ቻን 2018፡ ሩዋንዳ እና ናይጄሪያ ድል ቀንቷቸዋል

በቶታል የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒየንሺፕ የምድብ ሶስት ጨዋታ አርብ ምሽት ታንገ ላይ ሲደረጉ ናይጄሪያ እና ሩዋንዳ ተጋጣሚዎቻቸው አሸንፈዋል፡፡ በግራንድ ስታደ ደ ታንገ በተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች አሸናፊዎቹ ሩዋንዳ እና ናይጄሪያ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢወስዱም ግብ ለማስቆጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ኤኳቶሪያል ጊኒ ከዚህ ምድብ መሰናበቷን አረጋግጣለች፡፡

ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ናይጄሪያ ሊቢያን 1-0 ረታለች፡፡ ናይጄሪያ ሶስት ነጥብ ለማሳካት የተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነትን ስታሳይ ሊቢያ በአንፃሩ በጥንቃቄ መከላከልን ምርጫዋ አድርጋለች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽም የረባ ሙከራ ሳይደረግበት ነበር ቡድኖቹን ለእረፍት ያመሩት፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ጨዋታው ሙከራዎችን ያሳየን ሲሆን ኤሜካ አግቡግ እና አብደልሰላም አልቆብ ለግብ የቀረቡ ጠንካራ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ ናይጄሪያ በ79ኛው ደቂቃ ሰንደይ ፌላይ ባስቆጠረው ግብ ማሸነፍ ችላለች፡፡ ፌላይ ከማዕዘን የተሻረገለትን ኳስ ነበር ወደ ግብነት የለወጠው፡፡ በቀሩትም ደቂቃዎች ናይጄሪዎች ውጤታቸውን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል፡፡

ሩዋንዳ በበኩሏ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠረችው ግብ ታግዞ ኤኳቶሪያል ጊኒን 1-0 ረታለች፡፡ አማቩቢዎቹ ከኤኳቶሪያል ጊኒ በተሻለ በጨዋታው ላይ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በጨዋታው ላይ የታዩትን አብዛኞቹ ሙከራዎች ከቆሙ እና ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች የተገኙ ነበሩ፡፡ የራዮን ስፖርቱ የመሃል ተከላካይ ቴሪ ማንዚ የጂሃዲ ቢዚማናን የማዕዘን ምት በግንባሩ በመግጨት ሩዋንዳን አሸናፊ አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም ኤኳቶሪያል ጊኒ ከምድብ የተሰናበትች አምስተኛዋ ሃገራ ሆኗለች፡፡

ምድብ ሶስትን ናይጄሪያ እና ሩዋንዳ በእኩል ስድስት ነጥብ ይመሩታል፡፡ ዛሬ በምድብ አራት አንጎላ እና ካሜሮን ሲጫወቱ የምድብ መሪዋ ኮንጎ ሪፐብሊክ ቡርኪና ፋሶን ትገጥማለች፡፡ ጨዋታዎቹ በአጋድር ከተማ በሚገኘው ስታደ ደአጋድር ይደረጋሉ፡፡

የአርብ ውጤቶች

ሊቢያ 0-1 ናይጄሪያ

ሩዋንዳ 1-0 ኤኳቶሪያል ጊኒ

 

የዛሬ ጨዋታዎች

1፡30 – አንጎላ ከ ካሜሮን

4፡30 – ኮንጎ ሪፐብሊክ ከ ቡርኪና ፋሶ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *