የጨዋታ ህግጋት [1] – ቅጣት ምቶች እና ከጨዋታ ውጪ

በቅርብ ጊዜያት በዳኞች ላይ እየደረሱ የሚገኙ ተቃውሞዎች እና ቅሬታዎች እየጨመሩ መጥተዋል። አሰልጣኞች በተለይም ከጨዋታ በኃላ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ስለዳኛ ሳያነሱም ሆነ ቅሬታን ሳያቀርቡ አያልፉም።

በሀገራችን እግር ኳስ የሚስተዋሉ የዳኝነት ችግሮች በሁለት መክፈል ይቻላል። የመጀመሪያው የዳኞች ጨዋታን በአግባቡ መምራት እና መቆጣጠር አለመቻል ነው። ህጉን በቀጥታ ከመተርጎም እና ተፈፃሚነቱን ከማረጋገጥ ይልቅ እንደ ሁኔታው እና ተመሳሳይ ባልሆነ መልኩ መዳኘታቸው ጥያቄ የሚያጭር ነው። ከአዳዲስ ህጎች ጋር አለመላመድ፣ የወረደ አካል ብቃት እና የተለያዩ አካላት ተፅዕኖ ስር መውደቅ ለእነዚህ መንስኤ ተብለው ይጠቀሳሉ።

ሁለተኛው ችግር እና ይህን አምድ እንድናዘጋጅ ዋና ምክንያት የሆነው አሰልጣኞች ፣ተጫዋቾች እና ተመልካቾች በአጠቃላይ የእግር ኳስን ህግጋት ጠንቅቆ ካለማወቅ የተነሳ በዳኞች ላይ የሚያነሱት መጠኑን ያለፈ ተቃውሞ እና ጫና ነው። አሰልጣኞች ሽንፈታቸውን በዳኞች ላይ ያላክካሉ፤ ተጫዋቾች ዳኞችን ይገፈትራሉ ወይም በሃይል ይከባሉ፤ እንደዚሁም አንዳንድ ደጋፊዎች ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን ዳኞች ላይ ይሰነዝራሉ።

ህግጋቱን በአግባቡ መረዳት ምክንያታዊ የሆኑ ተቃውሞ እና ጥያቄን ለማንሳት ይረዳል ፤ አላስፈላጊ ከሆኑ ግራ መጋባቶችም ያድናል። የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል የሆነው ፊፋ ‘Rule of the Game’ በሚለው የደንብ መፅሃፋ የዳኝነት ሃላፊነትን በጥሩ ሁኔታ አስቀምጥቶታል። እኛም በተለያዩ ክፍሎች በመክፈል እነዚህን ደንቦች እንመለከታለን። በቀጣይ ጊዜያትም በባለሙያዎች ታግዞ በጥልቀት እና በስፋት የምናቀርብ ይሆናል።
የጨዋታ ውጪ (Offside) እና ቅጣት ምት ህግጋት በዚህ ክፍል እንዲህ ቀርበዋል።


(ከጨዋታ ውጪ (Offside)

ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ መሆን በራሱ ጥፋት አይደለም በማለት ይጀመራል የፊፋ የደንብ መፅሀፍ።

አንድ ተጫዋች ከጨዋታ ውጪ የሚባለው መቼ ነው?

1) ለተጋጣሚው ግብ ከኳሱም ሆነ ከመጨረሻ ሁለተኛ (ከእርሱ ኃላ) ላይ ካለ ተጫዋች ቀድሞ ሲገኝ።

መቼ ከጨዋታ ውጪ አይባልም?

– በራሱ የጨዋታ አጋማሽ ሲገኝ
– ከመጨረሻ ተጫዋች/ቾች እኩል ቦታ (መስመር) ከቆመ

ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ጨዋታው የሚቋረጠው መቼ ነው?

ከጨዋታ ውጪ የሚገኝ ተጫዋች ኳሷን ለመንካት ጥረት ካደረገ ፣ ተጋጣሚ ተጫዋች እንዳይነካ ጣልቃ ከገባ ወይንም ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ የተለየ ዕድል (advantage) ካገኘ። የመስመር ዳኛው እነዚህን በማጤን ለዋናው ዳኛ ምልክት ይሰጣል።

ከጨዋታ ውጪ የማይባለውስ መቼ ነው?

-ተጫዋቹ ምንም እንኳን ከጨዋታ ውጪ ቢሆንም እንኳን ኳሱን ከመልስ ምት፣ ከእጅ ውርወራ እና ከማዕዘን ምት ከተቀበለ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ አይቀጣም።

አንድ ተጫዋች ከጨዋታ ውጪ ነው ከተባለ በኃላ በክስተቱ ቦታ ላይ ቅጣት ምት ተስጥቶ ጨዋታው ይቀጥላል።


ቅጣት ምቶች

ቀጥተኛ ቅጣት ምት 7 የህግ ጥሰቶች ሲፈፀሙ የሚሰጥ ነው። እነዚህ ጥፋቶች በዳኛው እይታ ያልተገባ እና ጥንቃቄ የጎደለው ተብሎ ሲታሰብ ጥፋት ይሰጣል።

ጥፋቶቹ:

– ተጋጣሚን መማታት ወይንም ለመማታት መሞከር (ተጋጣሚውን አላገኘውም የሚለው ምክንያት አይሰራም)

– ተጋጣሚን መጥለፍ አልያም ለመጥለፍ መሞከር

– ተጋጣሚ ላይ መዝለል (ለግንባር ኳስ ሲሻሙ)

– በኃይል ሮጦ ተጋጣሚን መግጨት

– ተጋጣሚን ለመደብደብ መሞከር

– ተጋጣሚን መግፋት

– ታክል ማድረግ

በተጨማሪም

– የተጫዋች ማልያን መጎተት
– ተጋጣሚ ላይ ምራቅን መትፋት እና
– ሆን ብሎ ኳስ በእጅ ሲነካ

እነዚህ ሲፈፀሙ ጥፋቱ በተሰራበት ቦታ ቅጣት ምት ይሰጣል።

ከላይ የተዘረዘሩት 10 ጥፋቶች በ16:50 ሳጥን ውስጥ ከተፈፀሙ የፍፁም ቅጣት ምት ይሰጣል።

ቀጥተኛ ያልሆነ ቅጣት ምት (Indirect free kick)

ቀጥተኛ ያልሆነ ምት ከቀጥተኛ ምት የሚለየው በአንድ ጊዜ ወደ ግብ መምታትን አለማካተቱ ነው። ይህ ምትን ለመምታት ሁለት ተጫዋቾች ኳሱ ጋር ይቆማሉ። አንዱ ተጫዋች ከጎኑ ላለው ጓደኛ ያቀብላል። ከዛም በኃላ ነው ኳሱ የሚመታው።

እንደዚህ አይነት ምት መቼ ነው የሚሰጠው

ግብ ጠባቂው:

– ከ6 ሰከንድ በላይ ኳሱን በእጁ ይዞ ካቆየ (ኳሱን ከመልቀቁ በፊት)

– ኳሱን ከለቀቀ በኃላ ሌላ ተጫዋች ሳይነካው መልሶ ከያዘ

– የቡድን አጋሩ እያወቀ በእግሩ ያቀበለውን ኳስ በእጁ ከያዘ

– ከእጅ ውርወራ በቀጥታ የመጣን ኳስ በእጁ ከያዘ

ከዚህም በተጨማሪ በዳኛው እይታ አንድ ተጫዋች:

– ከመጠን በላይ በኃይል ከተጫወተ
– የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ከገታ
– ግብ ጠባቂው ኳሱን እንዳይለቅ ከገታ
– ጨዋታው እንዲቋረጥ የሚያደርግ ማንኛውም አይነት ጥፋት ሲሰራ እና ጨዋታው ካቆመበት ሲቀጥል ጥፋቱ በተሰራበት ቦታ በመመታት ይቀጥላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *