የኤሌክትሪክ አመራሮች ከቡድኑ አባላት ጋር ተወያይተዋል

​የኢትዮ ኤሌክትሪክ አመራሮች ትላንት ምሽት ከቡድኑ አባላት ጋር ስብሰባ ማድረጉ ተሰምቷል። ተጫዋቾቹ እያነሱት የሚገኘውን ቅሬታ ለመቅረፍ ክለቡ ጥረት እንደሚያደርግ መግለፁም ታውቋል።

በፕሪምየር ሊጉ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ኤሌክትሪክ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ በ9 ነጥቦች ተቀምጧል። ክለቡ በውጤት መጥፋት ምክንያት አስቀድሞ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩን ወደ ሴቶች ቡድን በማሸጋሸግ ያለፉትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የለቀቁት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ቢሾምም ውጤቱን ማሻሻል አልቻለም።

ከክለቡ እየወጡ ባሉ መረጃዎች ከሆነ 16 የቡድኑ ተጫዋቾች በአዲሱ አሰልጣኝ ጉልበት ላይ ያመዘነ የልምምድ አሰጣጥ እና በመከላከል ላይ ያተኮረ የጨዋታ አቀራረብ ደስተኛ እንዳልሆኑ ከመግለፃቸው በተጨማሪ ክለቡ የሚያቀርበው ምግብ እና የሚሰጣቸው ኢንሴንቲቭ በቂ እንዳልሆነ በመግለፅ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ትላንት ምሽት ክለቡ ከተጫዋቾቹ እና አሰልጣኝ ቡድኑ ጋር ባደረገው ስብሰባም ተጫዋቾች በክለቡ ዙርያ አሉ ያሏቸውን ችግሮች የገለፁ ሲሆን ክለቡም ችግሮችን ለመፍታት እንደሚንቀሳቀስ በመግለፅ የቡድኑ አባላትም የክለቡን ስም የሚመጥን ስራ በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ አሳስቧል። በቀጣይ ከሲዳማ ቡና በሚያደርገው ጨዋታ ድል ከተቀዳጀ ከፍተኛ ኢንሴንቲቭ ይጠብቃቸዋልም ተብሏል።

ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ በተደጋጋሚ እየራቁ የሚገኙት አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ፣ ተከላካዩ ሞገስ ታደሰ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዐወት ገ/ሚካኤል አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ የመጀመርያ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የተሰጣቸው ሲሆን ክለቡ በበኩሉ ደብዳቤውን ለተጫዋቾቹ መላኩን አምኖ ውይይቱ ከተደረገ በኋላ በመተማመን ማስጠንቀቂያውን እንደተወዉ መግለፁ ተነግሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *