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት ደደቢቶች ከጥቂት ወራት በፊት ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት እና ከወልዋሎ ዓ.ዩ ክለብ ምስረታ ጀምሮ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ያገለገሉትን የአቶ ሰለሞን ገብረጻዲቅን የማስታወሻ ፎቶግራፍ በስጦታ መልክ ለተጋጣሚያቸው አበርክተዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ደደቢቶች ወደ መሀል ሜዳ የተከላካይ መስመራቸውን አስጠግተው ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩት ወልዋሎዎች ጀርባ የሚገኘውን ሰፊ ክፍተት በረጃጅሙ በሚላኩ ኳሶች ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ይህም ጥረታቸው በ8ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶ ከተከላካዮች በረጅሙ የተላከውን ኳስ የወልዋሎው የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው ሮቤል ግርማ ከጀርባው የነበረውን ተጨዋች በአግባቡ ማየት ባለመቻሉ በሰራው ስህተት የተገኘውን አጋጣሚ ሽመክት ጉግሳ በፍጥነት አምልጦ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በተመሳሳይ አይነት አካሄድ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካዮች በረጅሙ የተላከለትን ኳስ አቤል ያለው ከቀኝ መስመር አጥብቦ በመግባት ወደ ግብ ሲሞክር ለጥቂት እና በግቡ አናት ስትወጣበት ለቡድኑ በጣም የሚያስቆጭ ነበር። በወልዋሎዎች በኩል በመስመር አጥቂነት በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች የተሰለፈው መኩሪያ ደሱ በጣም ወደ መሀል እያጠበበ ከመጫወቱ የተነሳ የወልዋሎዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር በኩል ያጋደለ እንዲሆን አድርጓል፡፡ 24ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎ ተጫዋቾች በአደገኛ ቀጠና ላይ የተሳሳቱትን ኳስ ተጠቅመው ደደቢቶች በቁጥር ብልጫ 3ለ2 ሆነው ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል ያደረሱትን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከያብስራ ተስፋዬ ተቀብሎ ግሩም ግብ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ 30ኛው ደቂቃ አካባቢ የወልዋሎው አሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሔር በአንድ በኩል ብቻ ያጋደለውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመቅረፍ በማሰብ የተከላካይ አማካዩ ብርሃኑ አሻሞን አስወጥተው አጥቂውን ከድር ሳሊህን በማስገባት በተወሰነ መልኩ ሚዛኑን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ ነበር፡፡ በይበልጥ ወደ ወልዋሎ ሜዳ ክፍል አጋድሎ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በ37ኛው ደቂቃ አልሳሪ አልመሀዲ አቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በአግባቡ በመጠቀም ለራሱ በጨዋታው ሁለተኛውን እንዲሁም በአመቱ 9ኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀር ደግሞ በሌላኛው የሜዳ ክፍል የደደቢቱ ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ ሙሉአለም ጥላሁን ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሙሉአለም አስቆጥሮ ቡድኑ ለሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ ተስፋ ሰንቆ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አስችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በሙሉአለም ግብ የተነቃቁ የሚመስሉት ወልዋሎዎች ወደ ቀኝ መስመር ባደላ መልኩ ተደጋጋሚ ጫናዎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን ግብ ማግኘት የቻሉት ደደቢቶች ነበሩ። በዚህም 60ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቴ ከግራ መስመር ያሻማውን የማዕዘን ምት ተጠቅሞ አምበሉ ስዩም ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት የቡድኑን አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ 77ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነውና ረዥም ጊዜ በጉዳት ለቡድኑ ግልጋሎት መስጠት ያልቻለው ብርሃኑ ቦጋለ ሰለሞን ሀብቴን ተክቶ በመግባት ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል፡፡ ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢቶች ነጥባቸውን ወደ 25 በማሳደግ ከተከታያቸው ያላቸውን ልዩነት ወደ 8 በማሳደግ ሊጉን በርቀት መምራት ጀምረዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት ንጎሴ ደስታ – ደደቢት

“በዛሬው ጨዋታ ላይ ተጋጣሚያችን በመሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በርከት በማለት ለመከላከል አስበው የገቡ ይመስል ነበር ፤ ይህንንም ለመስበር ተጫዋቾቼ በሁሉም የሜዳው ክፍል ላይ ጫና በመፍጠር በመጫወታቸው አሸንፈን ለመውጣት ችለናል፡፡”

ብርሃኔ ገ/እግዚያብሔር – ወልዋሎ ዓ.ዩ

“በዛሬው ጨዋታ ላይ የራሳችን ተጫዋቾች ከሰሯቸው ስህተቶች በተጨማሪ በእኛና በእነሱ ተጫዋቾች መሀከል ያለው ተጫዋቾች የልምድ ልዩነት በጨዋታው ላይ ትልቅ ልዩነት ፈጥሯል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *