የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲደረግ አዲስ አበባ እና ዓዲግራት ላይ ሁለት ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ይሄናል። ጨዋታዎቹን አስመልክተን ዳሰሳችንን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኃል።

መከላከያ ከ ሲዳማ ቡና

በሊጉ ድል አልባ ጉዞ ሲያደርግ የሰነበተው መከላከያ ወልዋሎን እና ድሬደዋ ከተማን አሸንፎ መነቃቃትን ካሳየ በኃላ በድጋሜ ወደ መቀዛቀዙ ተመልሷል። መከላከያ በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ያደረገው ጥር 6 ላይ ወደ ጅማ አምርቶ ከአባ ጅፋር ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ነበር። የ12ኛው እና የ13ኛው ሳምንት መርሀ ግብሮቹ ለሌላ ጊዜ በመሸጋገራቸውም ቡድኑ ከአይናችን ርቆ ሰንብቷል። በ13ኛው ሳምንት መቐለ ላይ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ ሽንፈት የገጠመው ሲዳማ ቡና ከስምንተኛ ሳምንት በፊት የነበረውን አስከፊ ጉዞ እያሻሻለ መምጣት ችሎ ነበር። ነገር ግን ይህ መሻሻሉ የታየው በሜዳው ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በማሸነፉ ነው። ከሜዳው ውጪ ግን አሁንም የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት እየጠበቀ ይገኛል ። ከመቐለው ሽንፈት በፊትም ወደ አዳማ እና ድሬደዋ ተጉዞ አንድ ነጥብ ነበር ይዞ የተመለሰው። ዛሬ ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ የመሀል ዳኝነት የሚመራው ጨዋታ አስራ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መከላከያን ሁለት ደረጃዎችን እንዲያሻሻል የሚረዳው ሲሆን ምንም የተላለፈ ጨዋታ ካልገጠማቸው የሊጉ ግማሽ ክለቦች መሀከል የሆነው ሲዳማ ቡና ውጤት ከቀናው ደሞ የፋሲል ከተማን የስድስተኛነት ደረጃ የሚረከብ ይሆናል።

የመከላከያው የመሀል ተከላካይ አዲሱ ተስፋዬ አሁንም ከጉዳት ያለተመለሰ ሲሄን ሌላኛው የኃላ መስመር ተሰላፊ ቴዎድሮስ በቀለም ለጨዋታው አይደርስም። ከዚህ ውጪ መከላከያዎች የሳሙኤል ታዬን አገልግሎት ከጉዳት መልስ እንደሚያገኙ ይጠበቃል። ፍቅሩ ወደሳ ፣ አብዱለጢፍ መሀመድ እና ፍፁም ተፈሪ ደግሞ በሲዳማ ቡና በኩል በጉዳት ዝርዝር ውስጥ የተገኙ ተጨዋቾች ናቸው።

መከላከያም ሆነ ሲዳማ የምጥቃት እንቅስቃሲያቸው በዋነኛነት የመስመር ተጨዋቾቻቸውን ማዕከል ያደረገ ነው። ነገር ግን ከአሰላለፍ ልዩነታቸው ጀምሮ በአጨዋወታቸው ምክንያት የመስመር ተጨዋቾቻቸውን በማጥቃት ሂደት የሚጠቀሙበት መንገድ የተለያየ ነው። የመከላከያ ጥቃት በዋናነት ከግራ እና ከቀኝ የሚነሳ ቢሆንም ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ከሚሰጠው አቀራረቡ ለመሀል አማካዮች ቀርበው የሚጫወቱት የመመር አማካዮች ከተጋጣሚ ሜዳ እጅግ ርቀው የሚታዩ በመሆናቸው የማጥቃት እንቅስቃሴው መነሻ እንጂ መድረሻ አይደሉም። የእንቅስቃሴው መቋጫ የሚሆኑት ወደ እነሱ ቀርበው ኳስ ለመቀበል የሚሞክሩት በሀለተኛ አጥቂነት የሚሰለፉ ተጨዋቾች እና የቡድኑ አይን የሆውነ የፊት አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ናቸው። ወደ ሲዳማ ቡና ስንመጣ ደግሞ እንደተጋጣሚው ሁሉ ከግራ እና ከቀኝ የሚነሱ ኳሶችን የመጨረሻ ዕድል ለመፍጠሪያነት ቢጠቀምም ከመከላከያ በተለየ የእንቅስቃሴው መጨረሻ የሚሆኑት የመስመር አጥቂዎቹ ናቸው። ከአማካይ ክፍሉም ሆነ ከኃላ የሚነሱ ኳሶች እነዚህ ተጨዋቾች ጋር ሲደርስ ፍጥነቱ የሚጨምር ሲሆን በተለይ የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ላስጠጋ ቡድን እጅግ ፈታኝ ሆኖ ይታያል። በዚህ መሰረት በዛሬው ጨዋታ የመከላከያ የመስመር አማካዮች እንደ እነ ኤቤል ከበደ እና መስፍን ኪዳኔ አይነት ተጨዋቾች ከፊት መስመር አጥቂዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ተጠባቂ ነው። እዚህ ላይ ቡድኑ ከምንይሉ ወንድሙ ጀርባ ከአማካይ መስመሩ ጋር የሚገናኝ ተጨዋችን ሚና በአቅሌሲያስ ግርማ ፣ ማራኪ ወርቁ ፣ የተሻ ግዛው እና ሳሙኤል ሳሊሶ ለመተግበር ሲሞክር ቢታይም ወጥነት ያለው ጥምረት አለመፍጠሩ እየጎዳው እንዳለ መናገር ይቻላል። በተመሳሳይ አማካይ ክፍሉ ላይ ተደጋጋሚ ጥምረትን ለመፍጠር ሲቸገር የሚታየው ሲዳማ ቡና አዲስ ግደይ እና ሀብታሙ ገዛሀኝ ከሚደርሷቸው ኳሶች ከጤሩ የመስመር ተከላካዬች ጋር በመፋለም አጥብበው ወደ ፊት አጥቂው ባዬ ገዛሀኝ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፍሬ ያለው አጋጣሚን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ሀዋሳ ከተማ
በፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው መሪነት የሚደረገው የዓዲግራቱ ጨዋታ ሜዳው ላይ ውጤት ማምጣት የከበደው ወልዋሎ ዓ.ዩን እስካሁን ከሜዳው ውጪ ድል ካልቀናው ሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል። ወልዋሎ ዓ.ዩ አሁንም ቁልቁል መጓዙን ቀጥሎበታል። በርካታ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ የሰነበተው ክለቡ ሳምንት አዳማ ላይ የደረሰበት ሽንፈት በአመቱ አራተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚህ በፊት በጅማ አባ ጅፋር እና በደደቢት እንደገጠሙት ሽንፈቶች ሁሉ ይሄኛውም ሶስት ጎሎችን ያስተናገደበት ነበር። ወልዋሎ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሽንፈት ባይገጥመውም እስካሁን ማሸነፍ የቻለው ኢትዮጵያ ቡናን ባስተናገደበት የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ብቻ ነበር። በሌላ በኩል ሀዋሳ ላይ የነበረውን ጥንካሬም እያጣ የመጣው ሀዋሳ ከተማ ከሜዳ ውጪ ያለውን ሪከርድም ማሻሻል ባለመቻሉ ተፎካካሪነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ይገኛል። በርግጥ እስከ አምስተኛው ሳምንት ድረስ በሜዳቸው ባስተናገዱት ክለቦች ሁሉ ሲሸነፍ ቆይቶ ከዛ በኃላ በነበሩት የመከላከያ እና የፋሲል ከተማ ጨዋታዎች ነጥብ ቢጋራም ሲዳማ ላይ ደግሞ በአዲስ ግደይ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ዳግም ወደ ሽንፈት ተመልሷል። የዛሬው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመሸናነፍ ከተጠናቀቀ አስራሶስት ነጥቦች ላይ የቆመው ወልዋሎንም ሆነ ከተጋጣሚው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ የተቀመጠውን ሀዋሳ ከተማን እስከ ሶስት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ ዕድል የሚሰጣቸው ይሆናል።

ዋልዋሎ ዓ.ዩ ሙሉአለም ጥላሁንን እና ኤፍሬም ጌታቸውን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን በቅጣት ከማይኖረው ፍሬው ሰለሞን በተጨማሪ የሀዋሳ ከተማዎቹ ያቡን ዊልያም ፣ ሳዲቅ ሴቾ እና ተክለማርያም ሻንቆም ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ሰምተናል። በሌላ በኩል የረጅም ጉዳት ገጥሟቸው የነበሩት ዳንኤል ደርቤ እና ላውረንስ ላርቴም በማገገም ላይ ቢሆኑም ለጨዋታው ብቁ እንደማይሆኑ ተነግሯል።

ይህ ጨዋታ በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች መሀከል ሜዳቸውም ላይ ሆነ ከሜዳቸው ውጪ መሉ ለሙሉ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ መሰረት አድረገው ከሚጫወቱ ክለቦች መሀከል ሁለቱን የሚያገናኝ ይሆናል። ዛሬም ሁለቱም ክለቦች በተቻላቸው መጠን የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ በማስጠጋት በበርካታ የኳስ ቅብብሎች እስከ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ድረስ ዘልቆ ለመግባት በመሞከር እንደሚፋለሙ ይጠበቃል። በርግጥ ይህን በትክክል ለማድረግ የመጫወቻ ሜዳው ምቹ እንደማይሆን በተመሳሳይ አቀራረብ እስካሁን የዘለቁት የወልዋሎዎችን ደካማ የዓዲግራት ውጤቶች መመልከት በቂ ነው። የሆነ ሆኖ ግን ዛሬም ቡድኖቹ በአጨዋወታቸው ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። አሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሄርን ካሰናበተ በኃላ አዳማ ላይ የሙሉአለም ጥላሁንን ጉዳት ተከትሎ ጨዋታውን ሲጀምር አምስት የሚደርሱ ተጨዋቾችን ቦታ ያሸጋሸገው ወልዋሎ በሁለተኛው አጋማሽ ተጨዋቾቹን ቀድሞ ወደ ሚታወቁበት ቦታቸው መልሶ ታይቷል። ይህ ክስተት ቡድኑ በጨዋታው ወጥነት ያላቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን እንዳያደርግ አንዱ ምክንያት ነበር። በሀዋሳ ከተማ በኩልም ተመሳሳይ ችግር ይታያል። ጉዳት እና ቅጣት የማያጣው የቡድኑ ስብስብ እንደ ተጋጣሚው በአንድ ጨዋታ በርካታ ሽግሽጎችን ባያደርግም በወጥነት የሚጠቀማቸው አስራአንድ ተጨዋቾችን አለማግኘቱ ከፍተኛ መግባባትን ለሚጠይቀው አጨዋወቱ የተመቸ እንዳይሆን አድርጎታል። በነዚህ ችግሮች ውስጥ የሚገኙት ሁለት ቡድኖች ዛሬ ሲገናኙ የአማካይ መስመራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለአሸናፊነታቸው ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በዚህም የሙሉአለም ረጋሳ እና ታፈሰ ሰለሞን ከኳስ ጋር በሚኖር እንቅስቃሴ የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር በልምድ እና በክህሎት ላይ የተመሰረት ጥምረት ከአፈወርቅ ሀይሉ እና ዋለልኝ ገብሬ በታታሪነት የተሞላ እና ከኳስ ውጪ የተጋጣሚን አማካይ ክፍል ኳስ ለማስጣል ምቹ የሆነ የአማካይ መስመር እንቅስቃሴ ጋር የሚገናኝበት መሆኑ ትኩረትን ይስባል። ሆኖም የነዚህ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች ከጀርባቸው ከሚኖሩ የተከላካይ አማካዮች እንዲሁም ከመስመር አጥቂዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው የቦታ አያያዝ ርቀት እና የቅብብል ስኬት ጨዋታውን ለማሸነፍ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል። በአንፃሩ የሁለቱም ቡድኖች የአጨራረስ ችግር በጨዋታው ዕድሎች እንኳን ቢፈጠሩ ግቦችን የማስቆጠር ብቃታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። ከዚህ ውጪ በተለይ ቀድሞ ግብ የሚያቆጥር ቡድን ተጋጣሚው በኳስ ቁጥጥሩ ይበልጥ ገፍቶ ግብ ለማግኘት ከሚያደርገው በጉጉት የተሞላ እንቅስቃሴ አንፃር የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሊያገኝ የሚችልበት ጨዋታም እንደሆነ ይገመታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *