ሞሮኮ – የቻን 2018 ቻምፒዮን!

ሞሮኮ የቶታል አፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ያሸነፈች የመጀመሪያዋ አዘጋጅ ሃገር ሆናለች፡፡ ሞሮኮ በፍፃሜው ናይጄሪያን 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት ነው የውድድሩን ዋንጫ ያነሳችው፡፡ የፍፃሜው ጨዋታ ጋምቢያው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ የመራ ሲሆን ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ አራተኛ ዳኛ ነበር፡፡

የሞሮኮው አሰልጣኝ ጀማል ሰላሚ በ4-2-3-1 የጨዋታ አቀራረባቸው በፍፃሜም የተገበሩ ሲሆን ለማጥቃት በማሰብ የናይጄሪያው አሰልጣኝ ሳሊሱ የሱፍ 4-3-3 ተጠቅመው ነበር፡፡ ሆኖም ካዛብላንካ በሚገኘው ስታደ መሃመድ አምስተኛ በተደረገው ጨዋታ ሞሮኮ ተጋጣሚዋ ላይ የጨዋታ ብልጫን ወስዳለች፡፡ ዛካሪያ ሃድራፍ ሞሮኮን በ45ኛው ደቂቃ መሪ ሲያደርግ አመቻችቶ ያቀበለው አብደልጃሊል ጅቢራ ነበር፡፡ ሱፐር ኢግልሶች ከእረፍት መልስ ኢንጂ ሞሰስ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በመውጣቱ ይበልጥ ጨዋታው እንዲከብዳቸው አድርጓል፡፡ የዋይዳድ ካዛብላንካው የአጥቂ አማካይ ዋሊድ ኤል ካርቲ በ61ኛው ደቂቃ መሪነቱን ወደ ሁለት ሲያሰፋ ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ሃድራፍ ሶስተኛው አክሏል፡፡ ልማደኛው አጥቂ እና ለውድድሩ ፍፁም ልዩ የነበረው አዩብ ኤል ካቢ በ73ኛው ደቂቃ የማሳረጊያ ግቡን ከመረብ አዋህዷል፡፡

ቅዳሜ ሱዳን ሊቢያን በመለያ ምት 4-2 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ አንድ አቻ በተጠናቀቀው መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሱዳን በዋለልዲን መሃመድ የ8ተኛ ግብ ለረጅም ግዜ ስትመራ ቆይታለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያቸውን ላይ ጫናን አሳድረው የተጫዋቱት ሊቢያዎች የሱዳኑ ግብ ጠባቂ አክራም ኤል ሃዲ ያመለጠውን ኳስ ሳልም አብሎ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሃገሩን በ84ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል፡፡ አሸናፊው ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት በሱዳን በኩል ሙሃናድ ጣሂር ኦስማን፣ አታሂር ኤል-ጣሂር፣ አህመድ አደም መሃመድ እና መአዝ አብደልራህማን ሲያቆጥሩ ሙፍታህ ታክታክ እና አብደልሰላም አል-ፊቶሪ በሊቢያ በኩል የተሰጠውን የመለያ ምት ወደ ግብነት ቀይረዋል፡፡ ነገር ግን ኤል መህዲ አል ማስሪ እና ሳለም አብሎ መለያ ምቶቻቸውን አምክነዋል፡፡ የሱዳኑ ግብ ጠባቂ ኤል ሃዲ የአብሎን ምት በማዳን ሃገሩን አሸናፊ አድርጓል፡፡

አዩብ ኤል ካቢ የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ (በ9 ግቦች እንዲሁም) እና ተጫዋቾች ሆኖ መርጧል፡፡ ለአምስተኛ ግዜ በተዘጋጀው ቻንም እንደቀደሙት ውድድሮች ሁሉ አዲስ አሸናፊ ከመገኙቱ አልፎ አዘጋጅ ሃገር ለመጀመሪያ ግዜ ዋንጫውን አሸንፏል፡፡ በካዛብላንካ፣ ታንገ፣ ማራካሽ እና አጋድር ጨዋታዎቹን ሞሮኮ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ችላለች፡፡

ያለፉት 100 ቀናት ለሞሮኮ ልዩ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የሞሮኮ ክለብ የሆነው ዋይዳድ ካዛብላንካ የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግን ከ25 ዓመታት በኃላ ሲያሸንፍ የአትላስ አንበሶቹ ኮትዲቯርን ከሜዳቸው ውጪ በመርታት ከ1998 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህም በላይ በጥር ወር የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ካቀረቡ ሃገራት መካከልም ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በ2020 የሚስተናገደውን ቻን ለማስተናገድ የካፍ አርማን ከፕሬዝደንት አህመድ አህመድ እጅ የፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት ጁኒይዲ ባሻ ተቀብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *