​ይድነቃቸው ተሰማ – ታላቁ የአስተዳደር ሰው!

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ – የአፍሪካ እግር ኳስ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ የነበረውን ትግል በምን መልኩ መሩት?


ቶም ደንሞር ለብሊዛርድ እንደፃፈው
(ሁሉም ዘመናት የተጠቀሱት በአውሮፓውያን አቆጣጠር ነው)


“በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ አፍሪካ አንድ እና የማትከፋፈል መሆኗን በማረጋጠጥ፣ የአፍሪካን አንድነት ለማስጠበቅ በጋራ እንድንሰራ፣ በእግርኳሳችን እና በአጠቃላይ የኑሮ ገጽታችን ላይ የተንሰራፋውን ባዕድ አምልኮ፣ ጎሰኝነትና ሌሎች የምንገለልባቸውን ነገሮች በሙሉ እንድናወግዝ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡”

የወቅቱ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሽን (ካፍ) ፕሬዘዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በ1974 በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተናገሩት፡፡


በ1936 የክረምቱ ወቅት ቀዳማዊ ኅይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ በሲዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ በተደረገው የመንግስታቱ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አስደናቂ ንግግር አደረጉ፡፡ ንጉሱ አገራቸው በ1935 በኢጣሊያ ከተወረረችበት ጊዜ አንስቶ ዜጎቿ በማያባራ ጭካኔያዊ አገዛዝ ስር እንደሆኑ በማሳወቅ ወራሪው የፋሺሽት መንግስት አሰቃቂ በሆነና ህግን በተላለፈ ሁኔታ በአውሮፕላን የጦር መሳሪያ ጥቃት የሰውን ህይወት በጅምላ የሚቀጥፍ ሰው-በላ እርምጃን በመላው የአገሪቱ ክፍሎች እየወሰደ እንደሆነ አጋለጡ፡፡ የንጉሡ ንግግር በአለምአቀፍ ደረጃ የጋራ ደህንነት መርህን በማስጠበቅ ረገድ እምብዛም የማያስተማምነውን ማህበር ህልውና የተፈታተነ እና በመላው አለም የመነጋገሪያ ርዕስም የፈጠረ ነበር፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላ ቀዳማዊ ኀይለስላሴ በ1937 ታይም መጽሔት “የአመቱ ምርጥ ሰው” በሚል መረጣቸው፡፡

የመንግስታቱ ማህበር በኢጣሊያ መንግስት ላይ የጠነከረ እና ቋሚ የሆነ የእርምት ትዕዛዝ ባለመስጠቱ የአፄው ንግግር ያመጣው ጊዜያዊና መጠነኛ ለውጥን ብቻ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የንጉሱ ታማኝ ደጋፊዎች በየካቲት 19 ቀን 1937 በወቅቱ የፋሺስቱ አገረ ገዢ ግራዚያኒ ላይ የከሸፈ የግድያ ሙከራ አደረጉ፡፡

ከአደጋው በኋላ የፋሽስታውያኑ ጭካኔ መጠን ጫፍ ደረሰ፡፡ ከተማዋን የተቆጣጠሯት ጣልያናውያን ወታደሮች ዘግናኝ በሆነ መንገድ በስለታማ መሳሪያዎች፣ ጠመንጃ እና የነዳጅ ፈንጂዎችን በመጠቀም በሁለት ቀናት ውስጥ ሰላሳ ሺህ በሚሆኑ ንፁሀን ዜጎች ላይ ዘግናኝ እልቂትን ፈጸሙ፡፡ አቶ ይድነቃቸው ተሰማና ቤተሰቡ በአዲስ አበባ ፋሽስቶቹ በከበቡት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ይኖሩ በነበሩት ግሪካውያኖች ዘንድ መሸሸጊያን አገኙ፡፡ በጊዜው ወታደሮቹ የውጭ ዜጎችን ቤት ዘልቀው  ስለማያስሱ የይድነቃቸው ቤተሰብ ከዘግናኙ ጭፍጨፋ ሊተርፍ ቻለ፡፡

የበቀል እርምጃው የተወሰደው ሁለቱ ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ በወረወሩት ቦምብ ሰበብ ነበር፡፡ ከቦንቡ ወርዋሪዎች አንዱ አብርሃ ደቦጭ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የእግር ኳስ ጨዋታ መካሄድ ሲጀምር ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡ ከይድነቃቸው ጋር የነበራቸው ትውውቅም ከዚያ ጊዜ የጀመረ ነው፡፡ በወራሪው የአገዛዝ ዘመን እግር ኳስ ቀጥተኛው የቅራኔዎች መነሻ ሆኖ ሰንብቷል፡፡  በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታ መለመድ የጀመረው ከወረራው አገዛዝ ቀደም ብሎ ነው፡፡ በ1935 የፈረንሳይ ጎብኚ የባህር ሐይል ቡድን በዋና ከተማዋ ከሚገኙ ተጫዋቾች የተውጣጡ ምርጦች ስብስብን ሲገጥም በአገሪቷ ውስጥ እግር ኳስ እንዲስፋፋ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከቱት አቶ ይድነቃቸው ከስብስቡ ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ ይህ ቡድን በርካታ የዝግጅት ጨዋታዎችን ሲያደርግ በጊዜው ይዳኛቸው ስለነበረው ሰው ሁኔታ አቶ ይድነቃቸው እንዲህ ይላሉ። ”አንድ ግዙፍ ጥቁር አሜሪካዊ ሰው በእግሩ ቆሞ ሊዳኘን ስላልቻለ በፈረስ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ይዳኘን ነበር፡፡” ይላሉ፡፡ ያ የቡድን ስብስብ የተመሰረተው ከከተማዋ ወጣቶች፣ ከአገሬው ተወላጆች እና ከሌሎች ስደተኛ ዜጎች ነበር፡፡

በ1935 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች የተዋቀረ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰኘ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በከተማዋ ይገኙ ከነበሩት የአርመንና የግሪክ ቡድኖች ጋር ግጥሚያዎችን ያደርግ ነበር፡፡ እግር ኳስ በኢትዮጵያ ከአስር አመታት የጨቅላነት ቆይታ በኋላ ትንሽ እድገትን እያሳየ መጣ፡፡ ነገርግን በስድስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የጣሊያን ወረራ ተጀመረና ኢትዮጵያ ከየኢጣልያ-ሶማሊ እና የኢጣልያ-ኤርትራ ጋር ተደባልቃ የኢጣሊያ-ምስራቅ አፍሪካ እንዲመሠሰረት ተፈለገ፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስም ከማህበረሰቡና ከተቀሩት ባህላዊ እሴቶቹ ጋር በመሆን ለከፍተኛ ጥቃት ተጋላጭ ሆነ፡፡ የጣሊያን ወራሪዎች እግርኳስን-እርስ በእርሳቸው ይጫወቱ የነበረ ሲሆን ሁሉም የጊዜው የኢትዮጵያውያን ቡድኖች ደግሞ እንዲበተኑ ተደረገ፡፡ አቶ ይድነቃቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክን በሚያወሳ መጽሐፍ ላይ እንዳስቀመጡት “የኳስ ጉጉት የነበራቸው አትዮጵያውያን የኳስ ፍቅራቸውን እና ናፍቆታቸውን ለመወጣት በመደበቂያ ቦታዎች በመሆን ጣልያኖቹ ሲጫወቱ ይመለከቷቸው ነበር፡፡” ይላሉ፡፡ ወራሪው ኃይል በባህላዊ ጉዳዮች የዘር መከፋፈልን በግዛት በመወሰን የመምራት ስርዓትን በመከተሉ እግርኳስም የዚህ አስተዳደራዊ ስርአት ሰለባ ነበር ፡፡

በ1937 ዓ.ም “የሀገሬው ተወላጆች የስፖርት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት” የሚሰኝ ተቋም በጣሊያናዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ አማካኝነት ተከፈተ፡፡ የውሳኔው ፖለቲካዊ ፋይዳም ግልጽ ነበር፡፡ አቶ ይድነቃቸው ሲያብራሩት ”ኢትዮጵያውያን ቢያንስ በድጋሚ እግርኳስን የሚጫወቱበት እድልን አገኙ። በውሳኔው የራሳችንን ጨዋታ በኛው ሜዳ እናደርጋለን፤ ሁሉም ይከፋፈላል፤ የተለያዩ ሜዳዎችን እንጠቀማለን፤ የተለያዩ ደጋፊዎች ይመለከቱናል፤ ለብስክሌት ተወዳዳሪዎች እንኳ የሚሰጣቸው መቀመጫዎች የተለያዩ ነበሩ፡፡” ብለዋል።

የይድነቃቸው ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ የጣልያኖች እንዲሆንና ስሙም ሊቶሪዮ ውቤ ሰፈር እንዲባል ተደረጎ ነበር፡፡ በጊዜው የ16 አመት ታዳጊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው በስፖርት ቢሮው ውስጥ የእግርኳስ ህግና ደንቦችን የመተርጎም ስራ ጀመሩ፡፡ ምንም እንኳ እድሜያቸው ትንሽ የነበረ ቢሆንም ”የጣሊያኖቹ ፖሊሲ ሞራላዊ ዝርክርክነት ይታይበት እንደነበረ ለመረዳት አልተቸገርኩም፡፡” ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ የጽህፈት ቤቱ መመስረት ዋነኛ አላማም የስፖርት መርሆዎች ላይ ከመስራት ይልቅ ማህበረሰቡን የመነጣጠልና የመከፋፈል ሒደት ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡ በመጫወቻ ስፍራው ውስጥ ሁለት አነስተኛ የአገሬው ቡድኖች “የነጮች-ብቻ” በሆነው ሜዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ የጣሊያን ዳኞችና ተመልካቾች ተጫዋቾቹ እርስ በርሳቸው እንዲደባደቡ ይገፏፏቸው ነበር፡፡ ይህን ሁኔታ አቶ ይድነቃቸው ሲያወሱም እንዲህ ይላሉ፡፡ ”ለአመጽ በተነሳሳ የቡድን ህብረት ድጋፍና አበረታች ሒደት በጥንታዊቷ ሮም ህዝብ ፊት በትግል መድረክ ላይ የሚጋጠሙትን ግላዲያተሮች ሆንን፡፡ ይህም ሁኔታ ወደ አንድ አሰገራሚ የባላንጣነት ስሜት ወሰደን፡፡ ስለዚህም በሜዳ ውስጥ ኃያል ጦርነትን ፈጠርን፡፡ ጣልያኖቹ የሚጮሁበት ወይም የሚያጓሩበት ጊዜ ነበራቸው፡፡ ኳሱን ሳንጫወት ቁስላችንን እየጠረግን ወደ ቤታችን ሄድን፡፡” ወጣቱ ይድነቃቸው ኳስን እየተጫወተ በስፖርት አስተዳደር ዘርፍ በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጪ እኩልነትን ለማስፈን፣ በፍትህ መርህ በኩል ደግሞ ፅኑ እና የማያወላውል እምነትን በመያዝ አውዳሚዉንና ለጣልያኖቹ ጥቅም የቆመውን የእግርኳስ ጨዋታ ህግና ደንብ ለማስወገድ በቁርጠኝነት የመጋፈጥን ልምድ እያዳበረና እያጎለበተ የጣልያን አገዛዝ እስካበቃበት እ.ኤ.አ. 1941 ዓ.ም ድረስ ቆየ፡፡

የጣልያን የግዛት ጊዜ እንዳበቃ አቶ ይድነቃቸው በፍጥነት በእግርኳሱ ማህበረሰብ ዘንድ ስመጥሩ እና ነባር ተጫዋች፣ አሰልጣኝ፣ ዳኛ እና አስተዳደር በመሆን በኢትዮጵያ ስፖርት በተለይም በእግርኳሱ የአገሪቷ ምልክት ሆኑ፡፡ የተለየ የማስተባበር ክህሎትን፣ የፖለቲካ አረዳድ፣ ኳስን በሚጫወቱበት መንገድና በመምራት ችሎታቸው ከልጅነት ጊዜያቸው አንስቶ በእኩዮቻቸው ዘንድ የተለየ ከበሬታንና አድናቆት አግኝተዋል፡፡

በ1943 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስፖርት ጉዳዮች ሲቋቋም የአቶ ይድነቃቸው አስተዋጽኦ እጅጉን ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህም ቢሮ በዛኑ አመት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲመሠረት በር ከፈተ፡፡ ይድነቃቸው የተቋሙ ዋና ጸሀፊ ሆነው ሲሾሙ የመተዳደሪያ ደንቦችን ራሳቸው ወደ አማርኛ በመተርጎም አረቀቁ፡፡ በ1943 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ሻምፒዮና ላይም ተሳታፊ ከነበሩት አራት ቡድኖች አንዱ የይድነቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ይገኝበት ነበር፡፡ ሌሎቹ የግሪክ፣ ጣልያን እና የእንግሊዝ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ታህሳስ 5 ቀን 1947 ዓ.ም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን አለምአቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ (ከፈረንሳዩ የባህር ሐይል ቡድን ጋር ከተደረገው ግጥሚያ በኋላ) አድርጋ የጅቡቲን ብሄራዊ ቡድን አፄ ኀይለስላሴ በታደሙበት 5-0 ረታች፡፡ አቶ ይድነቃቸው በአጠቃላይ ከ1948 -1954 ለብሔራዊ ቡድኑ 15 የሚጠጉ ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ በአሰልጣኝነትና በእግርኳስ አስተዳደር ስራዎች ደግሞ እጅግ የገዘፈ አበርክቶ ነበራቸው፡፡ አቶ ይድነቃቸው ከኳስ ተጫዋችነቱ ከመገለላቸው አንድ አመት ቀድሞ ኢትዮጵያ በይፋ የአለም አቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) በመቀላቀል ከአፍሪካ አህጉር ከግብፅ፣ ሱዳን እና ደቡብ አፍሪካ ጋር አራተኛዋ አገር ሆነች፡፡

በ1957 ዓ.ም የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ካፍ) አህጉራዊ ውክልና ኖሮት በአለም አቀፉ እግርኳስ ማህበር ውስጥ እንዲሳተፍ ታቀደ፡፡ በምስረታ ስብሰባው ላይም አቶ ይድነቃቸው ኢትዮጵያን በመወከል ተገኙ፡፡ በወቅቱ የተሻለ አቅም የነበረውን ፌዴሬሽን የመሰረተችው ግብጽ የማህበሩን ጽህፈት ቤት በካይሮ አቋቁማ ግብፃዊው ጀነራል አብደላዚዝ ሳሊም የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት ሆነው ተሾሙ፡፡ ከግብፅ እና ኢትዮጵያ በመቀጠልም ደቡብ አፍሪካ እና ሱዳን ታዳጊውን ተቋም በአባልነት ተቀላቀሉ፡፡ ከድርጅቱ ምስረታ ጀርባ የይድነቃቸው ሚና የጎላ ነበር፡፡ የካፍን መተዳደሪያ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በተመሳሳይ አመት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሲጀመር በሶስት አገሮች ተሳትፎ በተካሄደው የመጀመሪያው ውድድር በፍፃሜው ግብጽ ኢትዮጵያን አሸንፋ ዋንጫውን ወሰደች፡፡

ከአምስት አመታት በኋላ አቶ ይድነቃቸው ራሳቸው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ በመሆን በውድድሩ ሀገራቸው የነበራትን ደረጃ ከፍ አደረጉ፡፡ እስካሁንም ድረስ በብቸኝነት የሚጠቀሰውን ትልቅ ዋንጫ አገሪቱ ራሷ ባዘጋጀችው ውድድር አሸናፊ እንድትሆን አስቻሏት፡፡ በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ በነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ላይ በሚያሳዩት ተቃውሞም ይታወቁ ነበር፡፡ ያለ አቶ ይድነቃቸው ውትወታ አራቱም መስራች አገራት በ1957 በዉድድሩ ጅማሮ ወቅት ሊገኙ ቢችሉም በጊዜው የደቡብ አፍሪካ እግርኳስ ማህበር (ሳፋ) ”ሁሉንም ጥቁር” አልያም “ሁሉንም ነጭ” ተጫዋቾች እንጂ በምንም አይነት ሁኔታ “ከሁለቱም የተዋሀደ” ቡድን ወደ ውድድሩ አልክም ማለቱን ተከትሎ ኢትዮጵያውያኖች ደቡብ አፍሪካ ከካፍ እንድትገለል ጫና በማሳደራቸው በ1958 ካፍ ደቡብ አፍሪካን ከአባል አገርነት አገዳት፡፡ በወቅቱ የይድነቃቸው የስራ ባልደረባና የካፍ ተወካይ አብድልሐሊም መሀመድ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ፖለቲካዊ ስርዓቷን በስፖርት ውስጥ እንዲንሰራፋ በማድረጓ ካፍ ከአባልነት ሲያገላት በይድነቃቸው የማያወላውል ጽኑ አቋም ምክንያት እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ በወቅቱ አለምአቀፍ ተቋም ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን አይነት ውሳኔ ያሳለፈው ካፍ ብቻ ነበር፡፡

በይድነቃቸው የሚመራው ካፍ የዘር ክፍፍል ፖለቲካን (በራሱ ክልልም ቢሆን) በስፖርቱ ውስጥ የሚያራምድ የትኛውም ፌዴሬሽን ከሞራል አንጻር ትክክል ያልሆነ እንዲሁም የተቋሙን ህግና ደንብ የሚጥስ በመሆኑ የአለም አቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) እንደዚህ ያሉ ፌዴሬሽኖችን ከተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ እንዲታገዱ የማድረግ እርምጃን እንዲወስድ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኗን የተለያየ ቀለም ካላቸው ተጫዋቾች እስከምታዋቅር ድረስ ከአለም አቀፉ ተቋም እንድትታገድ ጥያቄ ሲያቀርብ ካፍ በ1961 ጥያቄውን ተቀብሎ ተግባራዊ አደረገ፡፡ ነገር ግን በዚሁ አመት አዲሱ የፊፋ ፕሬዘዳንት ሆነው የተመረጡት ሰር ስታንሊ ሮውስ በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ አገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን እገዳ በ1963 አነሱ፡፡

ፕሬዘዳንት ስታንሊ ሮውስ ከካፍ እና አቶ ይድነቃቸው ጋር የከረረ አለመስማማት ነበራቸው፡፡ ለጆሀንስበርግ ስታር በሰጡት አስተያየትም ”እኛ የምንፈልገው በአገሪቱ ያለው እግር ኳሱን የሚቆጣጠረው የበላይ አካል ስፖርቱን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግረው ነው፡፡” ሲሉ ተናገሩ፡፡ ፊፋ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው የዘር ፖለቲካ ምንም እንኳ በስፖርቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ ቢገኝም ተቋሙን የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነ በማሰብ ዝምታን መረጠ፡፡ እንዲያውም ፕሬዘዳንት ሮውስ የአገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፊፋን ትዕዛዛት በአግባቡ እየተገበረ ስለመሆኑ ምስክርነት ሰጡ፡፡ ይባስ ብሎም በቀለም ልዩነት በተከፋፈለው እግርኳስ ላይ እርምጃ መውሰድ በራሱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ወደ ስፖርቱ ማምጣት ነው ሲሉ ተከራከሩ፡፡ <ዘ ቦል ኢዝ ራውንድ> ላይ ታዋቂው ዴቪድ ጎልድባት ”በፖለቲካዊ ዩኒቨርሳሊዝም ሽፋን ስር ተደብቆ የቆየው ዘረኝነት ውስጥ ውስጡን እያደባ ሄዶ ከአፓርታይድ ስርአት ጋር ሲያብር ያጠናከረው ሞራልና ልምድ ስርዓቱን ለማስወገድ ከፈየደው ይልቅ እግርኳስን ለማሳደግ ያበረከተው በለጠ፡፡” ሲል ጽፏል፡፡

በአዳዲስ ነፃነታቸውን በሚጎናፀፉ የአፍሪካ አገሮችና በእስያ አባል አገሮች ቁጥር መጨመር ምክንያት በፊፋ ስብሰባ ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች ሮውስን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከተታቸው፡፡ እስከ 1965 ድረስ ምክርቤቱ በ”አንድ አባልና አንድ ድምፅ ፖሊሲ” ሲሰራ ከረመ፡፡ ከአራትና ከአምስት አመታት ቀደም ብሎ 26 አባላት የነበሩት በአቶ ይድነቃቸው የሚመሩት አባላት “ድምጻችን ይሰማልን!” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡ <በፊፋ ኤንድ ኮንቴስት ፎር ወርልድ ፉትቦል> ውስጥ የሚሰሩት ጆን ሰደንና አለን ቶምሊንሰን እንዳሉትም “የአፍሪካ አገሮች የአለም እግርኳስ መድረክን ሉዓላዊ ነፃነታቸውን በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚያሳዩበት እና እውቅና ከሚያገኙበት ቁልፍ መንገዶች ዋነኛው አደረጉት፡፡ የኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ነፃነታቸውን የሚያሳዩበት አለማቀፍ ገጽታ ይኸው በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጪ ያለው እግር ኳሳዊ መስመር ሆነ፡፡”

በ1966 ዓ.ም በሮውስ የትውልድ ሀገር እንግሊዝ በተዘጋጀው የአለም ዋንጫ የአፍሪካውያኑ የኮታ ውትወታ ሰሚ አላገኘም፡፡ ከሁለት አመት በፊት የፊፋ ስብሰባ ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች ጋር ተዳብሎ በጃፓን ቶኪዮ ሲካሄድ ይህ አጋጣሚ ከደሀ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡትን ተወካዮች ተሳታፊ የማድረግ የተሻለ እድልን ፈጠረ፡፡ ከአፍሪካ፣እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ሶቭየት ህብረት በተገኘ ሰፊ ድጋፍና የጊዜው ምክትል የካፍ ፕሬዘዳንት አቶ ይድነቃቸው መሪነት የፊፋ ምክር ቤት ደቡብ አፍሪካ ላይ በድጋሚ የእገዳ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በወቅቱ የሮውስ ተገማች ቅሬታ ተቀባይነት አጣ፡፡ ካፍም ሮውስ በድጋሚ የእገዳ ውሳኔውን የሚቀለብሱ ከሆነ በቀጣዩ የፊፋ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ እንደማይሆን ቀድሞ ማስጠንቂያ ሰጠ፡፡ በስፖርቱ ውስጥ የሰነበተው ኢ-ፍትሐዊነትም ሌላው የቶኪዮ አጀንዳ ነበር፡፡

በእንግሊዝ የሚዘጋጀው የአለም ዋንጫ እየቀረበ በመጣበት ሰዓት ካፍ ወደ 30 የሚደርሱ አባል አገሮች ነበሩት፡፡ ሆኖም ለነዚህ ሁሉ አገራት በአለም ዋንጫ ለመሳተፍ የነበራቸው “ግማሽ እድል”ን የያዘ ከእስያ ጋር የሚጋራ ኮታ ነበር፡፡ የእያንዳንዱ አህጉር አሸናፊ አገር ለአንዷ የተሳትፎ ቦታ በብቸኝነት ለመግባት የማጣሪያ ጨዋታ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሮውስ እና ፊፋ የተሳትፎ ኮታውን ለመቀየር የፍቃደኝነት አዝማሚያ ማሳየት አልፈለጉም፡፡ ከአፍሪካ የሚመጡ በርካታ ተሳታፊዎች የውድድሩን የጥራት ደረጃ ያወርዱታል የሚለው ስጋት ደግሞ የባለስልጣናቱን ልብ አደንድኖታል። የአውሮፓውያኑን የመቆርቆር ሁኔታ የተመለከተው ብሪያን ግላንቪል በዚህ ጉዳይ “የኢትዮጵያ እና አሜሪካ አይነት አገሮች የአለም ዋንጫ ተሳትፎ የአገራቸውን እግር ኳስ የማሳደጉ ሚና ግልጽ ቢሆንም ውሳኔው የአለም ዋንጫን ደረጃ የማውረድ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያመጣ መሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ የሆነው ውድድርን የማሳነስ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፡፡” ሲል ስለ ምዕራባውያኑ ፍራቻ ያወሳል፡፡

በአለም ዋንጫው ከሚነሳው የተሳትፎ ጥያቄ በተጨማሪ በፊፋ ምክር ቤት ውስጥ በቁጥር እያደገ በመጣው የታዳጊ አባል አገሮች እኩል ደረጃ የማግኘት አሰራር ላይ የሮውስ እምነት ሌሎችን የሚያሳምን አልነበረም፡፡ “ብዙ ሰዎች ተጨባጭ ያልሆነ ሀሳብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ እንግሊዝ ያለች እግርኳስ የተጀመረባትና ምስረታውን ያደራጀች አገር ወይም ደግሞ ሰፊ ልምድ ያለቸው፣ በፊፋ ምስረታ ወቅት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው እንዲሁም ደግሞ በአለም እግርኳስ ጉዳዮች ላይ በሚነሱ ችግሮች ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጣልያን እና ፈረንሳይ የመሳሰሉት አገሮች ከአፍሪካና እስያ ከሚመጡ አገሮች ጋር እኩል ድምጽ የመስጠት መብት መኖር የለበትም፡፡” ብለው አስተያየት ሰጡ፡፡ አቶ ይድነቀቻውም በዚህ የሮውስ የማንአለብኝነት አመለካከት ተገርመው ይበልጡን ግትር ሆኑ፡፡ ” ምንም እንኳ ለፊፋ መመስረት የተወሰኑ አህጉራት በተቋሙ  የእድገት ሒደት ውስጥ በሀሳብ፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ረገድ ያበረከቱትን የተሻለ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ብንረዳም እኛ የምንጠብቀው ግን ተቋሙ አለማቀፋዊ ድርጅት የመሆኑን ያህል በዴሞክራሲያዊ አሰራር የሁሉንም አባል አገራት መብቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የሚያስከብር እንዲሆን ነው፡፡ ሰለዚህም አሰራሩ በህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የአለም እግርኳስን ጥቅም እና አንድነትን በዘላቂ ሒደትን የሚከተል እንዲሁም በፊፋ ወስጥ ያሉት አባላት በሚያድግ ሚዛናዊ ውክልና እንዲሳተፉ መደረግ አለበት፡፡” ሲሉ ሞገቱ፡፡

አቶ ይድነቃቸው “አንድ አገር-አንድ ድምጽ” የሚለውን የምክር ቤቱን መመሪያ በስኬታማነት ከመታገላቸውም በላይ በሮውስ አመራር የአለም ዋንጫ አውሮፓን ማዕከል ባደረገው ንፍቀ-ክበብ ብቻ ተወስኖ እንዳይዘልቅና በሌሎች አህጉራትም እንዲዳረስ ረጃጅምና ተከታታይ የደብዳቤ ግንኙነቶችን ከሮውስ ጋር በማድረግ አፍሪካ የቀጥታ ተሳትፎ ኮታ ኖሯት እግርኳሷ እንዲበረታታና እንዲያድግ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡ በፊፋ ሀሳበ-ግትርነት ምክንያትም አፍሪካ በ1966ቱ የአለም ዋንጫ ተካፋይ ከመሆን ራሷን አገደች፡፡ በምላሹ ፊፋም ለአፍሪካ እግርኳስ ማህበር የሚለግሰውን በሺዎች የሚቆጠር የፈረንሳይ ገንዘብ አስቀረ፡፡ ሆኖም በዚያው አመት በተካሄደው የፊፋ ስብሰባ ካፍ አሸናፊ ሆኖ ወጣ፡፡ በ1970ው የአለም ዋንጫም አፍሪካ የሙሉ ተሳትፎ ኮታ አገኘች፡፡ የሙሉ ተሳትፎው ፈቃድ የተሰጠው ካፍ ከፊፋ አባልነት ራሱን እንደሚያገል በማሳወቁ እና ሮውስ የደቡባዊ አፍሪካ የእግርኳስ ማህበርን በተለይም ደግሞ ደቡብ አፍሪካና ሮዴሺያን ይረዳሉ በሚል የሚወጣውን መረጃ ለማስተባበል ይረዳቸው ዘንድ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የአፍሪካን እግርኳስ ጥቅምና ፍላጎት በአለምአቀፍ ደረጃ በማስጠበቅ ረገድ የአቶ ይድነቃቸው ሚና እየጎለበተ ሄዶ ኃላፊነታቸውም ጨመረ፡፡ በ1966 ዓ.ም. የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ በ1967 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሀፊ እና በ1972 ደግሞ የካፍ ፕሬዘዳንት ሆነው ተሾሙ፡፡ በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ከጥሩ አማርኛ ተናጋሪነታቸው በተጨማሪ እንግሊዘኛን፣ ፈረንሳይኛን እና ጣልያንኛን  በጥሩ ሁኔታ መናገር መቻላቸው በአለም አቀፍ ስፖርት አስተዳደር መድረኮች ውስብስቡን ፖለቲካ በአፍሪካ የእንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ ማዕዘናት በተሟላ ክህሎት ለማሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶላቸዋል፡፡

በ1970ዎቹ የአቶ ይድነቃቸው አስተዳደራዊ  አቅም ከፍታው ላይ ወጣ፡፡ በ1960ዎቹ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓትን በመቃወም እና በአለም ዋንጫ የአፍሪካ አገሮች ተሳትፎን በሚመለከት በተደረገው ትግል የካፍ ባለስልጣናት አውሮፓን ማዕከል ባደረገው የፊፋ አመራር ውስጥ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በተቃውሞ አሳዩ፡፡ በፊፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የነበረውን የተማከለ የስልጣን ክምችት ማከፋፈል መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ይድነቃቸው ቀድመው ተረዱ፡፡ ሮውስ በ1960ዎቹ ለደቡብ አፍሪካ እና ሮዴሽያ በሚያደርጉት ያልተቋረጠ እርዳታ የካፍን ባለስልጣናት ማስከፋታቸውን ሲያያይዙት ካፍም በምላሹ በ1965 ሮዴሽያን የዘር መድልዎ ፓለቲካን በስፖርቱ ውስጥ አንሰራፍታለች ብሎ ከካፍ አባልነቷ አነሳት፡፡ ሆኖም አገሪቷ እስከ 1970 ድረስ በፊፋ አባልነቷ ሰነበተች፡፡

ለታላቁ የአስተዳደር ሰው አቶ ይድነቃቸው ካፍ የተቋሙን ግብ ካሰበበት እንዲያደርስ፣ በአለም ዋንጫ የተሳታፊ አገራቱ ቁጥር እንዲጨምር፣ ፊፋ ከቀረጥ ውጪ ከሚያገኘው ትርፍ ተገቢውን የእድገት ድጎማ እንዲያገኝና እንዲያድግ እንዲሁም በስፖርት ውስጥ የሚታየውን የዘር መድልዎ ለመቃወም ፕሬዘዳንት ሮውስ ከፊፋ መንበራቸው መነሳት ነበረባቸው፡፡ የ1974ቱ የፊፋ ስብሰባ ሲቃረብ ሮውስ በብራዚሉ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ጃኦ ሀቫላንጅ ከፍተኛ ፉክክር ገጠማቸው፡፡ ሀቫላንጅም በእንግሊዛዊው የአስተዳደር ዘመን ቅሬታ የነበረባቸውን ቦታዎች በቀጥታ አተኮሩባቸው፡፡ የአለምን እግርኳስ በአዲስ የአስተዳደር ስርዓት መንገድ እንደሚቀይሱለትና በደቡባዊው የአለም ንፍቀ ክበብ ላይ እንደሚያተኩሩ ቃል ገቡ፡፡ በ”ምረጡኝ” ዘመቻው 86 ያህል አገሮችንም ሲጎበኙ በአፍሪካና ኤዥያ ድምፅ በሚያገኙባቸው ቦታዎች ላይም ትኩረታቸውን አደረጉ፡፡ የአፓርታይድ ስርዓት የተንሰራፋባትን ደቡብ አፍሪካንም ከፊፋ አባልነቷ እስከመጨረሻው እንደሚያግዷት፣ አፍሪካ በአለም ዋንጫ የምትወከልበትን ቁጥር እንደሚጨምሩና ለአዳዲስ የህብረት ጥምረቶች (ኮንፌዴሬሽኖች) የፊፋ አባልነትን ፈቃድ እንደሚሰጡ አሳወቁ፡፡

በተፃራሪው ወገን የነበረው የሮውስ የ”ምረጡኝ” ቅስቀሳ በሰለጠነ መንገድ ያልተሰራበት፣ በትምክህት የታጀበና ለካፍ አባል አገራት ምንም አይነት አዲስ ጥቅም ይዞ ያልመጣ ሆኖ ቀረበ፡፡ ስለዚህም የሀቫላንጅ መንገድ አቶ ይድነቃቸው ለሚፈልጉት የካፍ አላማ መሣካት ጥሩ ምርጫን ፈጠረ፡፡ አቶ ይድነቃቸው ሀቫላንጅን በደቡብ አፍሪካ በ1973 ዓ.ም በሚካሄደው የስፖርት ፌስቲቫል ላይ እንዳትሳተፍ ወተወቱ፡፡ ፌስቲቫሉ በደቡብ አፍሪካ የነገሰውን አፓርታይዳዊ አገዛዝ አለም አቀፍ እውቅና ለማሰጠት የታሰበበት ነበር፡፡ ሮውስ ራሳቸው ስለሁኔታው ሲያብራሩ “ብራዚላውያን ራሳቸውን ከፌስቲቫሉ አገለሉ፤ የአፍሪካ እግርኳስ ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ይድነቃቸው ሀቫላንጅ ከእኔ ጋር በነበረው የፊፋ ፕሬዘዳንትነት የምርጫ ፉክክር አገሩ ብራዚል በውድድሩ ከተሳተፈች የአፍሪካ አገሮችን የድጋፍ ድምፅ ሊያጣ እንደሚችል አስረድቶ አሳመነው፡፡” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

<አፍሪካ፣ እግርኳስና ፊፋ> በሚለው መጽሀፉ ፖል ዳርቢ ሀቫላንጅን በማገዝ አቶ ይድነቃቸው እና እርሳቸው የሚመሩት ካፍ በአለም እግርኳስ ላይ የነበረውን የስልጣን መደላድል መልሰው የሚያስተካክሉበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል ሲል ይሞግታል፡፡ “አቶ ይድነቃቸው የፊፋ ፕሬዘዳንትነት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የአፍሪካን የድጋፍ ድምጽ የማጣትን ስጋት ለሀቫላንጅ የሚያሳውቁበት የስልጣን መንበር ላይ መሆናቸው ካፍ በአለም እግርኳስ የፖለቲካ መስመር እያጎለበተ ያመጣውን ልምድና የራስ መተማመን ከማሳየቱም በላይ በምርጫው ላይ የሚሰጠው ድምጽ ዋጋም ለአህጉሪቱ መብትና ጥቅም የቆመ መሆኑን ጠቁሞ አልፏል፡፡ በእርግጥም በ1974ቱ የፊፋ ስብሰባ ላይ እንደታየው የአፍሪካ አገሮች ራሳቸውን የፊፋን መንበር ለመቆጣጠር በሚደረግ የስልጣን ሽኩቻ ድምፃቸውን የሚሰጡ ብቻ አድርገው የማያዩ እንደሆነ አመላካች ነገር አነሱ፡፡ ሀቫላንጅንም ቢሆን የተመለከቱት በተቋሙ ውስጥ የስልጣን ክፍፍል በማድረግ አፍሪካውያን በእግርኳሱ አለም የሚገባቸውን እድገት የሚያሳዩበትን መንገድ በትክክለኛው ሁኔታ የሚፈጥር መሪ ይሆናል ብለው ነው፡፡ ”

ሀቫላንጅ እና ይድነቃቸው

በ1974ቱ የፊፋ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሀቫላንጅ 68 ድምጽ በማግኘት 52 ድምጽ ከሰበሰቡት ሮውስ ላይ የፊፋን መንበረ ስልጣን ተረከቡ፡፡ አፍሪካም በ1960ዎቹ ስትታገልላቸው ለነበሩት አላማዎቿ ግልጽ ድጋፍ የሚያደርግ የእግርኳስ መሪን በ1970ዎቹ አጋማሽ አገኘች፡፡ ቀድሞ ከፊፋ ጋር ካፍ የማይስማማባቸውን ከውድድሮች ራስን የማግለል እና ከባለስልጣናቱ ጋር የሚደረጉ እልህ አስጨራሽ ትግሎች ሳይኖሩ የአፍሪካን ግቦች ማሳካት ተጀመረ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀቫላንጅ በዓለ-ሲመት የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በአፍሪካ አህጉር በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ተደረገ፡፡

በካፍ ደረጃ በ1960ዎቹ በአንገብጋቢነት ሲነሱ የነበሩ ሁለት ትልልቅ አጀንዳዎች ላይ አዎንታዊ መፍትሔዎች ተገኙ፡፡ ካፍ በፍራንክፈርት በተካሄደው የ1974ቱ የፊፋ ስብሰባ <የጎሳ፣ የዘር እና የሐይማኖት መድልዎን> በአገሩ ውስጥ የሚያሰፍን ማንኛውም የፊፋ አባል አገር ከዚህ ድርጊቱ የማይታቀብ ከሆነ ፈጣን የእገዳ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ሐሳብ አቀረበ፡፡ በሮውስ ዘመን ቅሬታ ፈጥሮ የደቡብ አፍሪካን የአባልነት እገዳ በእንጥልጥል ያስቀረውንና የአሻሚነት ችግር ውስጥ የከተተውን ጉዳይ አነሳ፡፡ ከዚህ ስብሰባ ቀደም ብሎ በዚያው አመት በሞንትሪያል በተደረገ ጉባኤ አቶ ይድነቃቸው በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን ተስፋ ለፊፋ ተወካዮች በፃፉት ጽሁፍ የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ “የፊፋ አመራሮች የተቋሙን ህግና ደንቦች ይዘው የማስቀጠል ድፍረቱና ፍላጎቱ አላቸው፡፡ የፊፋ ህግ በደቡብ አፍሪካ ነጮችን አልያም ጥቁሮችን የሚመለከት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሳይሆን በአገሪቱ ያለውን የዘር መድልዎ የሚፃረር ነው፡፡” ከዚያም በ78-9 የድምጽ ብልጫ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ አባልነቷ ተባረረች፡፡ የካፍ አላማዎች በመሳካት ጉዞአቸው ቀጠሉ፡፡ ቀጣዩ የካፍ ስኬት በሜዳ ውስጥ ካሉት ጉዳዮች ባንዱ የተከተለ ነው። በ1978 ያለምንም ከባድ ተጋድሎ እና አድማ የአፍሪካ በአለም ዋንጫ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ሁለት አደገ።

በ1980ዎቹ በሀቫላንጅ የስልጣን ስርዓት ያልተለመዱ አሉታዊ ገጽታዎች መታየት ጀመሩ፡፡ የፊፋ የግብይት ማዕቀፍ የስፖርታዊ አንድነትን ከመፍጠር ይልቅ የገቢ መጠንን በማሳደግ ሒደት ላይ አተኮረ፡፡ ከባድ የሙስና ስርአቶችም ሰፈኑ፡፡ ፍጹም ታማኙ አቶ ይድነቃቸው በዚህ ችግር ዘርፍ ያመጡት ለውጥ ሳይታይ ቀረ፡፡ በካፍ የሐላፊነት ዘመናቸው ሁለቱን ትልልቅ ህልማቸውን በሀቫለንጅ ጊዜ ቢያሳኩም ከዛ በኋላ በፊፋ ውስጥ በተፈጠረው ብልሹ አሰራር ምክንያት ለሀቫለንጅ ድጋፍ መስጠታቸው ይቆጫቸው ይሆን? በካፍ ምክትላቸው የነበሩት ኢሳ ሐያቱስ ይህን ሁሉ ጊዜ በስልጣን ይቆዩ ነበር? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው፡፡

በእርግጥ አቶ ይድነቃቸው የአፍሪካ እግርኳስ የወደፊት አቅጣጫን በሚመለከት ከፍተኛ የሆነ ሀሳብ ነበራቸው፡፡ በየትኛው የፕሮፌሽናሊዝም ስርአት አንድነቱን በጠበቀ መልኩ የስፖርት ፉክክሩን ማካሄድ እንደሚቻል ለረጅም ጊዜ በጥርጣሬ ሲመለከቱት የቆዩት ጉዳይ ነው፡፡ በኦሎምፒክ ውስጥ ያለውን እግርኳስ በአማተርነት በመደገፍ (በ1971 የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሆነው ነበር፡፡) በግብይት ስርዓቱ በዝባዥ መንገድን ከሚከተለው የሀቫላንጅ አመራር ይልቅ ለወግ አጥባቂው ሰር ስታንሊ ሮውስ የቀረበ እምነት ነበራቸው፡፡

በ1987 ዓ.ም በካንሰር ህመም ምክንያት በ65 አመት እድሜያቸው ከመሞታቸው ቀደም ባሉት አመታት ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በሚሰደዱት በርካታ ወጣት እግርኳስ ተጫዋቾች እጣፈንታ ጉዳይ ፍሬቢስ ከሆኑ ውሳኔዎች እንዲቆጠቡ የራሳቸው የሚሉትን ሐሳብ አቅርበዋል። በተጨማሪም የተጫዋቾቹ ፍልሰት በራሱ የአፍሪካ ስፖርት እድገት ላይ በሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ዙሪያ የነበራቸውን ስጋት ገልፀው ነበር፡፡ “የአፍሪካ እግርኳስ አመራሮች ተጫዋቾችን በአህጉሪቱ ምድር አቆይቶ በጊዜ ሒደት በአለምአቀፍ ውድድሮች ከፍታ ላይ ባልተበዘበዘ አቅም ለማድረስ አስችሎ የአፍሪካን ህዝብ ክብር እንዲመለስ የማድረግ አልያም ደግሞ ተጫዋቾችን ከነጥሩ ክህሎታቸው ከአገራቸው እየተሰደዱ ለሌሎች አገሮች የሚጠቅሙበትንና ምንም አይነት የሀገር ስሜት ሳይኖራቸው የሚያድጉበትን ሒደት የመምረጥ ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው፡፡ ሀብታሞቹ ሀገራት ምርጥ እሴቶቻችንን ሲወስዱብን በተሻለው የማደጊያ ቦታ እንኳ ቢሆን የአፍሪካን እግርኳስ የመርዳት ፍላጎት አያሳዩም፡፡”ሲሉ የወደፊቱን የአፍሪካ እግርኳስ መልክ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው በረጅሙ የማስተዳደር ስራ ዘመናቸው የሚታወሱት በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ፍትህን ለማስፈን በጽናት ያካሄዱት ትግል ነው፡፡ በአለም እግርኳስ የአስተዳደር አቀራረባቸውም በልዩነት የሚጠቀስ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *