​ወልዋሎ ከወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓዲግራት ላይ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ወላይታ ድቻ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻዎች በ33ኛው ደቂቃ ዳግም በቀለ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም የመጀመርያው አጋማሽ መደደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም ጥላሁን ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል።

በጨዋታው የወልዋሎ ደጋፊዎች በቡድናቸው ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን የቡድኑ አባላትም ሜዳውን ለቀው ለመውጣት ረጅም ጊዜ እንደጠበቁ ታውቋል።

የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ተከታታይ 7 ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወልዋሎ በ13 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአዲሱ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ስር ውጤቱን እያሻሻለ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ ነጥቦች በግብ ልዩነት በመቅደም 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በጨዋታው ዙርያ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

ብርሀኔ ገ/እግዚአብሔር – ወልዋሎ

እንቅስቃሴያችን በጣም ጥሩ ነበር ፤ የአቻ ውጤቱ በፍፁም አይገባንም።  እነሱ ምንም የፈጠሩት ነገር አልነበረም። አንድ የተሻማ ኳስ የኛ የተከላካይ ስህተት ታክሎበት ከማስቆጠራቸው ውጪ በእንቅስቃሴ እና ወደ ጎል በመድረስ እኛ የተሻልን ነበርን። በጨዋታው መጨረሻ ደጋፊያችን በውጤቱ ተናዶ ከሜዳ ለመውጣት ተቸግረን ነበር።

ግማሹ አባታችን ይላል ፤ ግማሹ ይሰድበኛል። በነበረው ተቃውሞ ደስተኛ አደለሁም። ይህም በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ይህ አዲስ ቡድን ነው ፤ የውጭ ተጫዋቾች ይምጡ ተባለ መጣ። ይባረሩ ማለት ደግሞ በጣም ያሳዝናል። በቀጣይ ግን ነገሮች ካልተስተካከሉ መቀጠል ይከብደኛል፡፡ እነሱ ይፈልጉኛል ፤ እኔ ግን በዚሀ መንገድ አልዘልቅም፡፡

ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ

ከሜዳ ውጭ እንደ መጫወታችን ውጤቱ ጥሩ ነው። የመጀመሪያ አርባ አምስት ተመጣጣኝ ነበር። ጎሉም የገባብን በተከላካይ መስመር ትኩረት ማነስ ነው። ማሸነፍ የምንችለው ጨዋታ ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *