ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት በመነሳት ፋሲል ከተማን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከተማን አስተናግዶ በአቡበከር ነስሩ የማሸነፊያ ጎል 3-2 ድል ማድረግ ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡና ድሬደዋ ከተማን ከረታበት ስብስቡ ኤፍሬም ወንደሰንን እና መስዑድ መሀመድን በቶማስ ስምረቱ እና ክሪዚስቶን ንታንቢ የተካ ሲሆን ፋሲል ከተማዎች በበከላቸው በሜዳቸው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ካሸነፉበት የመጀመሪያ አሰላለፍ መሀል ጉዳት ባጋጣመው ዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ ኤፍሬም አለሙን ተጠቅመዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ወደግብ ከተደረጉ ስድስት ሙከራዎች አራቱ ወደግብ የተቀየሩበት ፣ የቀይ ካርድ የተመዘዘበት እና አከራካሪ የዳኛ ውሳኔዎች የታዩበት ነበር። ገና በሁለተኛው ደቂቃ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የሆኑት ፋሲሎች ሲሆኑ ሔኖክ ገምቴሳ ከመሀል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ ኳስ እና መረብን ያገናኘው የመስመር አጥቂው ኤርሚያስ ሀይሉ ነው። ኤርሚያስ አምናም ሁለቱ ክለቦች በተገናኙበት ወቅት ለፋሲል ብቸኛዋን የማሸነፊያዋ ግብ ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቡናዎች ሳሙኤል ሳኑሚ ሳጥን ውስጥ ከከድር ሀይረዲን ቀምቶ ወደ ሚኬል ሳማኬ በመቅረብ ባስቆጠራት ጎል አቻ መሆን ችለዋል። ተቀራራቢ በሆነ ፉክክር የቀጠለው ጨዋታ 14ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ጎል አስተናግዷል። ፋሲሎች 14ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም መሀል ሜዳ ላይ ከነጠቁትን ኳስ በቀኝ በኩል ሰብረው በመግባት በመሀመድ ናስር ለሁለተኛ ጊዜ ጨዋታውን መምራት ያስቻላቸውን ግብ አግኝተዋል። የፋሲል ከተማ ሁለት ግቦች ምንም እንኳን በግራ እና በቀኝ አቅጣጫ ከተከፈቱ ጥቃቶች የተገኙ ቢሆንም የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ኳስ መስርተው ከሜዳቸው በሚወጡበት እና የመስመር ተከላካዮቹም ከመከላከል ወረዳቸው በራቁበት ሰዐት በፍጥነት በተሰነጠቁ ኳሶች የተገኙ መሆናቸው ያመሳስላቸዋል።

ፋሲሎች ተመሳሳይ የጨዋታ ወቅቶችን እየጠበቁ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉ ሲሆን ባለሜዳዎቹ አቅም ያጣው የኳስ ቁጥጥራቸውን ለማጠናከር በማሳብ ኤልያስ ማሞን ጨዋታውን ከጀመረበት የመስመር አጥቂነት ሚና ወደ ተለመደው የአማካይ ክፍል በመመለስ እና ሳኑሚን በብቸኛ አጥቂነት ከፊት በማድረግ አምስት አማካዮች ያሉት የመሀል ክፍል እንዲኖራቸው አድርገዋል። ከዚህ በኃላም ቡድኑ የተሻለ ሆኖ ሲታይ ኢላማቸውን ባይጠብቁም 26ኛው ደቂቃ ላይ በኤልያስ ማሞ እንዲሁም 28ኛው ደቂቃ ላይ በሳምሶን ጥላሁን አማካይነት ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። የሳምሶንን ሙከራ ከተመለከትን ከሁለት ደቂቃ በኃላም ሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ በሳሙኤል ሳኑሚ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ በቀትታ በመምታት ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በመስመር አጥቂዎቻቸው እንቅስቃሴ አሁንም ጫና መፍጠራቸውን ያልቀነሱት ፋሲሎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ይህን ጥንካሬያቸውን የሚያሳጣ ክስተት ተፈጥሯል ። በቀኝ መስመር በኩል የቡድኑን ማጥቃት ሲመራ የነበረው ራምኬል ሎክ አስናቀ ሞገስን በክርኑ በመማታቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥቶታል። አንድ ሰው የጎደለባቸው ፋሲሎች በቀሩት ደቂቃዎች መሀመድ ናስርን ከፊት በማድረግ ኤርሚያስ ሀይሉን እና ኤፍሬም አለሙን በሔኖክ ገምቴሳ እና ያስር ሙገርዋ ግራ እና ቀኝ ሆነው መከላከሉን እንዲያግዙ አድርገዋል። የሚያስገርመው ነገር በዚህ ሁኔታ ላይም የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን መፍጠራቸውን አለማቆማቸው ነው። ከሁሉም በላይ ግን ትኩረት የሳበው ሔኖክ ገምቴሳ 42ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር አማካይነት ሚና ለተሰጠው ኤርሚያስ ሀይሉ ያሳለፈለት ድንገተኛ ኳስ ነበር። ኳሱ ኤርሚያስን የፍፁም ቅጣት ምት ክልሉን ለቆ ከወጣው ሀሪሰን ሄሱ ያገናኘው ሲሆን ኤርሚያስ ኳሱን ለማሳለፍ ሲሞክር ሀሪሰን አድኖበታል። ሆኖም ግብ ጠባቂው ኳሱን ሲያድን እጁን ተጠቅሟል በሚል የፋሲል ተጨዋቾች ከአልቢትሩ ጋር የተወዛገቡ ሲሆን ክስም እንዳስያዙ መመልከት ችለናል። ይህ ሁኔታ በካታንጋ ተቀምጠው ከነበሩ የአፄዎቹ ደጋፊዎች መሀል የተወሰኑቱ ጨዋታውን አቋርጠው እንዲወጡ ምክንያት የሆነ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያውን ያህል ፉክክር ያልታየበት ነበር። ባልተጠበቀ መልኩ ፋሲል ከተማዎች አሁንም ውጤቱን አስጠብቀው ከመውጣት ይልቅ ምርጫቸው ያደረጉት ተጋጣሚያቸውን ተጭነው የግብ ዕድሎችን መፍጠርን ነው። በዚህ ሂደትም ውስጥ የተከላካይ ክፍላቸውን እስከመሀል አስጠግተው ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ቡና የሜዳ አጋማሽ ላይ የሚገኙበትም አጋጣሚ ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከእረፍት መልስ የታየው የመጀመሪያ ሙከራም የታየው ከእንግዶቹ በኩል ነበር ። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ መሀመድ ናስር ከቡና ሳጥን ውስጥ አክርሮ ሞክሮ ኳስ በጎን ወደ ውጪ ወጥታበታለች።

የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረው ተስፈኛው አጥቂ አቡበከር ነስሩ ክሪዚስቶም ንታንቢን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባውም በዚሁ ደቂቃ ነበር። በሳምንቱ አጋማሽ ከሌላው የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ሚኪያስ መኮንን ጋር በመሆን በቂ የጨዋታ ጊዜ አለማግኘቱ ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረበት እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሮ የነበረው አቡበከር በገባ በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ በጨዋታው ልዩነት የፈጠረችን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል። አቡበከር አስናቀ ሞገስ ከግራ መስመር ያሻማውን እና ከድር ሀይረዲን በግንባሩ ለማውጣት ሞክሮ ያልተሳካለትን ኳስ ከጀርባው ነፃ ሆኖ በመገኘት ነበር በሳማኬ መረብ ላይ ያሳረፈው። ከግቡ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡና በአጨዋወትም ሆነ በተጨዋች ቅያሪዎቹ ጥንቃቄን የመረጠ መስሏል። ፋሲሎች አሁንም ወደፊት መሄዳቸውን የገፉበት በመሆኑ ባለሜዳዎቹ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ቢያገኙም በአግባቡ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። የጨዋታውም የፉክክር መንፈስ ከደቂቃ ወደ ደቂቃ የተዳከመ ሲሆን ሌሎች ጠንካራ ሙከራዎችም ሳይታዩበት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከተማ በ19 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀር ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ነጥብ አንሶ ወደ ሰባተኛ ደረጃ መጥቷል።

የአስልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ መሀመድ ኢብራሂም

ትንሽ ጫና ያለው ጨዋታ ነበር። ከድሬደዋ መልስ አሁን በሜዳችን ያገኘነው ነጥብ እንደ ድጎማ ነው። ለሚቀጥሉት ለቀሩን ጨዋታዎች የሚያበራታታ እና ቡድኑን ወደ ጥሩ መንፈስ የሚያመጣው ይመስለኛል። የቁጥር ብልጫው እንደ አንድ ጥቅም ነው። እግር ኳስ እንዲህ አይነት ነገሮች ስለማያጡት በታክቲክ ደረጃ የተለወጡ ነገሮችን ለውጠናል። በቁጥር ስለበለጥን የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች አስገብተን ተጭነን ለመጫወት ሙከራ አድርገናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ግን ፋሲል ጫና ፈጥሮ ተጫውቶ ያገኘውን አጋጣሚሚ ተጠቅሟል። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ የተሻለ ተንቀሳቅሰን ጎል ካገባን በኃላ የታክቲክ ለውጥ አድርገን ውጤቱን አስጠብቀን ወጥተናል።

አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

የዛሬው የሁለታችንም ጨዋታ ደጋፊውንም ተመልካቹንም ያዝናና ነበር። ቡና የነበረው የኳስ ቁጥጥር ጥሩ ነው። እኛም ራምኬል እስኪወጣ ያደረግነው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። የግብ ዕድሎችንም እንፈጥር ነበር። የፈጠርናቸውን የግብ ዕድሎችም ወደ ግብነት ቀይረናል። ከዚህ በፊት የነበረብን ችግርም ይሄ ነው። ቡና የተሻለ ተጫውቷል ቢሆንም በእንቅስቃሴ እኛ ማሸነፍ ነበረብን ። ነገር ግን አንዳንድ የተዛቡ እና ጥሩ ያልሆኑ የዳኝነት ውሳኔዎች ቡድናችንን እና አጨዋወቱን እንዲወርድ አድርገውታል። በቁጥር መጉደላችን እንደ አንድ ችግር ሆኖ ከሰባአምስት በመቶ በላይ የዳኛው ጫና ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *