​የወልዲያ ተጫዋቾች እና ክለቡ ነገ ይወያያሉ

የወልዲያ ስፖርት ክለብ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ከክለቡ አመራሮች ጋር ነገ ረፋድ አዲስ አበባ ላይ በክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ወልዲያ በከተማው ባለው ወቅታዊ ችግር እና ተጫዋቾቹ በሚያነሷቸው ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ባሳለፍነው ሳምንት ከአካባቢው ተጫዋቾች በስተቀር የክለቡ አብዛኛው ተጫዋቾች ከከተማው ለቀው ወደሚኖሩባቸው አካባቢዎች በማቅናታቸው ቡድኑ በጊዜያዊነት መበተኑ ይታወቃል። የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛው ዙር እስኪጠናቀቅ ድረስም የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በሙሉ እንደማይካሄዱ መገለፁ ይታወሳል።

የወልዲያ ስፖርት ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ” አሁን ነገሮች ተስተካክለው በወልዲያ ሁሉም ነገር የተረጋጋ በመሆኑ ወደ ካምፕ እንድትገቡ” የሚል የስልክ ፅሁፍ መልዕክት ወደ እያንዳንዱ የቡድኑ አባል እንደላኩላቸው ሰምተናል። ይህንን ተከትሎ የቡድኑ አባላት በፅሁፍ መልክት ወደ ካምፕ እንዲገቡ ትዕዛዝ መተላለፉ አግባብ እንዳልሆነ በመግለፅ የክለቡ ስራ አስኪያጅ ” ተጫዋቾቹ ያለ ክለቡ እውቅና እና ፍቃድ ጠፍተዋል ” በማለት ለሚዲያ የሰጡት መረጃ ትክክል አለመሆኑን ገልፀዋል። የክለቡ አመራሮች አዲስ አበባ በመምጣት ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በመነጋገር መተማመን ላይ ሲደርሱ ወደ ወልዲያ እንደሚያቀኑ ለክለቡ ማሳወቃቸውም ተነግሯል። በዚህ የተጫዋቾቹ ጥያቄ መሰረትም ነገ ረፋድ አዲስ አበባ ላይ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ እና አንድ የዞኑ ኃላፊ በተገኙበት ውይይት እንደሚያደርጉ ሰምተናል።

ነገ በሚኖረው ውይይት የክለቡ አመራሮች እና ተጫዋቾች በሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ዙርያ መተማመመን እና መግባባት ላይ ከደረሱ የቡድኑ አባላት ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ፤ ባለው ነገር መግባባት ላይ ካልደረሱ ደግሞ የክለቡ እጣፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ነው።

ወልዲያ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 11 ነጥቦች ሰብስቦ በ12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *