​ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

በሴቶች ፕሪምየር 1ኛ ዲቪዝዮን ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ መከላከያ ኢትዮ ኤሌትሪክን 2-1 በማሸነፍ ወደ ድል ሲመለስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ አምስተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

በውጤት ቀውስ ውስጥ ሆነው ሁለቱ ክለቦችን ባገናኘው  የዛሬው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ከማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ተደርጎበት በተካሄደው ጨዋታ ከአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ጋር የተለያዩት ኢትዮ ኤሌትክሪኮች በምክትል አሰልጣኟ ከበቡሽ ሸዋረጋ እየተመሩ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።

በመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኤሌክትሪኮች ጤናዬ ወመሴ በግሩም ሁኔታ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተጭነው ሲጫወቱ ጥረታቸው ተሳክቶ አሻሚ በሆነ ውሳኔ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት በዛሬው ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ ያደረገችው እመቤት አዲሱ ወደ ጎልነት በመቀየር መከላከያን አቻ ማድረግ ችላለች። በዚህ ጎል የተነቃቁት መከላከያዎች ብዙም ሳይቆዩ በብሩክታይት አየለ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው 2-1 መምራት ቻሉ።

ሁለት ጎል ቢቆጠርባቸውም እንደቡድን ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የአቻነት ጎል ፍለጋ በጤናዬ ወመሴ አማካኝነት ከፍተኛ  ጥረት ቢያደርጉም ረዳት ዳኛው በተደጋጋሚ በሚሰራው ስህተት ምክንያት ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። በአንፃሩ መከላከያ መዲና አወል በሰራችው አላስፈላጊ ስህተት ምክንያት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቷን ተከትሎ በተወሰደባቸውን የቁጥር ብልጫ ምክንያት ወደ ኋላ በማፈግፈግ ሲከላከሉ ቆይተው ጨዋታውን 2-1 አሸንፈው ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ደረጃውን በማሻሻል ከአራተኝነት በ10 ነጥብ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ኢትዮ ኤሌትሪክ በሁለተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከአሸነፈበት ድሉ ውጭ በአምስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ በ3 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ይገኛል።

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን የ6ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ነገ ይርጋለም ላይ ሲደረግ 09:00 ሲዳማ ቡና ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ኢትዮ ኤሌትሪክን ወደተመለከቱ ወቅታዊ ዜናዎች ስናመራ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ከረጅም ቆይታ በኋላ የተለያዩ ሲሆን ከክለቡ ጋር የተለያየበት መንገድ በኢትዮዽያውያን አሰልጣኞች ያልተለመደ መሆኑ ትምህርት ሰቶ ያለፈ ሆኗል። 

አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ከክለቡ ጋር የተለያየበትን ምክንያት ለሶከር ኢትዮዽያ እንዲህ ገልጿል። ” ቡድኑን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ሆኖም በተከታታይ አራት ጨዋታ ላይ በመሸነፋችን ምንም ሊስተካከል አልቻለም ። የዚህ ሁሉ ውጤት መጥፋት ተጠያቄው እኔ በመሆኔ በራሴ ሀላፊነት ልለቅ ችያለው።”

አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ከ1990ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ በሴቶች እግርኳስ እድገት ላይ ከፍተኛ ስራ የሰራ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ሲሆን በቅርቡም ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ መስራቱ ይታወቃል። በቀጣይ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ በምን የስልጠና ዘርፍ ይመጣል የሚለው ወደፊት መልስ የሚያገኝ ቢሆንም ክለቡ የአሰልጣኙን ውሳኔ በመቀበል በምትኩ የወንዶቹ ዋና ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ያለፉትን 3 አመታት በዋና አሰልጣኝነት የመሩትና በቅርቡ የተሰናበቱት ብርሃኑ ባዩን የሴቶች ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ እንደሾመ ተነግሯል። በዛሬው ጨዋታ ላይ ቡድኑ በምክትል አሰልጣኟ ቢመራም አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ በስታድየሙ ግራ ጥላ ፎቅ አካባቢ በመቀመጥ ጨዋታውን ሲከታተሉ ተመልክተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *