ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ| ደደቢት ከ ጅማ አባ ጅፋር

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲደረግ መሪው ደደቢት ጅማ አባ ጅፋርን የሚያስተናግድ ይሆናል። ይህን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

የደደቢት አስገራሚ ግስጋሴ እንደቀጠለ ነው። በ12ኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ የነበረው ተጠባቂ ጨዋታ ከተላለፈ በኃላም ደደቢት ተጨማሪ ጨዋታ ካደረጉት ተከታዮቹ የአራት ነጥብ ልዩነት ኖሮት በሊጉ አናት ተቀምጧል። ቡድኑ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ አስራስድስት ጎሎችን አስቆጥሮ አምስት ግቦችን ብቻ ማስተናገዱ ደግሞ አሁን ላይ ላለው ጥንካሬ ተጨማሪ ማሳያ ነው። በታህሳስ ወር መግቢያ እና አጋማሽ ላይ በተከታታይ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ተከትሎ ደረጃውን በሚገባ ያሻሻለው ጅማ አባ ጅፋር ወሩ ሲገባደድ ለመጨረሻ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረገው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 መሸነፉ ውደ ደካማው አቋሙ እንዳይመለስ ስጋት የጫረ ነበር። ነገር ግን በሜዳው ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን አሳክቶ ከመሪዎቹ ብዙም ሳይርቅ እንዲቀመጥ ሆኗል። በደፌራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት የሚደረገውን የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ደግሞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ይችላል። በአንፃሩ ደደቢቶች ሰባተኛ ተከታታይ ድላቸውን ካስመዘገቡ ከወዲሁ ከተከታዮቻቸው ጋር ያለው ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ የሚል ይሆናል።

የደደቢቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ስዩም ተስፋዬ እና የጅማ አባ ጅፋሩ የፊት አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ሲሆኑ ለረዥም ጊዜ ከሜዳ የራቁት የእንግዶቹ ዝናቡ በፋአ ፣ ጌቱ ረፌራ እና አሸናፊ ሽብሩ አሁንም ከጉዳታቸው አላገገሙም።

ጨዋታው ወጥ የቡድን ቅርፅን እና አጨዋወትን ይዘው ለሳምንታት በዘለቁ ቡድኖች መሀል የሚደረግ ነው። ሁለቱም በመጀመሪያ ሳምንታት የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ በየቡድናቸው ላይ ማሻሻዮችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ደደቢትን ለስድስት ጅማ አባ ጅፋርን ደግሞ ለሶስት ተከታታይ ድሎች በመሩት አሰላለፎቻቸው እና የተጨዋቾች ምርጫቸው ላይ ረግተዋል። በዛሬውም ጨዋታ እንደሰሞኑ ሁሉ ደደቢት በ4-3-3 እንዲሁም ጅማ አባ ጅፋር በ4-4-2 አሰላለፍ ጨዋታውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

በዛሬው ፍልሚያ ደደቢት በሜዳው እንደመጫወቱ ሙሉ ለሙሉ እንደሚያጠቃ መገመት ቢቻልም ጅማ አባ ጅፋርም የተወሰነ ጥንቃቄ የታከለበት ጨዋታን ይመርጥ እንደሆነ እንጂ ሙሉ ለሙሉ በመከላከሉ እንደማይጠመድ ይታሰባል። በዚህም መሰረት የአባ ጅፋሮቹ አሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው የደደቢት የማጥቃት አማካዮች የሆኑትን አቤል እንዳለን እና የአብስራ ተስፋዬን እንቅስቃሴ ለመግታት በብዛት ለተከላካይ መስመራቸው ቀርበው እንዲሁም በመከላከል ሽግግር ወቅት በተጨዋቾቹ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርተው ሰው በሰው በመያዝ እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል። ደደቢቶች የተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ከአማካዩ ጋር ሲራራቅ በፍጥነት ሰብሮ ገብቶ ግብ የማስቆጠር ብቃታቸውን የወልዋሎው ጨዋታ በሚገባ ያሳየ በመሆኑ ጅማዎች ተመሳሳይ ስህተት የሚሰሩ ከሆነ በቀላሉ ግብ ማስተናገዳቸው የማይቀር ነው። በደደቢት በኩል ከጅማ አባ ጅፋር ሁለተኛ አጥቂ ጫና ካልደረሰበት በቀር አስራት መገርሳ የተሻለ ነፃነት ሊኖረው ይችላል። ተጨዋቹ ከጫና ነፃ በሚሆንባቸው አጋጣሚዎች የቡድንን ማጥቃት የማስጀመር ክህሎት ያለው በመሆኑ ልዩነት የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን የማስጀመር ዕድል ይኖረዋል። የፊት አጥቂዎቹ ጌታነህ ከበደ እንዲሁም ጅማዎቹ ሳምሶን ቆልቻ እና ተመስገን ገ/ኪዳን በተረጋጉት የተጋጣሚዎቻቸው የተከላካይ መስመሮች ፊት የሚያገኟቸው ዕድሎች ከመሀል አማካዮቻቸው በላይም ከመስመር ተሰላፊዎቻቸው እንደሚመጡ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ የደደቢቶቹ የመስመር አጥቂዎች ሽመክት ጉግሳ እና አቤል ያለው ወደ መሀል አጥብበው በመግባት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ይሆናሉ።

በአባጅፋር በኩልም የመስመር አማካዮቹ ዮናስ ገረመው እና ሔኖክ ኢሳያስ ከሚኖርባቸው የመከላከል ተሳትፎ አንፃር እንደ ሽመክት ጉግሳ እና አቤል ያለው እስከ ተጋጣሚ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ድረስ በተደጋጋሚ ዘልቆ የመግባት ዕድል ባይኖራቸውም ባለፉት ጨዋታዎች እንዳየነው መሀከለኛ ርዝመት ባላቸው ኳሶች ከአጥቂዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚሞክሩ ይታሰባል። በጥቅሉ ጨዋታው ክፍት የሆነ እና ጥሩ የኳስ ፍሰትን ከሙከራዎች ጋር የምንመለከትበት ሆኖ እንደሚያልፍ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *