​ሉቺያኖ ቫሳሎ – የታላቁ ተጫዋች ረጅም የህይወት መንገድ

ኢትዮጵያ ብቸኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድሏን ካጣጣመች እነሆ 56 አመታት ተቆጠሩ። ኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመኗን የሚደግምላት ትውልድ ሳታገኝ ታሪክ የሰሩላት ልጆቿንም ሳታከብር ግማሽ ክፍለ ዘመንን ተሻገረች። ታሪክ ሰርተው የመረሳት ሰለባ ከሆኑ ባለውለተኞች መካከል ሉቺያኖ ቫሳሎ ቀዳሚው ነው። ዳሚያኖ ቤንዞኒ በ blizzard ድረ ገፅ ያቀረበውን የዚህን ታላቅ የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ ረጅም የህይወት መንገድ ሚልኪያስ አበራ ወደ አማርኛ መልሶታል።


በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ብቸኛው እና ትልቁ ድል ሲገኝ የቡድኑ መሪ በኤርትራ የተወለደው፣ ባለ ቅይጥ ዜግነቱ፣ በጣሊያንኛ ስም የሚጠራው የወቅቱ ታላቁ ተጫዋች ሉቺያኖ ቫሳሎ ነበር፡፡ የዚህ ታላቅ ሰው ታሪክ አንድም በታላቅ ስኬት እና ገድል የሚጠቀስ በሌላ በኩል ደግሞ በመገለል፣ ጭቆና እና ስደት የተከበበ ነው፡፡

በአስመራ ሲኒማ ኢምፔሮ የፋሽስት ኢጣልያ የስነ-ህንፃ ውርስ እንደሆነው ሁሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ ደግሞ ከባዱን የማንነት ክፍፍል ጥያቄን የሚወክል ኮከብ ነበር፡፡ ሉቺያኖ የተወለደው ከጣሊያናዊ የቱስካን ወታደር አባት ቪቶሪዮ ቫሳሎ እና ከኤርትራዊት እናቱ መብራክ አብርሃም ነበር፡፡ ቫሳሎ በኤርትራ ይኖሩ ከነበሩት በርካታ ቅይጥ ማንነት ካላቸው ዜጎችም አንዱ ነው፡፡

ከምንም ነገር ቀልድና ጨዋታ በመፍጠር የሚታወቀው ሉቺያኖ ቫሳሎ በአስመራ ጭርንቁስ መንደሮች እግር ኳስን መጫወት ጀመረ፡፡ በሀርነት (ነፃነት) ጎዳና ለሲኒማ ኢምፔሮ ቅርብ የሆነውና በአስመራ ከሚገኙ የኃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የነበረው ኮሌጂዮ ላቬላ የሉቺያኖ የእግር ኳስ ህይወት በጥሩ ሁኔታ እንዲጀምር  ጥርጊያ ከፍቷል፡፡ ይህ የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ስቴላ አስመሪና (የአስመራ ኮከብ) ተብሎ የሚጠራ የእግር ኳስ ቡድን ነበረው፡፡ ጥቁርና ነጩ የቡድኑ መለያ በጣልያን- ኤርትራዊ (ኢታሎ-ኤርትራ) ጥንድ-ማንነት ላይ የተመሠረተው ቡድን መገለጫ ነበር፡፡ በወቅቱ ክለቡ የተቋቋመበት ዋነኛ ምክንያትም የቤተክርስቲያኗ አስተዳደሮች በከተማዋ የሚታየውን በክልስ ታዳጊዎች ውስጥ የነበረውን አሉታዊ የስነ-ልቦና ተጽዕኖ ለማስወገድ እንዲያስችል ታስቦ ነበር፡፡ በጊዜው ከጣልያናውያን አባቶች የሚወለዱ ልጆች በአባቶቻቸው ያለመፈለግ ችግር ይገጥማቸው ነበር፡፡ በኤርትራውያኑ ዘንድም ቢሆን የጨቋኙ እና ቅኝ ገዢው ዝርያ በመሆናቸው የመገለል እና የመነጠል ጫና ይደርስባቸዋል፡፡

ሉቺያኖ በስቴላ አስመሪና በግራ መስመር ተከላካይነት መጫወት ቢጀመርም ከቡድኑ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ቆይታ አላደረገም፡፡ ጥቁርና ነጮቹ የተጫዋቹን ፍላጎት የማሟላት ድክመትን አሳዩ፡፡ ቫሳሎም የሌሎች ክለቦችን ትኩረት አገኘ፡፡ የአገሪቱ የምድር ባቡር ሰራተኞች ሉቺያኖን አወያዩት፡፡ ግሩፖ ስፖርቲቮ ፌሮቬሪ በኤርትራ የባቡር ድርጅት ክለብ ነበር፡፡ ድርጅቱ በባቡር መንገድ ጥገና ሰራተኝነትና በተጫዋችነት ሉቺያኖን ለመቅጠር ቢደራደርም የተጫዋቹ ልብ ግን ወደ ሰማያዊ ለባሾቹ ገጀረት አደላ፡፡

በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉ የኤርትራ ተወላጆችን የያዘው ይህ ቡድን የሉቺያኖ ማረፊያ ሆነ፡፡ የቡድኑ አባላት በከፍተኛ የአንድነት እና በጠንካራ የቡድን መንፈስ የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎችን በመጠቀምና በየሳምንቱ መጠነኛ መዋጮ በማሰባሰብ የቡድኑን የበጀት እጥረት ለመቀነስ ይጥሩ ነበር፡፡ ከቡድኑ ዋነኛ ሰዎች አንዱ ጸጋየ ባህረ ነበረ፡፡ ይህ ሰው በኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይሰራ የነበረና በኋላም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በምክትል አሰልጣኝነት ያገለገለ ነው፡፡ ሉቺያኖ በገጀረት እ.ኤ.አ ከ1953 ዓ.ም -1958 ዓ.ም ባሳለፈው የስድስት አመታት ቆይታ ቡድኑ ወደ ከፍተኛው የሊግ እርከን እንዲያድግ አይነተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ወደ ከፍተኛው ዲቪዚዮን ባለፉበት አመትም ገጀረት ከጣልያን ቡድኖች አንዱ በነበረው ግሩፖ ስፖርቲቭ ቪስቲኒቲ ላይ የተቀዳጀው የ 4-0 ድል የሉቺያኖን የላቀ የችሎታ ደረጃ ያሳየ ነበር፡፡ በጨዋታው ሉቺያኖ ያሳየው  ብቃት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ያስቻለውን የመጀመሪያ ጥሪ አስገኘለት፡፡

በጣልያንኛው “ሎ ስፖርት ኤርትሪዮ – ክዌስቺኒ ዲ አይደንቲታ ኤድ ኦርጎግሊዮ” በሚለው ርዕስ ተጽፎ በእንግሊዝኛ የተተረጎመው እና “የኤርትራ ስፖርት – የማንነት እና የክብር ጥያቄ” በሚል በታተመው መጽሐፍ ጣሊያናዊው አጥኚ ማርኮ ባጎዚ ስለዚህ ቡድን አመሠራረት የሚከተለውን ብሏል፡፡ “ባለ ብርቱካናማ መለያው ዲፖላቬሮ ሲሴሮ በኤርትራ ሻምፒዮና መሳተፍ የጀመረው አ.ኤ.አ. በ1937/38 ዓ.ም የውድድር ዘመን ነው፡፡ ይህ ሻምፒዮና ከጣልያን 4ኛ ዲቪዚዮን የውድድር እርከን ጋር እንዲቀላቀልም ተደርጎ ነበር፡፡ ፍራንቼስኮ ሲሴሮ ወደ ጣልያን የተጓዘው እ.ኤ.አ. በ1915 ዓ.ም ሲሆን በአስመራና በቀይ ባህር ወደብ ከተማዋ ምጽዋ መካከል እየተመላለሰም በበርካታ የንግድ ዘርፎች ይሳተፍ ነበር፡፡ በእንጨትና መስታወት ስራዎች ፋብሪካዎችን በማስተዳደር እንዲሁም በአስመራ ዋናዋና መንገዶች ደግሞ ትልልቅ ባዛሮችን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡ በምጽዋም ሊዶ የተባለውን ሬስቶራንትና የፒያኖ ባር በመክፈት ታዋቂው የሙዚቃ አቀንቃኝ ሬናቶ ካሮሶኔን በኤርትራ እውቅና እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህን የሲሴሮ ስራ ልጁ ሮቤርቶ “ማይ ታክሊ” በተባለው የጣልያን-ኤርትራውያን መጽሔት ላይ አውስቷል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ክለቡ ቀዳሚ መጠሪያውን ወደ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ በመቀየር የመለያ ቀለሙንም ወደ ቀይና ሰማያዊ ለወጠ፡፡ በእርግጥ ከአመታት በኋላም በድጋሚ የመለያ ቀለሙ ወደ ቀይና ጥቁር ተቀይሮ ነበር፡፡ በአሰልጣኝ ኤንዞ አርቺዮሊ አመካኝነትም ሶስት የሊግ ዋንጫዎችን እ.አ.አ. በ1945፣ በ1947 እና በ1948 ዓ.ም ማሸነፍ ቻለ፡፡ ቫሳሎ ወደዚህ ክለብ በገባበት ጊዜ ቡድኑን በአምበልነት የሚመራው በአስመራ የሚገኙ የጣልያን ስፖርተኞች ምልክት የነበረው እና ‘ኤርትራዊው ሄሬራ’ በመባል የሚታወቀው ማሲሞ ፌኒሊ ነበር ፡፡ ፌኒሊ በጣሊያን እንደተወለደ ቤተሰቦቹ ይዘውት ወደ አስመራ መጡ፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 1974 ዓ.ም በነበረው የኤርትራ ቆይታው በአገሪቱ እግርኳስ ላይ ትልቁን ተጽእኖ ያሳደረ ሰው ነበር፡፡ ሆኖም በ1974 ዓ.ም ላይ በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ ምክንያት ወደ አገሩ ጣልያን ተመለሰ፡፡ ፌኒሊ በኤርትራ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች የሻምፒዮንነት ክብሮችን ተቀዳጅቷል፡፡ በቅርጫት ኳስ፣ በእጅ ኳስና በጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በእግር ኳስ በግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ሁለት የኤርትራ ሻምፒዮና ድሎችን እ.ኤ.አ. በ1963 እና በ1964 ዓ.ም በተጫዋችነት እንዲሁም አ.ኤ.አ. በ1972 እና በ1973 ዓ.ም በአሰልጣኝነት አግኝቷል፡፡ በ1974 ዓ.ም ደግሞ ከእምባይሶራ ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን አሸንፏል፡፡ በወቅቱም ፌኒሊ የጣሊያን የስፖርት ሚዲያን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በጣልያኑ ክለብ ቦሎኛ በነበረው አጭር ቆይታ በጥቂት የወዳጅነት ጨዋታዎች ተሠልፎ ተጫውቷል፡፡ በኤርትራ የቅርጫት ኳስ ብሄራዊ ቡድንም የመሠለፍ እድልን አግኝቷል፡፡

ቀጣዩ የሉቺያኖ የክለብ ዝውውር በክልስነቱ የሚፈጠርበትን አሉታዊ ተጽዕኖ በጉልህ ያመላከተ ነው፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ የተባለው የጣልያኖች ቡድን ለሉቺያኖ የኮንትራት ጥያቄ አቀረበለት፡፡ የወቅቱ የክለቡ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ሴሬኞ ወርሀዊ 600 የኢትዮጵያ ብር ደመወዝ እና በጣሊያኖቹ በሚተዳደረው የባቡር ትራንስፖርት ከፍተኛ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ መደበኛ ስራ የመስራት እድልን አመቻቹለት፡፡ ለተጫዋቹ የቀረበለት ይህ ግብዣ አሉታዊ ምላሽ የሚሰጠው  አልነበረም፡፡ እናቱን እንዲሁም ሁለቱን ታናናሽ ወንድና እህቱን (ኢታሎ እና ሊና) የሚረዳበትን አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ ክለቡ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ሲመሠረት ስያሜው ዲፖላቮሮ ሲሴሮ ነበር፡፡ ይህን መጠሪያ ያገኘውም ታዋቂው ጣልያናዊ ስራ  ፈጣሪ (ኢንተርፕረነር) ፍራንቼስኮ ሲሴሮና በፋሽስቶች ከሚመሩት የእግር ኳስ ቡድኖች አንዱ የሆነው ይህ ክለብ በጋራ የመስራት ስምምነትን ከፈጠሩ በኋላ ነው፡፡

ሉቺያኖ ወደ ግሩፖ ዲፖርቲቮ አስመራ ሲገባ እድሜው በ20ዎቹ አጋማሽ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ በክለቡም ከመከላከል ወረዳ ተጫዋችነት ወደ ብልህ እና የተሻለ የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ያለው ደረጃ አሳደገ፡፡ ጨዋታን የመምራት ብቃቱም አስገራሚ እየሆነ ሄደ፡፡ በጠንካራ ምቶቹ ይታወቅም ጀመር፡፡ በጊዜው ውጤታማ የነበረው ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ እ.ኤ.አ. በ1959 ዓ.ም በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በወዳጅነት ጨዋታ አሸነፈ፡፡ ቡድኑ እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ.ም በተነሳው የተጫዋቾች ምስል ላይ የሉቺያኖ ጠየም ያለ መልክ በጥቁርና ነጩ መለያ ከሚታዩት አስር ጣልያናውያን ተጫዋቾች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ሉቺያኖ በዚህ ክለብ በመጫወቱ የደረሰበት ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ በቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች ምክንያት ክለቡ በአገሬው ህዝብ የተጠላ ነበረ፡፡ ህዝቡም ሉቻኖን በዚህ ክለብ በመጫወቱ እንደ ከዳተኛ ቆጠረው፡፡

የሉቺያኖ የህይወት ውጣ ውረድና ታሪክ የሚመደበው ሌሎች ታሪክን ከቀየሩና በአገሪቱ ለውጦች ከፈጠሩ ሰዎች ጋር ነው፡፡ ይህ እውነት በሀርነት ጎዳና ብቻ አይወሰንም፡፡ በአስመራ የሚገኘው ዋነኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የሲሴሮ ስታዲየም ነበር ፡፡ ስታዲየሙ እ.ኤ.አ. በመስከረም 29-1938 ዓ.ም በፍራንቼስኮ ሲሴሮ ተመርቆ የተከፈተና የራሱ ቡድን እንዲጫወትበት የተሰራ ነበር ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1949 ዓ.ም ስታዲየሙ ለጣሊያን የቀይ መስቀል ማህበር ተሰጠ፡፡በአዲሶቹ የአገሪቷ አስተዳዳሪዎች ቁጥጥር ስር እንዳይውል ታስቦ የተደረገ ስጦታ ነበር ፡፡ በኋላም ሜዳው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ በነበሩት ራስ አሉላ አባነጋ ስም እንዲጠራ ተወሰነ፡፡ ጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ የጣሊያንን ጦር በታላቅ ጀብዱ በዶጋሊ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1896 ዓ.ም በአድዋ ላይ ታሪካዊ ድል የተቀዳጁ ስመጥሩ የጦር መሪ ነበሩ፡፡ የአድዋው ሽንፈት በተለይ በጣሊያን ከፍተኛ  ውዝግብን ፈጥሯል፡፡ በወቅቱ በሽንፈቱ ምክንያት በአገሪቱ የነበሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዘግተው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንቼስኮ ክሪስፒም ከስልጣን ራሳቸውን አገለሉ፡፡ አዲሱ የስታዲየሙ ስያሜም እ.ኤ.አ. በ1962ዓ.ም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለተፈጠረው የመዋሀድ ውሳኔ መንገድን ፈጠረ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1953ዓ.ም ጀምሮም የኤርትራ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ከኢትዮጵያ የእግር ኳስ ውድድር ፎርማት ጋር ተቀላቅሎ ሶስቱ የኤርትራ ቡድኖች በሸዋ ክፍለ ሀገር እና ከሐረር ጠቅላይ ግዛት ቡድኖች በተውጣጡ የ8-ክለቦች ሻምፒዮና ተጀመረ፡፡ በወቅቱ በኤርትራ ይኖር የነበረው 1.5 ሚሊየን ህዝብ ከ23 ሚሊየኑ የኢትዮጵያ ህዝብ አንፃር ሲታይ ትንሽ የነበረ ቢሆንም ኤርትራውያኖቹ ከጣሊያን ባገኙት ልምድ የስፖርት ባህላቸው ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ነበረው፡፡ የኤርትራ ቡድኖች በተለያዩ ውድድሮች ይሳተፉ ነበር፡፡ ይህ “ፕሮፖጋንዳ” የሚል ስያሜ የነበረው ውድድር በተለያዩ የኤርትራ ክፍሎችም ወዲያው ተስፋፋ፡፡ ማርኮ ባጎዚ እ.ኤ.አ በ1936 ዓ.ም “ኤል ሎቶሪያሌ” በተባለው የፋሽስቶች የስፖርት መጽሄት ላይ ካለው ጽሁፍ የሚከተለውን ይጠቅሳል፡፡ ”የኤርትራ ተወላጆች መጀመሪያ ውድድሩን ከግርግር ጋር ያገናኙት ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ግን እየተላመዱት መጡ ፡፡ ህዝቡ እውነተኛ እግር ኳስ ወዳድ ነበር፡፡ በፍጥነትም ከስፖርቱ ጋር ተቆራኙ፡፡ ታዳጊዎች የሚመለከቷቸውና እንደነርሱ ለመሆን የሚያልሙባቸው ተጫዋቾችን እያዩ የማደግ እድልን አግኝተዋል፡፡”

እ.ኤ.አ በ1940ዎቹ የኤርትራ ቡድኖች ከጣልያናውያኖቹ ጋር በመቀላቀል በሻምፒዮናው መሳተፍ ጀምረው ነበር፡፡ ሀማሴን የተባለው ቡድንም በውድድሩ ከቀድሞው አሸናፊ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ የሁለተኛ ደረጃን አገኘ፡፡ እጅግ ወሳኝ ተጫዋቻቸው አብርሃ ግዛው ነበር ፡፡ ሉቺያኖ ለባጎዚ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ላይ አብርሃን ” ከትውልዱ የላቀና እውነተኛ አሸናፊ! ” ሲል ይገልፀዋል፡፡ አብርሃ ጥሩ የቅጣት ምት ባለሟል እንደነበር ይነገራል፡፡ ኤርትራዊ ሆኖም የጣልያን ክለብን መለያ የለበሰ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ መጀመሪያም የአብርሃ የፊዮረንቲና ዝውውር ጫፍ ደርሶ በዘረኝነት ችግር ምክንያት እንዳልተፈፀመ በጊዜው በምስራቅ አፍሪካ ከነበሩ ጣሊያናውያን የስፖርት ጋዜጠኞች ታዋቂው ኤንሪኮ ማንዴ እ.ኤ.አ በ1952 ዓ.ም አካባቢ በወጣው መጽሔት ላይ ባሰፈረው ጽሁፉ ያስረዳል፡፡

ከኢትዮ-ኤርትራ የእግር ኳስ ሊግ ውህደት በኋላ በነበሩት ሰባት አመታት ከኤርትራ የመጡ ቡድኖች አራት ጊዜ ሻምፒዮን መሆን ችለዋል፡፡ ሐማሴን እ.ኤ.አ በ1955 እና በ1957 ዓ.ም ሲያሸንፍ፤አካለ ጉዛይ በ1958 ዓ.ም እና የቴሌኮሙኒኬሽን ስፖርት ክለብ (ኋላ ገጀረት ተብሎ የተጠራው) በ1959 ዓ.ም የሻምፒዮንነት ክብርን ተጎናጽፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከኢትዮ-ኤርትራ ውህደት በተገኙ ተጫዋቾች የተመሰረተ ቡድን ነበር፡፡ ከነዚህ ተጫዋቾች አንዱ  ሉቺያኖ ቫሳሎ ነው፡፡ የመጀመሪያ ጥሪ የደረሰውም እ.ኤ.አ በ1956ዓ.ም ነው፡፡ በእርግጥ በቡድኑ ውስጥ ችግሮችን መቋቋም ነበረበት ፡፡ ኤርትራውያኑ ተጫዋቾች በኢትዮጵያውያኑ ላይ የነበራቸው ቅራኔ የህብረት ግንኙነቱን ቀላል አላደረገውም፡፡ሉቺያኖ እንዲያውም ከታላቁ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማም ጋር የነበረው ስምምነት የጠለሸ አይነት ነበር።

ሉቺያኖ በግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ለሁለት አመታት ከተጫወተ በኋላ ወደ ድሬዳዋ ጥጥ ክለብ አመራ፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበሩት ኮተኖች ቡድናቸውን ለማጠናከር በሐማሴን ጥሩ አጥቂነቱን ያስመሰከረው የሉቺያኖ ታናሽ ወንድም ኢታሎን ጨምረው አስፈረሙ፡፡ ሁለቱም የሉቺያኖ ታናናሾች ኢታሎና ሊና ከሉቺያኖ እናት ከወ/ሮ መብረክ አብርሀም እና ከሌላ አባት የተወለዱ ቢሆንም ስማቸው በአስመራ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቫሳሎ እንዲጠራ ተመዘገበ፡፡ አንቶኒዮ ፌልሲ በሉቺያኖ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ (ስቴላ ዲ አፍሪክ = የአፍሪካ ኮከብ) ላይ ሲገልጸውም “ሁሉም ልጆች በቫሳሎ ስም ተጠሩ፡፡እጣ ፈንታቸውም እንዲሁ ተመሳሳይ ነበር፡፡ጣሊያናዊው ወታደር ቢያንስ የአባት ስም ሰጣቸው፡፡ የቫሳሎ ቤተሰብም ተባሉ፡፡” በማለት ነበር፡፡ በኮተን የሉቺያኖ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን የተሳካ አልነበረም፡፡ ቡድኑ በከተማ ተቀናቃኙ ኢትዮ ሲመንት ከባድ ፉክክር ገጥሞት የዋንጫ ድሉን ማስጠበቅ ሳይችል ቀረ፡፡ እ.ኤ.አ ከ1960-1965 ዓ.ም ድረስ ሁለቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ኃያላን በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ የበላይነት አሳይተዋል፡፡ ኮተን ክለብም በቫሰሎ ወንድማማቾች ብቃት ታግዞ ሶስት የሊግ ድሎችን እ.ኤ.አ በ1962፣ በ1963 እና በ1965 ዓ.ም ተጎናፀፈ፡፡ ቡድኑ በአፍሪካ አሸናፊዎች ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ደርሶም ኩማሲ ላይ በማሊው ስታድ ማሊየን የ 3-1 ሽንፈት ገጠመው፡፡

በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቫሳሎ ወንድማማቾች የብቃት ደረጃ ከፍታ በገሀድ ታየ፡፡ የፍጻሜው ጨዋታ እ.ኤ.አ በጥር 1962ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀዳማዊ ኀይለ ስላሴ ተመልካችነት  የተደረገ ነበር፡፡ ከሁለት አመት በፊት እ.ኤ.አ በ1960ዓ.ም አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባመጣው ተዓምራዊ የወርቅ ሜዳልያ ድል የአገሪቱን የስፖርት ግርማ ሞገስ ከፍ አድርጎት ነበር፡፡ በእርግጥ በ1960ው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት አስከፊ የሚባል ነበር፡፡ በሶስት ቡድኖች ተሳትፎ ብቻ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ (ግብጽ) እና ሱዳን 5 ጎሎች ተቆጥረውባት፤ ምንም ጎል ሳታስቆጥር ከውድድሩ ተሰናበተች፡፡ ይህ ደካማ ውጤት አቶ ይድነቃቸውን አነቃቸው፡፡ በኤርትራውያን ተጫዋቾች ላይ የነበራቸውን ቸልተኝነኝትም እንዲተው አደረጋቸው ፡፡ ቀድሞ በብሔራዊ ቡድኑ የሚታየው ኤርትራውያንን ያለማካተት አቋምን እንዲለውጡ አስገድዷቸው በቡድኑ ውስጥ ከስድስት በላይ ቋሚ ተሰላፊ ኤርትራውያን ታዩ፡፡ አቶ ይድነቃቸው የአምበልነት ማዕረጉን ለሉቺያኖ ለመስጠት ባይፈልጉም በቡድን አጋሩ መንግስቱ ወርቁ ጉትጎታ ሉቺያኖ በአምበልነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን እንዲመራ ተደረገ፡፡ 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአራት ቡድኖች መካከል ነበር የተካሄደው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በሉቺያኖ 2 ጎሎች፣ በመንግስቱ 1 ጎል እና በተክሌ ኪዳኔ (በገጀረት የሉቺያኖ የቡድን ጓደኛ) ተጨማሪ 1 ጎል አማካኝነት ኢትዮጵያ ቱኒዝያን 4-2 ረታች፡፡

በፍፃሜው ጨዋታ ግብጾች ባልተረጋጋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ በ35ኛው ደቂቃ በበደዊ አብድልፈታህ አማካኝነት ጎል አግብተው አስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ በመሪነት ዘለቁ፡፡በ75ኛው ደቂቃ ላይ ተክሌ ኪዳኔ ኢትዮጵያን አቻ አደረገ፡፡ የበደዊ ሁለተኛ ግብ የግብፅን መሪነት መልሶ አስገኘ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩ ሉቺያኖ ያስቆጠራት ግብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወደ ዳግም አቻነት መለሰች፡፡ ይህች ጎል የግብጾችን ሞራል አወረደች፡፡ በጭማሪው ሰዓት ኢትዮጵያውያኖች በተዳከሙት ግብጾች ላይ ከፍተኛ ብልጫን አሳዩ፡፡ ኢታሎና መንግሥቱ አከታትለው ጎሎችን በማስቆጠር ለብሔራዊ ቡድናቸው የ 4-2 ድልን አስገኙ፡፡ኢትዮጵያም የመጀመሪያውንና ብቸኛውን አለም አቀፍ ዋንጫ አሸነፈች፡፡ በአስመራ ከጣሊያናዊ አባትና ከኤርትራዊት እናት የተወለደው ሉቻኖ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበልነት ከአፄ ኀይለስላሴ እጅ ዋንጫ ተቀብሎ ወደ ላይ ከፍ አደረገ፡፡ ጎሎችን አስቆጥሮ የአፍሪካን ዋንጫ የማንሳት ሀሳብ በአዕምሮው መጥቶ እንደማያቀው ሁሉ እጅጉን የሚያከብራቸው ንጉስ ኀይለ ስላሴ ከ12 አመት በኋላ መጨረሻቸው እንደዛ ይሆናል ብሎ አልጠበቀም፡፡የሳቸውን አይነት መሪ ተፈጥሯል ብሎም አያስብም፡፡

በኢትዮጵያ የንጉሳዊው አገዛዝ ስርዓት ሲያበቃና ደርግ ስልጣን ሲይዝ ሉቻኖ ኳስ መጫወትን አቁሞ ነበር፡፡ በጣሊያን ታዋቂ በሆነው የእግርኳስ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ማዕከል ኮቨርሲያኖ ከአርማንዶ ፒቺ ፣ ሴዛሬ ማልዲኒና ሉዊስ ቪንሲዮ ጋር በመማር የአሰልጣኝነት ባጁን ተረከበ፡፡ በዚሁም  ወደ አሰልጣኝነት አለም ተቀላቅሎ በአዲስ አበባ  ብዙም ስኬታማ ያልነበረ ቆይታን በቅዱስ ጊዮርጊስ አደረገ፡፡ በመቀጠልም ከአንድ አርመናዊ መካኒክ የቮልስዋገን ጋራዥ ገዛ፡፡ ከዚህ በኀላ ነበር ከደርግ ስርዓት ጋር የማይስማማባቸው በርካታ ምክንያቶች የተፈጠሩት።

የቫሳሎ ሀብታምነት፣ ክልስ መሆኑ፣ ኤርትራዊነቱ፣ ከውጭ ዜጎች ጋር የነበረው ግንኙነት እና ከንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር የመሰረተው ወዳጅነት ከደርግ ጋር በእጅጉ አቃረነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነቱ ተነስቶ በጀርመናዊው ፒተር ሺንግተር ሲተካ ከጊዜያት በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች “አምፊታሚን ካፕታጎን” የተባለ አነቃቂ፣ ጉልበት ሰጪና የምግብ ፍላጎት የሚቀንስ መድሀኒት መጠቀማቸውን ማውገዙና መንቀፉ በአዲሱ መንግሥት በጠላትነት እንዲፈረጅ አደረገው፡፡ በአንዱ ማለዳም በሉቺያኖ ጋራዠ ውስጥ ከወታደራዊው መንግሥት ሰዎች አንደኛው መኪናውን አቁሞ ሊወስደው ይጠብቀው ጀመር፡፡ የቀድሞ ዝነኛና ባለውለታ ኳስ ተጫዋች መሆኑን የሚያውቅ ኮሎኔል አግኝቶት ባያስለቅቀው ኖሮ የሉቻኖ መጨረሻ ምናልባትም ያ ቀን ይሆን ነበር፡፡ አስደንጋጩ አጋጣሚ ሉቻኖን ይበልጥ ጥንቁቅ እንዲሆን አገዘው፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ቡድኑን በድጋሚ እንዲያሰለጥን ጥያቄ ቀርቦለት እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በአሰልጣኝነት የመጨረሻ ጨዋታው ምስራቅ ጀርመንን ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ አሸነፈ፡፡ ከጨዋታው  ሁለት ሳምንት በኋላም በጠዋት ወደ ጋራዡ ሄዶ የሁሉንም ሰራተኞች ደመወዝ ከፈሎ ወደ ጅቡቲ አመራ፡፡ ከጅቡቲም በካይሮ በኩል ወደ ሮም በረረ፡፡ ከወራት በፊት ለደህንነት ሲል ቤተሰቦቹን ወደ ሮም ልኮ ነበር፡፡

የቫሳሎ ወንድማማቾች ትልቅ ዋጋ ከፍለው ላስገኙት አስገራሚ ድል ከኢትዮጵያ ስፖርት ምንም አይነት ክብርና ምስጋና አላገኙም፡፡ በአዲስ አበባ የከተመው ኢታሎ የራሱን ሬስቶራንት እያስተዳደረ ኑሮውን ቢገፋም እ.ኤ.አ በ1998 ዓ.ም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ሀገራቸው እንዲጓዙ ከተደረጉ ሌሎች 77,000 ኤርትራውያን ጋር ተሰደደ፡፡ ደርግ ሉቻኖ ከኮበለለ በኋላ ምስጉን ስሙን ከተለያዩ መረጃዎች ላይ እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡ ለኢትዮጵያ ያደረገው በጎ ነገር በሙሉ ተሸፈነ፡፡ ከሁሉ የከፋው ግን በስደት ከሌላ ማንነት ጋር እንዲላመድ መደረጉ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹን ከተለያዩ ችግሮች መታደግ ነበረበት፡፡ በአስቲያ ባህር ዳርቻም የመኪና ጥገና ጀመረ፡፡ ቆይቶም የራሱን ጋራዥ ከፈተ፡፡ ከሁለት አመት እድሜው ጀምሮ ሲከለከል የቆየው የጣሊያን  ፓስፖርትንም ተቀበለ፡፡ በሮም የወደብ ዳርቻም መጠለያውን አገኘ፡፡ ብዙ ችግሮችን ባየባት ከተማ ተቀምጦ ታሪኩን ማውጋቱን አያቆምም፡፡

በእርግጥም የሉቻኖን ማንነት በአንድ ቃል ብቻ ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ኤርትራዊ፣ ኢትዮጵያዊ ፣ ኢጣልያዊ፣ አፍሪካዊ፣ ባለ ጥምር ዜጋ (ክልስ)፣ ስደተኛ፣ የተገፋ እና አሸናፊ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *