​ሚኪያስ መኮንን እና አቡበከር ነስሩ ” የመጫወት እድል ተነፍጎናል ” ይላሉ

የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ተስፈኛ ወጣቶች አቡበከር ነስሩ እና ሚኪያስ መኮንን ዘንድሮ የመጫወት እድል ባለማግኘታቸው ምክንያት ከእይታ ርቀዋል።  ሶከር ኢትዮጵያም በየሳምንቱ ሀሙስ በምታቀርበው የተስፈኛ ተጫዋቾች አምዷ ሁለቱ ተጫዋቾች አሁን ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ፣ እያጋጠማቸው ስለሚገኘው ፈተና እና ተያያዥ ጉዳዮች ተከታዩን ጽሁፍ አዘጋጅታለች።


ትውልድ እና እድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ ነው። ሁለቱም በአንድ አካባቢ አድገው በአንድ አካባቢ ሜዳ እግርኳስን ተጫውተው ፣ በአንድ ክለብ የታዳጊ ቡድን (ሐረር ሲቲ) የእግርኳስ ህይወታቸውን ጀምረው በአትዮዽያ ቡና ከ2009 ጀምሮ በመጫወት ላይ ይገኛሉ።

አብሮ አደግነታቸው እና ቅርርባቸው የወንድማማች ያህል እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለቱ የወደፊት የኢትዮዽያ እግርኳስ ኮከቦች በአአ ሰሜን ገበያ አካባቢ ነው እድገታቸው። ለአካባቢያቸው ቅርብ ወደ ሆነው ጉቶ ሜዳ እግርኳስን መጫወት የጀመሩት ሚኪያስ እና አቡበከር የልዩ ተስዕጦ ባለቤት ናቸው። ይህ አቅማቸውን የተረዳው የአሁኑ የአአ ከተማ ምክትል አሰልጣኝ ቀድሞ የሐረር ሲቲ ከ17 አመት በታች ዋና አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር አማካኝነት ነበር ወደ ሐረር ሲቲ ከ17 አመት በታች ቡድን ታቅፈው መጫወት የጀመሩት። በቆይታቸው ባሳዩት ምርጥ አቋምም በ2008 ለኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው በሁለት የደርሶመልስ ጨዋታ ላይ ያሳዩት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በስፖርት አፍቃሪው አእምሮ ውስጥ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። አቡበከር ከግብፅ ጋር ካይሮ እና ድሬዳዋ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ሦስት ጎሎች ሲያስቆጥር የቦታ አያያዙ እና የአጨራረስ ችሎታው የወደፊቱ ምርጥ አጥቂ እንደሚሆን ተስፋ የሰጠ ነበር። የመስመር አጥቂው ሚኪያስ መኮንን ደግሞ በተለይ በካይሮ በተደረገው ጨዋታ ሦስት ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂውን በግሩም ሁኔታ አልፎ ያስቆጠረበት መንገድ በግብፅ ሚድያዎች መነጋገርያ የሆነች እና የጨዋታ ውጤት ብቻውን የመወሰን አቅም ያለው ባለ-ክህሎት እንደሆነ ያሳየበት ነበር።

እነዚህ ሁለት ተጫዋቾች ባሳዩት አቋም የብዙ ክለቦች አይን ያረፈባቸው ሲሆን ሚኪያስ መኮንን ወደ ቱንዚያው ኃያል ክለብ ኤቷል ደ ሳህል በማምራት የሙከራ ጊዜ አሳልፎ መምጣቱ የሚታወስ ነው። በ2009 ሁለቱም ተጫዋቾች ከብዙ ውዝግብ በኋላ ለኢትዮዽያ ቡና በመፈረም ወደዋና ቡድን በቀጥታ መግባት ችለዋል።

ወጣቶቹ ኢትዮዽያ ቡናን በተቀላቀሉበት አመት በተለይ በሁለተኛው ዙር ባገኙባቸው የመሰለፍ አጋጣሚዎች ተመልካች ማስገረማቸውን ቀጥለው ነበር። በተለይ አቡበከር ነስሩ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ በተሰለፈበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ላይ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን በአመቱም በአጠቃላይ 5 ጎሎች በስሙ ማስመዝገብ ችሏል። ሆኖም የሁለቱ ተጫዋቾች የዘንድሮ ጉዞ በተቃራኒ መንገድ ሆኗል። አምና ካሳዩት ተስፋ አንፃር ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ እድል እንደሚያገኙ ቢጠበቁም እምብዛም በሜዳ ላይ ሳንመለከታቸው የውድድር ዘመኑ ተጋምሷል።

ተጫዋቾቹ ስለመጀመርያ የውድድር አመታቸው ፣ ስለ ዘንድሮው የውድድር አመት እና የመሰለፍ እድል ስለማጣታቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋረ ባደረጉት አጠር ያለ ቆይታ ተናግረዋል።

በ2009 መልካም የሚባል የውድድር አመት አሳልፋችኋል። የኢትዮዽያ ቡና የመጀመርያ አመት ቆይታችሁን እንዴት ትመለከቱታላችሁ ?

ሚኪያስ : አምና በኢትዮዽያ ቡና የነበረን ቆይታ መልካም ነበር። አሰልጣኞቻችን በሚሰጡን የመጫወት አጋጣሚ የምንችለውን ነገር እያሳየን እንወጣ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ከአምናው የተሻለ የመሰለፍ እድል እናገኛለን ብለን የነበረ ቢሆንም በአሰልጣኝ መቀያየር ይሁን በሌላ ምክንያት የምንፈልገውን ያህል የመጫወት እድል እያገኘን አይደለም። እንዲያውም አሁን በመጣው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ትንሽም ቢሆን የመሰለፍ አገኘን እንጂ ብዙም አስደሳች ጊዜ እያሳለፍን አንገኝም።

አቡበከር ፡ አምና ጥሩ ጊዜ ነበር። ብዙም ሳልለፋ ወደ ዋናው ቡድን አድጌያለሁ። በብሔራዊ ቡድን ባሳለፍኩት ቆይታ ጥሩ ነበር። ቡናም ብዙ የመሰለፍ እድል አግኝቼ መልካም ነገሮችን መስራት ችያለው። ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ነገር ነበር የጠበቅኩት። ሆኖም አዳዲስ ተጨዋቾች መጥተዋል ፤ ከፍለህ በከፍተኛ ብር ካመጣሀቸው ደግሞ አሰልጣኞች ለእነሱ ነው ቀድመው የሚሰጡት ያው ምንም ማድረግ አይቻልም። ከዚህ በኋላ ጠንክሮ መስራት ነው ከእኛ የሚጠበቀው።

አምና በኢትዮዽያ ቡና ጥቂት የመሰለፍ እድል አግኝተህ ጥሩ ተንቀሳቅሰሀል። ከዛም ባለፈ ወደ ውጭ በመሄድ የሙከራ ጊዜ አሳልፈሀል። ከአምና የዘንድሮ እድገትህን እንዴት ታየዋለህ ?

ሚኪያስ ፡ ይህ አመት ለእኔ ጥሩ አይደለም እድገቴን የጎተተ እና ያዘገየብኝ ወቅት ነው። ፈጣን የነበረው እድገቴ መሄድ በሚገባው መጠን ማደግ አልቻለም ፤ ዘግይቷል። ለእድገቴ መዘግየት ደግሞ ችግሩ በእኔ ነው ብዬ አላስብም። የምገኘው በትልቅ ቡድን በመሆኑ የበዛ የመሰለፍ እድል ላላገኝ እንደምችል አምናለው። ሆኖም ግን እኛ ምንም የመሰለፍ እድል ሳይሰጠን ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ይመጣሉ። እነሱ እስሲታዩ ድረስ የእኛ እድገት ይቀጭጫል። ወደፊት ግን እድሉን እንደማገኝ አምናለው።


አቡበከር :
የአምና እና የዘንድሮ አቡበከር ልዩነት አለው። አምና በጣም ጥሩ ነበርኩ። ለእኔ መልካም አመት ነበር። ዘንድሮ በተወሰነ መልኩ ቡድናችን ጥሩ አይደለም። እኔም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ አልገኝም ፤ ምክንያቱም አሰልጣኝ ፓፒች በነበረበት ወቅት ከ18 ተጫዋች ዝርዝር ሁሉ እወጣ ነበር። አሁን ያለው አሰልጣኝ ደግሞ ለእኛ ጥሩ ነገር አለው። 18 ውስጥ እያካተተ ቀይሮም እያስገባኝ እየተጫወትኩ ነው። አንዳንዴ የማገኛቸውን እድሎች አለመጠቀም እኔ ጋር ችግር ቢኖርም ብዙ ጊዜ ተቀይሬ የምገባው ቡድናችን እየተመራ በመሆኑ ጫናውን መሸከም በእዚህ እድሜዬ ይከብዳል። አምና ቋሚ ሆኜ በተሰለፍኩባቸው አምስት ጨዋታዎች አምስት ጎል አስቆጥሬያለሁ። ያው የኳስ ባህርይ በመሆኑ ልምምዴን ጠንክሬ መስራት ነው።

ሚኪያስ ይህን መልስ ስትሰጠኝ ፊትህ ላይ መከፋትህ ይነበባል። ተስፋ የመቁረጥ ነገር አለ?

ሚኪያስ ፡ ምንም ተስፋ የሚያስቆርጠኝ የሚያሰጋኝ ነገር የለም። አቅሜን በደንብ አውቀዋለው ሆኖም የመጫወት እድል አለማግኘቴ መስራት በምችልበት በዚህ እድሜ አለመስራቴ እድገቴ መጓተቱ ቢያስቆጨኝም ወደ ፊት እድሉን እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ።

የመሰለፍ እድል አለማግኘትህ ችግሩ የት ጋር ነው ያለው ትላለህ?

ሚኪያስ : ዋናው በተለያየ ጊዜ አሰልጣኝ መቀያየሩ እና እኛ እያለን ብዙ ተጫዋች መፈረሙ ነው።  አዲስ ፈራሚዎቹ ራሳቸውን ለአሰልጣኙ እስኪያሳዩ ድረስ እኛ ቁጭ እንላለን። ይህ ነው የመጫወት እድል እንዳናገኝ ያደረገን። አሁን ያለው አሰልጣኝ ግን አሁን ቡድኑ እያወቀው ስለመጣ ወደፊት የመሰለፍ እድል ማግኘታችን አይቀርም።


መናገር የምትፈልገው ነገር ካለ?

ሚኪያስ : በዚህ እድሜህ ባልተጫወትክ ቁጥር ካለህ ነገር ላይ ብዙ ነገር ይቀንሳል ፤ የነበረህን ነገር ይነጥቅሀል። ነገር ግን እዚህ ትልቅ ቡድን በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ። በተለይ መስዑድ መሐመድን ከሚያክል ምርጥ ተጨዋች ጋር አብሮ መጫወቱ በራሱ ያስደስታል። ከእሱ ጋር ስትጫወት ብዙ ነገር ትማራለህ። በዚህ ደስተኛ ብሆንም መጫወት ባለመቻሌ ግን ይከፋኛል። ብዙ የመጫወቻ እድሜ አለኝ ፤ ራሴን አሻሽዬ ለመጫወት እሞክራለው ፤ አቅሜ የትም አይሄድብኝም።

በመጨረሻም ሁለቱም ተጫዋቶቾች ባስተላለፉት መልዕክት ክለቦች በታዳጊዎች ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ገለፀው በኢትዮዽያ ቡና ባለቸው ቆይታ ለሁሉም ነባር ተጫዋቾች የላቀ አክብሮት እንዳለቸው ተናግረዋል። በተለይ መስዑድ መሐመድ ለሚሰጣቸው ምክር እና የማበረታቻ ቃላት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *