ቻን 2018፡ ሞሮኮ እና ሱዳን ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል

በሞሮኮ አስተናጋጅነት በመደረግ ላይ ባለው የቶታል አፍሪካ ሃገራት ቻምፒየንሺፕ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ረቡእ አመሻሽ ተጀምረዋል፡፡ ከምድብ አንድም ከወዲሁ ሞሮኮ እና ሱዳን ወደ ሩብ ፍፃሜው ያመሩበትን ውጤት ማግኘት ችለዋል፡፡ ጊኒ እና ሞሪታንኒያ በበኩላቸው በግዜው ከውድድሩ ውጪ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሃገራት ናቸው፡፡

ካዛብላንካ በሚገኘው ስታደ መሃመድ አመስተኛ በተደረገ ጨዋታ ሞሮኮ ጊኒን 3-1 ረታለች፡፡ በጨዋታው ላይ ሙሉ ብልጫ የነበራት ሞሮኮ በመከላከል እና መልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሞከረችውን ጊኒን አሳይቶናል፡፡ የሞሮኮው አዩብ ኤል ካቢ ሃትሪክ በጨዋታው ላይ መስራት ችሏል፡፡ አብደሊላ ሃፊዲ መጎዳቱ ቀይሮት ወደ ሜዳ የገባው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው እና በጥብቅ በሳውዲ አረቢያው ክለብ አል ሂላል እየተፈለገ የሚገኘው የአጥቂ አማካዩ ዋሊድ ኤል ካርቲ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኤል ካቢ የጊኒውን ግብ ጠባቂ አብዱላሂ ካንቴ ቀድሞ በግንባሩ በመግጨት ሞሮኮን በ27ኛው ደቂቃ ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ሆኖም የገኒ ተጫዋቾች ኤል ካቢ ከጨዋታው ውጪ አቋቋም ላይ በመገኘቱ ግቡ መቆጠር አልነበረበትም ሲሉ ቅሬታቸው አቅርበዋል፡፡ ጊኒዎች አቻ ለመሆን ብዙም መቆየት አላስፈለጋቸውም በጥሩ መልኩ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ሴኮ ቴሬዝጌት ካማራ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሴዶባ ቢሲሪ በግሩም ሁኔታ በመጨረሽ ጊኒን አቻ አድርጓል፡፡ ቢሲሪ ከካማራ የተቀበለውን ኳስ በደረቱ በማብረድ ኳስን በሞሮኮው ግብ ጠባቂ አንስ ዚኒቲ አናት ላይ በመላክ ነበር የአቻነቷን ግብ ያስገኘው፡፡

በሁለተኛው 45 ሞሮኮ ዳግም መሪ ለመሆን ከፍተኛ ጫና ፈጥራ ብትጫወትም ኳስ ይዞ ለማንሸራሸር ውጪ የጊኒን የተከላካይ ክፍል ማስከፍት ተስኗት ታይቷል፡፡ በ64ኛው ደቂቃ የጊኒው የመሃል ተከላካይ አቡበከር ካማራ በስህተት ያቀበለውን ኳስ ኤል ካቢ ከመረብ በማገናኘት ሞሮኮን ዳግም መሪ አድርጓል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ በመልሶ ማጥቃት የጊኒን የተከላካይ ክፍል ያፈረሱት ሞሮኮዎች ጨዋታውን ያጠናቀቁበትን ግብ አግኝተዋል፡፡ ኤል ካቢ ያስጀመረውን የመልሶ ማጥቃት እራሱ ጨርሶ ሃትሪክ ሰርቷል፡፡

ኤል ኳቢ ለኢስማኤል ኤል ሃዳድ አማቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኤል ሃዳድ ወደ ሳጥኑ ደርሶ መልሶ ለኤል ካቢ በማሻገር ሞሮኮዋዊው ሃትሪክ እንዲሰራ አስችሎታል፡፡ ኤል ካቢ ከወዲሁ የቻን ውድድር ኮከብ ግብ አግቢነቱን በአምስት ግቦች መምራት ሲጀምር በ2009 ቻን አምስት ግቦች በውድድሩ ላይ ካስቆጠረው ዛምቢያዊው ጊቭን ሲንጉሉማ ጋርም መስተካከል ችሏል፡፡

ሱዳን እና ሞሪታንያ በተገናኙበት የምድብ ሌላኛ ጨዋታ ሱዳን 1-0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ አምርታለች፡፡ ሞሪታንያ የሙከራም ይሁን የጨዋታ ብልጫ በወሰደችበት የመጀመሪያው 45 የሱዳኑ ግብ ጠባቂ አክራም ኤል ሃዲ ኮከብ ሆኖ አምሽቷል፡፡ ኤል ሃዲ የባባካራ ባጊሊን የግንባት ኳስ በግሩም ሁኔታ ሲያመክን ከባጊሊ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶም ኳስ ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡ እስከ30ኛው ደቂቃ ድረስ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴን ያሳየችው ሱዳን ዋለልዲን መሃመድ ባስቆጠረው ግብ 1-0 መምራት ችላለች፡፡ ዋለልዲን ከአምበሉ ሙሃናድ ጣሂር ኦስማን የተቀበለውን ኳስ አክርሮ በመምታት ነበር ሱዳን መሪ ያደረገው፡፡

በሁለተኛው 45 ሞሪታኒያዎች ከሳጥኑ ውጪ በሚሞከሩ ጠንካራ ምቶች አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል፡፡ የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ሱዳን በተሻለ ወደ ግብ መድረስ ብትችልም ግብ ለማስቆጠር ግን አጨራረስ ድክመቷ አግዷታል፡፡ መአዝ አብደልራህማን በቮሊ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ከሱዳን በኩል ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡

አዲሱ የሱዳን ክሮሺያዊ አሰልጣኝ ድራኮ ሉጋሮሲች በመጀመሪያ የሱዳን ፈተናቸው ብሄራዊ ቡድኑን ለሩብ ፍፃሜ ማብቃት ችለዋል፡፡ ሱዳን በ2011 እራሷ አዘጋጅታ በነበረው የቻን ውድድር ላይ እስከግማሽ ፍፃሜ የተጓዘች ሲሆን አሁን ለሩብ ፍፃሜ በቅታለች፡፡ ከሴካፋ ዞን ሃገራትም የተሻለ የቻን የውጤት ሪከርድ ያላትም ሱዳን ነች፡፡

ሞሮኮ እና ሱዳን በእኩል 6 ነጥብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ጊኒ እና ሞሪታንያ በግዜ ተሸኝተዋል፡፡ የዚሁ ምድብ ቀጣይ ጨዋታዎች እሁድ የሚደረጉ ሲሆን ዛሬ በምድብ ሁለት ኮትዲቯር ከዛምቢያ ሲገናኙ የመጀመሪያውን ጨዋታዋን በሽንፈት የጀመረችው ዩጋንዳ ከናሚቢያ ጋር ትጋጠማለች፡፡ ዛምቢያ እና ናሚቢያ ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ከቻሉ ወደ ሩብ ፍፃሜው ያመራሉ፡፡ ኮትዲቯር እና ዩጋንዳ በበኩላቸው የቻን ውድድራቸውን ጉዞ ለማስተካከል ሶስት ነጥብ ማግኘት አስፈላጊያቸው ነው፡፡ ጨዋታዎቹ ማራካሽ በሚገኘው ስታደ ደ ማራካሽ ላይ ይደረጋል፡፡

የረቡእ ውጤቶች

ሞሮኮ 3-1 ጊኒ

ሱዳን 1-0 ሞሪታንያ

የዛሬ ምድብ ሁለት ጨዋታዎች በስታደ ደ ማራካሽ

1፡30 – ኮትዲቯር ከ ዛምቢያ

4፡30 – ዩጋንዳ ከ ናሚቢያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *