ሪፖርት | መቐለ ከተማ ከሜዳው ውጪ ድል በማስመዝገብ ከመሪው ያለውን ልዩነት አጥብቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ በእንግዳው ቡድን መቐለ አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ኤሌክትሪኮች ወደ ጎንደር አቅንተው በፋሲል ከተሸነፈው ስብስባቸው መካከል በጥላሁን ወልዴ ምትክ ተክሉ ተስፋዬን በመጀመርያ አሰላለፍ አካተው ሲቀርቡ መቐለ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት ሲዳማን ከረታው ስብስባቸው መካከል ዳንኤል አድሀኖም እና ሐብታሙ ተከስተን በዮናስ ግርማይ እና ኃይሉ ገብረየሱስ ምትክ በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል። በመቐለ ከተማ በኩል አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በፌዴሬሽኑ የአምስት ጨዋታ ቅጣት ቢተላለፍባቸውም ይግባኝ በመጠየቃቸው ጉዳዩ በድጋሚ እስኪታይ ጨዋታ እንዲመሩ ተፈቅዶላቸው በዛሬው ጨዋታ ቡድኑን መምራት ችለዋል።

በ9:05 ሲል በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች እርጋታ በጎደለው እና በተዘበራረቀ የጨዋታ አቀራረብ የቀረቡ ሲሆን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በሚመስል መልኩ የመሀለኛው የሜዳ ክፍል ላይ አዘንብለው ተስተውለዋል። ጨዋታው 25 ደቂቃዎች ከተጓዘ በኋላ እየተጋጋለ የመጣ ሲሆን ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመግባት ሲጥሩም ተስተውሏል።

በ31ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለው አጥቂ ጋይስ ቢስማርክ በኤሌክትሪክ የግብ ክልል በግብ ጠባቂው ዮሀንስ በዛብህ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል በአግባቡ በመጠቀም መቐለ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ኤሌክትሪኮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው ደቂቃም 6 ብቻ ነበር። በ36ኛው ደቂቃ ከዲዲዬ ለብሪ በቀኝ መስመር በኩል የተሻገረውን ኳስ ካሉሻ አልሀሰን እና የመቐለ ተከላካዮችን አልፋ ነጻ አቋቋም ላይ በነበረው ተክሉ ተስፋዬ እግር ስር ስትገባ አማካዩ በአግባቡ በመጠቀም ኤሌክትሪኮችን አቻ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ከአቻነት ጎሉ በኋላ በቀሩት የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ መቐለዎች በአንፃሩ በማፈግፈግ የመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ዘካርያስ ቱጂ ከቀረጣት ምት መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ዲዲዬ ለብሪ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የመታውና የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችው ኳስ ኤሌክትሪክ በመሪነት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ ለማስቻል የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገቡት ኤሌክትሪኮች ከመጀመርያው በተሻለ መልኩ የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾትን በመጨመር በማጥቃት አቀራረብ ወደ ሜዳ ቢገቡም ለተጋጣሚያቸው ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ክፍተት መተዋቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በ54ኛው ደቂቃ ጋይስ ቢስማርክ በኤሌክትሪክ ተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ ነበር። በ66ኛው ደቂቃ ተስፋዬ መላኩ ያሻገረውን ኳስ አልሀሰን ካሉሻ በአክሮባቲክ ምት ቢሞክረውም ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

በሙከራዎች ረገድ የተቀዛቅዞ የታየው ጨዋታ በተደጋጋሚ በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት መቐለዎች በ86ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ አሸናፊ የሚሆኑበትን ጎል ማግኘት ችለዋል። ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኢቮኖ በረጅሙ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል የለጋው ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች የትኩረት ማነስ ታክሎበት አማኑኤል ገብረሚካኤል በፍጥነት አምልጦ በመግባት ወሳኟን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ኤሌክትሪኮች በቀሩት ደቂቃዎች ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የመቐለን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል። ሆኖም በ88ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ቱጂ ያሻገረውን ኳስ ፊሊፕ ኢቮኖ ለመያዝ ሲሞክር አምልጦት ግብ ለመሆን ተቃርቦ አንተነህ ከመስመር ላይ ያወጣት ኳስ በባለሜዳዎቹ በኩል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

ጨዋታው በመቐለ ከተማ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በውድድር አመቱ ለሶስተኛ ጊዜ ከሜዳው ውጪ 3 ነጥቦች ያሳካው መቐለ ከተማ በ24 ነጥቦች ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ9 ነጥቦች የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለመቆየት ተገዷል።

 

የአሰልጣኞች አስተያየት


ቅጣው ሙሉ (የኤሌክትሪክ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ)

የሁለታችንም እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። በርካታ አጋጣሚዎችን አግኝተን አልተጠቀምንባቸውም። ይህ ደግሞ የሚያስቆጭ ነው። በተጨማሪም በመጨረሻ ሰአት ላይ ነው የማሰነፍያውን ጎል ያስቆጠሩብን። አንዳንድ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች በዛሬው ጨዋታ አልነበሩንም። ባለን አቅም እነሱን ለመተካት ሞክረናል። ነገር ግን አሁንም ከባድ ስራዎች እንደሚቀሩን አምናለሁ። አሁን ማሰብ ያለብን ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች ነው። በቀጣይ ጨዋታ ዛሬ የታዩብንን ክፍተቶች ለማረም ጥረት እናደርጋለን።


ዮሀንስ ሳህሌ – (መቐለ ከተማ )

ዘንድሮ ችግር የሆነብን ተጋጣሚዎቻችንን አለማወቃችን ነው። በምን አይነት ዘይቤ እንደሚጫወቱ ፣ ማን አደገኛ ተጫዋች እንደሆነ ፣ ምን አይነት አቀራረብ እንዳላቸው እና የመሳሰሉትን የምናውቀው ለጨዋታው ስንቀርብ ብቻ ነው። እዛው ጨዋታው ላይ ነወ ብዙ ነገሮችን የምናስተካክለው። አጨዋወታችንን በጨዋታው መሐል እየቀያየርን እዚህ ደርሰናል። ከጨዋታ ጨዋታ ራሳችንን እያሻሻልን ለቀጣይ ጨዋታዎች ለመቅረብ ነው የምንጠረው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *